ኢያሱ 21 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ለሌዋውያን የተሰጡ ከተሞች 1 የሌዊ ልጆች አለቆች ወደ ካህኑ ወደ አልዓዛር፥ ወደ ነዌም ልጅ ወደ ኢያሱ ወደ እስራኤልም ሕዝብ አባቶች ነገዶች አለቆች መጡ፤ 2 በከነዓን ምድር ባለችው በሴሎ፥ “እግዚአብሔር በሙሴ እጅ የምንቀመጥባቸውን ከተሞች፥ ለከብቶቻችንም መሰማሪያዎች ትሰጡን ዘንድ አዝዞአል” ብለው ተናገሩአቸው። 3 የእስራኤልም ልጆች እንደ እግዚአብሔር ትእዛዝ ከርስታቸው እነዚህን ከተሞችና መሰማርያቸውን ለሌዋውያን ሰጡአቸው። 4 ለቀዓትም ወገኖች ልጆች ዕጣ ወጣ፤ ሌዋውያንም ለነበሩ ለካህኑ ለአሮን ልጆች ከይሁዳ ነገድ፥ ከስምዖንም ነገድ፥ ከብንያምም ነገድ ዐሥራ ሦስት ከተሞች በዕጣ ተሰጡአቸው። 5 ለቀሩትም ለቀዓት ልጆች ከኤፍሬም ነገድ፥ ከዳንም ነገድ፥ ከምናሴም ነገድ እኩሌታ ዐሥር ከተሞች በዕጣ ተሰጡአቸው። 6 ለጌድሶንም ልጆች ከይሳኮር ነገድ፥ ከአሴርም ነገድ፥ ከንፍታሌምም ነገድ፥ በባሳንም ካለው ከምናሴ ነገድ እኩሌታ ዐሥራ ሦስት ከተሞች በዕጣ ተሰጡአቸው። 7 ለሜራሪም ልጆች በየወገኖቻቸው ከሮቤል ነገድ፥ ከጋድም ነገድ፥ ከዛብሎንም ነገድ ዐሥራ ሁለት ከተሞች ተሰጡአቸው። 8 እግዚአብሔርም ሙሴን እንዳዘዘው የእስራኤል ልጆች እነዚህን ከተሞችና መሰማሪያቸውን ለሌዋውያን በዕጣ ሰጡ። 9 የይሁዳም ልጆች ነገድ፥ የስምዖንም ልጆች ነገድ፥ የብንያምም ልጆች ነገድ በስማቸው የተጠሩትን እነዚህን ከተሞች ሰጡአቸው። 10 የፊተኛው ዕጣ ለእነርሱ ስለወጣ የሌዊ ልጆች የቀዓት ወገን ለሆኑ ለአሮን ልጆች ሆኑ። 11 የኤናቅ ልጆች ከተማ ቅርያትያርቦቅንና በዙሪያዋ ያሉ መሰማሪያዎችን ሰጡአቸው፤ ይህችውም በይሁዳ ተራራ ያለች ኬብሮን ናት። 12 ኢያሱም የከተማዪቱን እርሻ መንደሮችዋንም ለዮፎኒ ልጅ ለካሌብ ልጆች ርስት አድርጎ ሰጣቸው። 13 ለካህኑም ለአሮን ልጆች እነዚህን ሰጡ፤ ለነፍሰ ገዳይ መማፀኛ ከተማ የሆነችውን ኬብሮንንና መሰማርያዋን፤ ሌምናንና መሰማርያዋን፥ 14 ኤቴርንና መሰማርያዋን፥ ኤታምንንና መሰማርያዋን፤ 15 ሄሎንንና መሰማርያዋን፥ ዳቤርንና መሰማርያዋን፥ 16 አሳንና መሰማርያዋን፥ ዮጣንንና መሰማርያዋን፥ ቤትሳሚስንና መሰማርያዋን፤ ከእነዚህ ከሁለቱ ነገዶች ዘጠኝ ከተሞችን ሰጡ። 17 ከብንያምም ነገድ ገባዖንንና መሰማርያዋን፥ ጋቲትንና መሰማርያዋን፤ 18 ዓናቶትንና መሰማርያዋን፥ አልሞንንና መሰማርያዋን፤ አራት ከተሞችን ሰጡ። 19 የካህናቱ የአሮን ልጆች ከተሞች ከመሰማሪያዎቻቸው ጋር ዐሥራ ሦስት ናቸው፤ 20 ለቀሩትም ለሌዋውያኑ ለቀዓት ልጆች የዕጣቸው ከተሞች ከኤፍሬም ነገድ ደረሱአቸው። 21 ለነፍሰ ገዳይ መማፀኛ ከተማ የሆነችውን ሴኬምንና መሰማርያዋን፥ ጌዜርንና መሰማርያዋን፤ 22 ቄብጻይምንና መሰማርያዋን፥ ቤቶሮንና መሰማርያዋን፤ አራቱን ከተሞች ሰጡአቸው። 23 ከዳንም ነገድ ኤልቆታይምንና መሰማርያዋን፥ ገባቶንንና መሰማርያዋን፤ 24 ኤሎንንና መሰማርያዋን፥ ጌቴራሞንንና መሰማርያዋን፤ አራቱን ከተሞች ሰጡአቸው። 