Este libro no es inspirado por Dios y no forma parte del canon cristiano ni del Tanaj judío. Se muestra solo con fines históricos y de estudio. Ver explicación completa መጽሐፈ ዮዲት 1 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ንጉሥ አርፋክስድ የባጥናን ዙሪያ እንደ ቀጸረ 1 በታላቅዋ ከተማ በነነዌ ለአሦር በነገሠ በናቡከደነፆር በዐሥራ ሁለተኛው ዓመት፥ ሜዶንንና ባጥናን ይገዛ የነበረው ንጉሥ አርፋክስድ፥ 2 የባጥናን ዙሪያ በለዘበ ድንጋይ ሠራ፤ በከተማዋ ወርድ በኩል የመሠረትዋ ስፋት ሠላሳ ክንድ ነው፤ በከተማዋ ፊት ለፊት ያለው ስፋት ስድሳ ክንድ ርዝመት ነው። የግንቡን ቁመት ሰባ ክንድ አድርጎ ሠራ፤ ማዕዘኑም አምሳ ክንድ ነው። 3 በየበሩ መቶ መቶ ክንድ እያለፈ የጕበኛ ቤቱን አቆመ፤ መሠረቱም ከማዕዘን እስከ ማዕዘን ድረስ ስድሳ ክንድ ነው። 4 ጽኑዓኑ፥ ኀያላኑና የጥበቃ ሠራዊቱ የሚገቡባቸው የሚከፈቱ የበሮችዋን ደጃፍ ቁመታቸውን ሰባ ክንድ፥ ስፋታቸውን አርባ ክንድ አድርጎ ሠራ። 5 በዚያም ወራት ናቡከደነፆር ንጉሡ አርፋስክድን በሰፊ ሜዳ ተዋጋው፤ ያም ሜዳ በራግው አውራጃ ያለ ነው። 6 በአምባ የሚኖሩ ሰዎችም ሁሉ ወጥተው ተቀበሉት፤ በኤፍራጥስና በጤግሮስ፥ በሒደስጶንም፥ በኤሊሜዎን ንጉሥ በአርዮክ ግዛት አውራጃ ያሉ ሁሉ የካሉድን ልጆች ይዋጓቸው ዘንድ እጅግ ብዙ የሆኑ አሕዛብም ተሰበሰቡ። 7 የፋርስ ንጉሥ ናቡከደነፆርም በፋርስ አውራጃ ለሚኖሩ ሁሉ፥ በቂልቅያ፥ በደማስቆና በሊባኖስ ምዕራብ ወደሚኖሩ ሁሉ በወንዝ ዳርም ወደሚኖሩ ሰዎች ሁሉ ላከ። 8 በቀርሜሎስና በገለዓድ፥ በገሊላና ሰፊ በሆነ በአስዴራን ምድረ በዳ ለሚኖሩ አሕዛብ። 9 በሰማርያና በአውራጃዋ ለሚኖሩ ሰዎች ሁሉ፥ በዮርዳኖስ ማዶ እስከ ኢየሩሳሌምና እስከ ቢላጢኒ፥ እስከ ኪሎስና እስከ ቃዴስ እስከ ግብፅ ወንዝ፥ ጣፍናስና ራሚስ እስከ ጌሴም ምድር ሁሉ። 10 በጣኔዎስና በሜኒፌዎስ በላይ እስኪደርስ በግብፅ ለሚኖሩ ሁሉ እስከ ኢትዮጵያ ድንበር ድረስ ሁሉ ላከ። 11 በምድር የሚኖሩ ሁሉ የፋርስ ንጉሥ የናቡከደነፆርን ትእዛዝ እንቢ አሉ፤ ከእርሱም ጋር ወደ ጦር አልሄዱም። አልፈሩትምና በፊታቸው እንደ አንድ ሰው ሆኗልና። መልእክተኞቹም ባዶአቸውን በውርደት ከፊታቸው ተመለሱ። 12 ናቡከደነፆርም በዚያች ምድር ላይ ፈጽሞ ተቈጣ፤ የቂልቅያንና የደማስቂኒስን፥ የሶርያንም አውራጃ ሁሉ ይበቀልና በሞዓብ ምድር የሚኖሩትን ሁሉ፥ የአሞንንም ልጆች ይሁዳንም ሁሉ በግብፅ የሚኖሩትንም ከሁለቱ ባሕሮች ድረስ ተበቅሎ በሰይፍ ያጠፋቸው ዘንድ በዙፋኑና በመንግሥቱ ማለ። ንጉሥ አርፋክስድ ድል እንደ ሆነ 13 ከሠራዊቱ ሁሉ ጋር ንጉሡ አርፋክስድን በነገሠ በዐሥራ ሰባተኛው ዓመት ተዋጋው፤ ድል ነሥቶም የአርፋክስድን ሠራዊቱን ሁሉ፥ ፈረሶቹንና ሰረገላዎቹን ሁሉ ወሰደ። 14 ሀገሮቹንም ሁሉ ያዘ፤ እስከ ባጥናም ድረስ ሄዶ አምባቸውን ያዘ፤ ሀገሩንም ሁሉ በረበረ፤ አጠፋትም። 15 አርፋክስድንም በራግው አውራጃ ይዞ በጦር ወጋው፤ ፈጽሞም አጠፋው። 16 እርሱም ተመለሰ፤ ከእርሱ ጋር ያሉ እጅግ አርበኞች የሆኑ ብዙ ሰዎችም ሁሉ ተመለሱ፤ በዚያም ሲያስብና ሲመክር መቶ ሃያ ቀን ተቀመጠ። |