ኢያሱ 6 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)የኢያሪኮ ቅጥር መውደቅ 1 ኢያሪኮም በግንብ ታጥራ ተዘግታ ነበር፤ ወደ እርስዋ የሚገባ፥ ከእርስዋም የሚወጣ አልነበረም። 2 እግዚአብሔርም ኢያሱን አለው፥ “እነሆ፥ ኢያሪኮንና ንጉሥዋን ጽኑዓን፥ ኀያላንዋንም በእጅህ ሰጥቼአለሁ። 3 አንተም ተዋጊዎችን ሁሉ በዙሪያው አሰልፋቸው። ተዋጊዎቻችሁም ሁሉ በከተማዪቱ ዙሪያ አንድ ጊዜ ይዙሩ፤ እንዲሁም ስድስት ቀን አድርጉ። 4 ሰባትም ካህናት ሰባት ቀንደ መለከት በታቦቱ ፊት ይያዙ፤ በሰባተኛውም ቀን ከተማዪቱን ሰባት ጊዜ ዙሩ፤ ካህናቱም ቀንደ መለከቱን ይንፉ። 5 ቀንደ መለከቱም ባለማቋረጥ ሲነፋ፥ የመለከቱን ድምፅ ስትሰሙ፥ ሕዝቡ ሁሉ ታላቅ ጩኸት ይጩኹ፤ የከተማዪቱም ቅጥር ይወድቃል፤ ሕዝቡም ሁሉ እያንዳንዱ ፊት ለፊት እየሮጠ ይገባባታል።” 6 የነዌም ልጅ ኢያሱ ካህናቱን ጠርቶ፥ “የቃል ኪዳኑን ታቦት ተሸከሙ፤ ሰባትም ካህናት ሰባት ቀንደ መለከት ወስደው በእግዚአብሔር ታቦት ፊት ይሂዱ” አላቸው። 7 ሕዝቡንም፥ “ሂዱ፤ ከተማዪቱንም ዙሩ፤ ተዋጊዎችም ከጦር መሣሪያዎቻቸው ጋር በእግዚአብሔር ታቦት ፊት ይሂዱ ብላችሁ እዘዙአቸው” አላቸው። 8 በእግዚአብሔርም ፊት ይሄዱ ዘንድ ኢያሱ እንደ ነገራቸው ሰባቱ ካህናት የተቀደሱ ሰባቱን ቀንደ መለከት ይዘው ሄዱ፤ በሄዱም ጊዜ አሰምተው በምልክት ነፉ፤ የእግዚአብሔርም የሕጉ ታቦት ትከተላቸው ነበር። 9 ሰልፈኞችም ፊት ፊት ይሄዱ ነበር፤ ካህናቱም ነጋሪት ይመቱ ነበር፤ ከታቦቱ በኋላ ይከተሉ የነበሩትም ቀንደ መለከቱን እየነፉ ይሄዱ ነበር። 10 ኢያሱም ሕዝቡን፦ እንዳይጮኹ ማንም ድምፃቸውን እንዳይሰማ፥ እንዲጮኹ እስኪያዛቸውም ድረስ ከአፋቸው ቃል እንዳይወጣ አዘዛቸው። 11 የእግዚአብሔርም የቃል ኪዳኑ ታቦት ሄደች፤ ከተማዪቱንም ዞረች፤ ወደ ሰፈርም ተመልሳ በዚያ አደረች። 12 ኢያሱም በማግሥቱ ማለዳ ተነሣ፤ ካህናቱም የእግዚአብሔርን የሕጉን ታቦት ተሸከሙ። 13 ሰባቱም ካህናት ሰባቱን ቀንደ መለከት ይዘው በእግዚአብሔር ታቦት ፊት ይሄዱ ነበር፤ ቀንደ መለከቱንም ይነፉ ነበር፤ ተዋጊዎችም በፊታቸው ይሄዱ ነበር፤ የቀሩትም ሕዝብ ከእግዚአብሔር የቃል ኪዳን ታቦት በኋላ ይሄዱ ነበር፤ ካህናቱም ቀንደ መለከቱን ይነፉ ነበር። 14 በሁለተኛውም ቀን የቀረው ሕዝብ ሁሉ ከተማዪቱን አንድ ጊዜ ዞረው ወደ ሰፈር ተመለሱ፤ ስድስት ቀንም እንዲህ አደረጉ። 