ኢያሱ 17 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)የምናሴ ነገድ እኩሌታ ርስት 1 የምናሴ ልጆች ነገድ ድንበር ይህ ነው፤ የዮሴፍ በኵር እርሱ ነውና። የምናሴም በኵር የገለዓድ አባት ማኪር ብርቱ ተዋጊ ስለ ነበረ ገለዓድንና ባሳንን ወረሰ። 2 ዕጣውም ለቀሩት ለምናሴ ልጆች በየወገኖቻቸው፥ ለኢያዜር ልጆች፥ ለቄሌዝ ልጆች፥ ለኢየዚኤል ልጆች፥ ለሴኬም ልጆች፥ ለሱማሪም ልጆች፥ ለኦፌር ልጆች ሆነ፤ ወንዶቹ በየወገኖቻቸው እነዚህ ናቸው። 3 ለኦፌር ልጅ፥ ለሰለጰዓድ ግን ሴቶች ልጆች እንጂ ወንዶች ልጆች አልነበሩትም፤ የሰለጰዐድም የሴቶች ልጆቹ ስሞች፦ መሐላ፥ ኑዓ፥ ሔግላ፥ ሚልካ፥ ቴርሳ ነበሩ። 4 እነርሱም ወደ ካህኑ ወደ አልዓዛርና ወደ ነዌ ልጅ ወደ ኢያሱ ወደ አለቆችም ቀርበው፥ “እግዚአብሔር በወንድሞቻችን መካከል ርስት እንዲሰጠን በሙሴ እጅ አዘዘ” አሉ፤ በእግዚአብሔርም ትእዛዝ ከአባታቸው ወንድሞች ጋር ርስት ሰጣቸው። 5 ዕጣቸውም በዮርዳኖስ ማዶ ከአለው ከገለዓድና ከባሳን ሀገር በቀር ለምናሴ ዐሥር ዕጣ ሆነ፤ 6 የምናሴ ሴቶች ልጆች በወንድሞቻቸው መካከል ርስት ተቀብለዋልና፤ የገለዓድም ምድር ለቀሩት ለምናሴ ልጆች ሆኖአልና። 7 የምናሴም ልጆች ድንበር በሐነት ልጆች ፊት ያለው ዴላናታ ነው። በኢያሚንና በኢያሲብ ድንበር በተፍቶት ምንጭ ላይ ያልፋል። 8 የጣፌት ምድር ለምናሴ ነበረ፤ ጣፌት ግን በኤፍሬም ልጆችና በምናሴ ልጆች አውራጃ ያለ ነው። 9 ድንበራቸውም በደቡብ በኩል ወዳለው ወደ ቃራና ሸለቆና ወደ ኢያሪያል ሸለቆ ይወርዳል፤ የኤፍሬም ዕጣ የሆነው ጤሬሜንቶስ የሚባለው ዛፍም በምናሴ ከተሞች መካከል አለ፤ የምናሴም ድንበር በሰሜን በኩል ወደ ወንዙ ይወርዳል፤ መውጫውም በባሕሩ አጠገብ ነበረ። 10 በደቡብ በኩል ያለው ለኤፍሬም ነበረ፤ በሰሜን በኩል ያለውም ለምናሴ ነበረ፤ ድንበሩም ባሕር ነበረ፤ በሰሜን በኩል ወደ አሴር፥ በምሥራቅም በኩል ወደ ይሳኮር ይደርሳል። 11 በይሳኮርና በአሴር መካከል ቤትሳንና መንደሮችዋ፥ ዶርና መንደሮችዋ፥ መጌዶና መንደሮችዋ፥ የመፌታ ሦስተኛ እጅና መንደሮችዋ ለምናሴ ነበሩ። 12 የምናሴ ልጆችም የእነዚህን ከተሞች ሰዎች ማጥፋት ተሳናቸው፤ ነገር ግን ከነዓናውያን በዚያች ሀገር ለመቀመጥ መጡ። 13 የእስራኤልም ልጆች በረቱባቸው፤ ከነዓናውያንንም ገዙአቸው፤ ነገር ግን ፈጽመው አላጠፉአቸውም። የኤፍሬምና የምናሴ ነገድ እኩሌታ ተጨማሪ ርስት መጠየቃቸው 14 የዮሴፍም ልጆች ኢያሱን፥ “እኛ ብዙ ሕዝብ ስንሆን እስከ አሁንም እግዚአብሔር ስለ ባረከን ለምን አንድ ክፍል፥ አንድም ዕጣ ብቻ ርስት አድርገህ ሰጠኸን?” ብለው ወቀሱት። 15 ኢያሱም፥ “ብዙ ሕዝብ ከሆናችሁ፥ ተራራማው የኤፍሬም ሀገርም ከጠበባችሁ ወደ ዱር ወጥታችሁ መንጥራችሁ አቅኑአት” አላቸው። 16 እነርሱም፥ “ተራራማው የኤፍሬም ሀገር አይበቃንም፤ በሸለቆው ውስጥ ለሚኖሩት፥ በቤትሳንና በመንደሮችዋ፥ በኢይዝራኤልም ሸለቆ ለሚኖሩት ከነዓናውያን የተመረጡ ፈረሶችና ሰይፍ አሏቸው” አሉት። 17 ኢያሱም ለዮሴፍ ልጆች፥ “እናንተ ብዙ ሕዝብ ከሆናችሁ፥ ጽኑ ኀይልም ከአላችሁ አንድ ዕጣ ብቻ አይሆንላችሁም፤ 18 ነገር ግን ተራራማው ሀገር ለእናንተ ይሆናል፤ ዱር እንኳ ቢሆንም ትመነጥሩታላችሁ፤ ለእናንተም ይሆናል፤ ለከነዓናውያንም የተመረጡ ፈረሶችና የብረት ሰረገሎች ቢሆኑላቸው፥ የበረቱ ቢሆኑም እናንተ እስክታጠፉአቸው ድረስ ትበረቱባቸዋላችሁ” አላቸው። |