Este libro no es inspirado por Dios y no forma parte del canon cristiano ni del Tanaj judío. Se muestra solo con fines históricos y de estudio. Ver explicación completa መጽሐፈ ዮዲት 10 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ዮዲት ወደ ሆሎፎርኒስ ለመሄድ እንደ ተዘጋጀች 1 ከዚህም በኋላ ወደ እስራኤል አምላክ መለመኗን ከጨረሰችና ይህንም ነገር ሁሉ ከፈጸመች በኋላ፥ 2 ከወደቀችበት ቦታ ተነሣች፤ ብላቴናዋንም ጠርታ በሰንበታትና በበዓላት ቀኖች ወደምትቀመጥበት ቤትዋ ወረደች። 3 የለበሰችውንም ማቅ አወለቀች፤ የመበለትነትዋንም ልብስ ለበሰች፥ ሰውነትዋንም በውኃ ታጠበች፤ ጠጕርዋንም ያማረ ሽቱ ተቀባች፤ ጠጕርዋንም ተሠራች፤ አጌጠችም፤ ከዚህም በኋላ ባሏ ምናሴ በሕይወት በነበረ ጊዜ የምትለብሰውን የደስታ ልብሷን ለበሰች። 4 ጫማዋንም ተጫማች፤ አልቦዋንና ቀለበትዋን፥ አምባርዋንና ጉትቻዋንም አደረገች፤ ጌጡንም ሁሉ አጌጠች፤ የሚያዩአትንም ወንዶች ሁሉ ዐይን እስክታስት ድረስ ፈጽማ አጌጠች። 5 የወይኑን ገንቦና የዘይቱን ማሰሮ ትሸከም ዘንድ ለብላቴናዋ ሰጠቻት፤ ስልቅ በሶውን፥ የስንዴ አምባሻውንና በለሱን በስልቻዋ መላች፤ ገንዘብዋንም ሁሉ አንግታ አሸከመቻት። 6 ወደ ቤጤልዋ ከተማ በርም ሄደች፤ ዖዝያንን፥ ያገር ሽማግሌዎችን ከርሚንና ከብሪምንም በዚያ ቆመው አገኘቻቸው። 7 ፊትዋ ተለውጦ፥ በሚያስደንቅ ሁኔታ ልብሷን ለብሳ ባዩአት ጊዜ ከደም ግባቷ ማማር የተነሣ እጅግ ተደነቁ፤ እንዲህም አሏት፦ 8 “ለኢየሩሳሌም ልዕልናና ለእስራኤል ልጆች ክብር በልብሽ ያሰብሽውን ታደርጊ ዘንድ የአባቶቻችን አምላክ ሞገስን ይስጥሽ።” እርሷም ለእግዚአብሔር ሰገደች። 9 እንዲህም አለቻቸው፥ “አሁንም ከእናንተ ጋራ የተናገርሁትንነገር ወጥቼ አደርግ ዘንድ የከተማውን በር የሚከፍትልኝ ሰው እዘዙልኝ፤” እንደ ጠየቀችም ይከፍቱላት ዘንድ ጐልማሶችን አዘዙአቸው። 10 ይህንም በአደረጉ ጊዜ ዮዲት ወጣች፤ ብላቴናዋም ከእርሷ ጋር ወጣች፤ የከተማው ሰዎችም ካንባው ወርዳ ከሸለቆው እስክታልፍ ድረስ ያዩአት ነበር፤ ከዚህ በኋላ ግን አላዩአትም። 11 በቀጥታም በሸለቆው ሄደች፤ የአሦራውያንም ዘበኞች አገኙአት። 12 ይዘውም መረመሩአት፤ እንዲህም አሏት፥ “አንቺ ማን ነሽ? ከየት መጣሽ? ወዴትስ ትሄጃለሽ?” እርስዋም አለቻቸው፥ “እኔ ከዕብራውያን የተወለድሁ ነኝ፤ ሀገራቸውን ለእናንተ አሳልፈው ሊሰጡ በወደዱ ጊዜ ከእነርሱ ኰብልዬ መጣሁ። 13 እኔ እውነተኛ ነገርን እነግረው ዘንድ፥ የምትሄዱበትንም ጎዳና አሳየው ዘንድ ወደ ቢትወደዳችሁ ወደ ሆሎፎርኒስ አስቀድሜ መጣሁ፤ አውራጃቸውንም ሁሉ ገንዘብ ታደርጋላችሁ፤ ከሰዎቻችሁ አንድ ሰው ስንኳ የሚቈስል የለም።” 14 እነዚያም ሰዎች ቃልዋን በሰሙ ጊዜ፥ ፊትዋንም ባዩ ጊዜ፥ ደም ግባትዋም ፈጽሞ የተደነቀ እንደ ሆነ ባዩ ጊዜ እንዲህ አሏት፦ 15 “ወደ ጌታችን ፈጥነሽ የወረድሽ አንቺ ሕይወትሽን አዳንሽ። አሁንም ወደ ድንኳኑ ሂጂ፤ ወደ እርሱ የሚያደርስሽን ሰው ከእኛ እንልካለን። 16 በፊቱም በቆምሽ ጊዜ ይህን ነገርሽን ንገሪው እንጂ ልቡናሽ አይፍራ፤ በጎ ነገርን ያደርግልሻል።” 17 ከእርስዋና ከብላቴናዋ ጋር የሚሄዱ አንድ መቶ ሰዎችን መረጡ፤ ወደ ሆሎፎርኒስ ድንኳንም አደረሷት። 18 ሕዝቡም ሁሉ ተሰበሰቡ፤ በድንኳኑ ፊት እንዳለች ዜናዋ በሰፈሩ ተሰምቶ ነበርና መጥተው ስለ እርሷ እስኪነግሩት ድረስ ከሆሎፎርኒስ ድንኳን ውጭ ከብበዋት ቆሙ። 19 ደም ግባትዋንም አደነቁ፤ ስለ እርስዋም የእስራኤልን ልጆች አደነቁ፤ እርስ በርሳቸውም፥ “እንደ እነዚህ ያሉ ሴቶች ያሉትን ሕዝብ የሚንቅ ማን ነው? ዓለሙን ሁሉ ሊተነኰሉ ስለሚችሉ ከእነዚህ ሰዎች አንድ ሰውስ እንኳ ይቀር ዘንድ መልካም አይደለም” ተባባሉ። 20 በሆሎፎርኒስ አጠገብ የተቀመጡ አሽከሮቹም ሁሉ መጥተው ወደ ድንኳኑ አገቧት። 21 ሆሎፎርኒስም በወርቅ፥ በመረግድና ዋጋው ብዙ በሆነ ዕንቍ የተሠራ ነጭ ሐር በተነጠፈበት በዙፋኑ ላይ በድንኳኑ ውስጥ ተኝቶ ነበር። 22 የእርሷንም ነገር ነገሩት፤ ወደ አደባባይም ወጣ፤ በፊቱም የብር መቅረዝ ፋና ይበራ ነበር። 23 ዮዲትም ወደ እርሱ በቀረበች ጊዜ አሽከሮቹ ቆመው ነበር፤ ከመልኳ ደም ግባት የተነሣ ሁሉም ተደነቁ፤ እርሷም በግንባሯ በምድር ላይ ወድቃ ሰገደችለት፤ አሽከሮቹም አነሡአት። |