15 በሰባተኛውም ቀን በነጋ ጊዜ ማልደው ተነሡ፤ እንደዚህም ከተማዪቱን ሰባት ጊዜ ዞሩ፤ በዚያም ቀን ብቻ ከተማዪቱን ሰባት ጊዜ ዞሩ። 16 እንዲህም ሆነ፤ ከተማዪቱን ሰባት ጊዜ በዞሩና ካህናቱ ቀንደ መለከቱን በነፉ ጊዜ፤ ኢያሱ ለእስራኤል ልጆች አለ፥ “እግዚአብሔር ከተማዪቱን ሰጥቶአችኋልና ጩኹ። 17 ከተማዪቱም በእርስዋም ያለው ሁሉ ለሠራዊት ጌታ ለእግዚአብሔር እርም ይሆናሉ፤ የላክናቸውን መልእክተኞች ስለ ሸሸገች ዘማዊቱ ረዓብ፥ ከእርስዋም ጋር በቤቷ ውስጥ ያሉ ሁሉ ብቻ በሕይወት ይኖራሉ። 18 እናንተ ግን እርም ብለን ከተውነው እንዳትወስዱ ተጠንቀቁ፤ ከእርሱም ተመኝታችሁ አትውሰዱ፤ ብትወስዱ ግን የእስራኤልን ሰፈር የተረገመች ታደርጓታላችሁ፤ እኛንም ታጠፉናላችሁ። 19 ነገር ግን ብርና ወርቅ ሁሉ፥ የናስና የብረትም ዕቃ ለእግዚአብሔር የተቀደሰ ይሁን፤ ወደ እግዚአብሔርም ግምጃ ቤት ይግባ።” 20 ሕዝቡም ጮኹ፥ ካህናቱም ቀንደ መለከቱን ነፉ፤ ሕዝቡም የቀንደ መለከቱን ድምፅ በሰሙ ጊዜ ታላቅ ጩኸት ጮኹ፤ ቅጥሩም ወደቀ፤ ሕዝቡም ሁሉ ወደ ከተማዪቱ ገቡ፤ ሁሉም ወደ ፊታቸው ወደ ከተማዪቱ ሮጡ፤ ከተማዪቱንም እጅ አደረጉ። 21 ኢያሱም ከተማዋን፥ በከተማዪቱም ውስጥ የነበሩትን ሁሉ፥ ከወንድ እስከ ሴት፥ ከሕፃን እስከ ሽማግሌ፥ ከበሬ እስከ በግና እስከ አህያ በሰይፍ ስለት ፈጽሞ አጠፋ። 22 ኢያሱም ምድሪቱን የሰለሉ ሁለቱን ሰዎች፥ “ወደ ዘማዪቱ ቤት ግቡ፤ ከዚያም ሴቲቱንና ያላትን ሁሉ እንደማላችሁላት አውጡ” አላቸው። 23 እነዚያም ከተማዪቱን የሰለሉ ሁለቱ ጐልማሶች ወደ ዘማዪቱ ረዓብ ቤት ገብተው ረዓብን፥ አባቷንና እናቷን፥ ወንድሞችዋንም፥ ያላትንም ሁሉ፥ ቤተ ዘመዶችዋንም ሁሉ አወጡአቸው፤ ከእስራኤልም ሰፈር በውጭ አስቀመጡአቸው። 24 ከተማዪቱንም፥ በእርስዋም የነበረውን ሁሉ በእሳት አቃጠሉ፤ ነገር ግን ብሩንና ወርቁን፥ የናሱንና የብረቱንም ዕቃ በእግዚአብሔር ግምጃ ቤት ውስጥ አገቡ። 25 ኢያሪኮን ሊሰልሉ ኢያሱ የላካቸውንም መልእክተኞች ስለ ሸሸገች ዘማዊቱን ረዓብን፥ የአባቷንም ቤተ ሰብ፥ ያላትንም ሁሉ ኢያሱ አዳናቸው፤ እርስዋም በእስራኤል መካከል እስከ ዛሬ ድረስ ተቀምጣለች። 26 በዚያችም ቀን ኢያሱ፥ “ይህችን ከተማ ኢያሪኮን ለመሥራት የሚነሣ ሰው በእግዚአብሔር ፊት ርጉም ይሁን፤ መሠረቷን በበኵር ልጁ የሚጥል፥ በሮችዋንም በታናሹ ልጁ የሚያቆም ርጉም ይሁን” ብሎ ማለ። 27 እግዚአብሔርም ከኢያሱ ጋር ነበረ፤ ስሙም በምድር ሁሉ ላይ ደረሰ። |