25 ከምናሴም ነገድ እኩሌታ ጠናሕንና መሰማርያዋን፥ ዬባታንና መሰማርያዋን፤ ሁለቱን ከተሞች ሰጡአቸው። 26 የቀሩት የቀዓት ልጆች ወገኖች ከተሞች ሁሉ ከመሰማርያቸው ጋር ዐሥር ናቸው። 27 ለሌዋውያንም ወገኖች ለጌድሶን ልጆች ከምናሴ ነገድ እኩሌታ ለነፍሰ ገዳይ መማፀኛ ከተማ በባሳን ውስጥ የሆነችውን ጎላንንና መሰማርያዋን፥ ቦሶርንና መሰማርያዋን፤ ሁለቱን ከተሞች ሰጡአቸው። 28 ከይሳኮርም ነገድ ቂሶንንና መሰማርያዋን፥ ዳብራትንና መሰማርያዋን፤ 29 ሬማትንና መሰማርያዋን፥ ዓይንጋኒምንና መሰማርያዋን፤ አራቱን ከተሞች ሰጡአቸው። 30 ከአሴርም ነገድ መሴላንና መሰማርያዋን፥ አቤዶንንና መሰማርያዋን፥ 31 ሔልቃትንንና መሰማርያዋን፥ ረዓብንና መሰማርያዋን፤ አራቱንም ከተሞች ሰጡአቸው። 32 ከንፍታሌምም ነገድ ለነፍሰ ገዳይ መማፀኛ ከተማ የሆነችውን በገሊላ ውስጥ ቃዴስንና መሰማርያዋን፥ ኤማትንና መሰማርያዋን፥ ቃርቴንንና መሰማሪያዋን፤ ሦስቱን ከተሞች ሰጡአቸው። 33 የጌድሶን ልጆች ከተሞች ሁሉ በየወገኖቻቸው ዐሥራ ሦስት ከተሞች ከመሰማርያቸው ጋር ናቸው። 34 ከሌዋውያን ለቀሩት ለሜራሪ ልጆች ወገን ከዛብሎን ነገድ ዮቅናምንና መሰማርያዋን፥ ቃዴስንና መሰማርያዋን፥ 35 ዲምናንና መሰማርያዋን፥ ሴላንና መሰማርያዋን፤ አራቱን ከተሞች ሰጡ። 36 በዮርዳኖስ ማዶ በኢያሪኮ በኩል ከሮቤል ነገድ ለነፍሰ ገዳይ መማፀኛ በሚሶን ምድረ በዳ ቦሶርንና መሰማርያዋን፥ ኢያዜርንና መሰማርያዋን፤ 37 ቄዴሞትንና መሰማርያዋን፥ ሜፍዐትንና መሰማርያዋን፤ አራቱን ከተሞች ሰጡ። 38 ከጋድም ነገድ ለነፍሰ ገዳይ መማፀኛ ከተማ የሆነችውን በገለዓድ ውስጥ ራሞትንና መሰማርያዋን፥ ቃሚንንና መሰማርያዋን፤ 39 ሐሴቦንንና መሰማርያዋን፥ ኢያዜርንና መሰማርያዋን፤ አራቱን ከተሞች ሰጡ። 40 ከሌዊ ወገኖች የቀሩት የሜራሪ ልጆች ከተሞች ሁሉ በየወገኖቻቸው እነዚህ ነበሩ፤ ዕጣቸውም ዐሥራ ሁለት ከተማ ነበረ። 41 በእስራኤል ልጆች ርስት መካከል የነበሩት የሌዋውያን ከተሞች ሁሉ በእነዚህ ከተሞች ዙሪያ ካሉ ከመሰማርያዎቻቸው ጋር አርባ ስምንት ከተሞች ነበሩ። 42 እነዚህም ከተሞች እያንዳንዳቸው ከመሰማርያቸው ጋር ነበሩ፤ እነዚህም ከተሞች ሁሉ እንዲሁ ነበሩ። [ኢያሱም በየድንበሮቻቸው ምድርን ማካፈልን ጨረሰ። የእስራኤል ልጆችም ለኢያሱ በእግዚአብሔር ትእዛዝ ድርሻውን ሰጡት፤ እርሱ የሚፈልጋትን ከተማ በኤፍሬም ተራራ የምትገኘውን ቴምናሴራን ሰጡት፤ ከተማም ሠራባት፤ በውስጧም ተቀመጠ። ኢያሱም በምደረ በዳ በመንገድ የተወለዱትን የገረዘባቸውን የድንጋይ ባልጩቶች ወስዶ በቴምናሴራ አኖራቸው።] እስራኤል ምድሪቱን ወርሰው ዕረፍት እንዳገኙ 43 እግዚአብሔርም ይሰጣቸው ዘንድ ለአባቶቻቸው የማለላቸውን ምድር ሁሉ ለእስራኤል ሰጠ፤ ወረሱአትም፥ ተቀመጡባትም። 44 እግዚአብሔርም ለአባቶቻቸው እንደ ማለላቸው በዙሪያቸው ካሉት አሳረፋቸው፤ ከጠላቶቻቸውም ሁሉ ይቋቋማቸው ዘንድ ማንም ሰው አልቻለም፤ እግዚአብሔርም ጠላቶቻቸውን ሁሉ በእጃቸው አሳልፎ ሰጣቸው። 45 እግዚአብሔር ለእስራኤል ቤት ከተናገረው መልካም ነገር ሁሉ ተፈጸመ እንጂ ምንም አልቀረም። |