ዮሐንስ 2 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)በቃና ዘገሊላ ስለ ተደረገው ሰርግ 1 በሦስተኛውም ቀን የገሊላ ክፍል በምትሆን በቃና ሰርግ ሆነ፤ የጌታችን የኢየሱስ እናትም በዚያ ነበረች። 2 ጌታችን ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱም ወደ ሰርጉ ታደሙ። ስለ እናቱ ምልጃ 3 የወይን ጠጃቸውም ባለቀ ጊዜ እናቱ ጌታችን ኢየሱስን፥ “የወይን ጠጅ እኮ የላቸውም” አለችው። 4 ጌታችን ኢየሱስም፥ “አንቺ ሆይ ካንቺ ጋር ምን አለኝ? ጊዜዬ ገና አልደረሰም” አላት። 5 እናቱም ለአሳላፊዎቹ፥ “የሚላችሁን ሁሉ አድርጉ” አለቻቸው። ስለ መጀመሪያው ተአምር 6 በዚያም እንደ አይሁድ ልማድ የሚያነጹባቸው ስድስት የድንጋይ ጋኖች ነበሩ፤ ከእነርሱም እያንዳንዱ ሁለት ወይም ሦስት እንስራ ይይዙ ነበር። 7 ጌታችን ኢየሱስም፥ “ጋኖቹን ውኃ ሙሉአቸው” አላቸው፤ እስከ አፋቸውም እስከ ላይ ሞሉአቸው። 8 “አሁንም ቅዱና ወስዳችሁ ለአሳዳሪው ስጡት” አላቸው፤ ወስደውም ሰጡት። 9 አሳዳሪውም ያን የወይን ጠጅ የሆነውን ውኃ ቀምሶ አደነቀ፤ ከወዴት እንደ መጣም አላወቀም፤ የቀዱት አሳላፊዎች ግን የወይን ጠጅ የሆነውን ያን ውኃ ያውቁ ነበር። ውኃዉን የሞሉ እነርሱ ነበሩና። 10 አሳዳሪውም ሙሽራውን ጠርቶ፥ “ሰው ሁሉ መልካሙን የወይን ጠጅ አስቀድሞ ያጠጣል፤ ከጠገቡ በኋላም ተርታውን ያመጣል፤ አንተ ግን መልካሙን የወይን ጠጅ እስካሁን አቈየህ” አለው። 11 ጌታችን ኢየሱስም በቃና ዘገሊላ ያደረገው የተአምራት መጀመሪያ ይህ ነው፤ ክብሩንም ገለጠ፤ ደቀ መዛሙርቱም አመኑበት። ወደ ኢየሩሳሌም ስለ መውጣቱ 12 ከዚህም በኋላ እርሱና እናቱ፥ ወንድሞቹና ደቀ መዛሙርቱም ወደ ቅፍርናሆም ወረዱ፤ በዚያም ብዙ ያይደለ ጥቂት ቀን ተቀመጡ። 13 የአይሁድም የፋሲካቸው በዓል ቀርቦ ነበር፤ ጌታችን ኢየሱስም ወደ ኢየሩሳሌም ወጣ። 14 በቤተ መቅደስም በሬዎችንና በጎችን፥ ርግቦችንም የሚሸጡትን፥ ገንዘብ ለዋጮችንም ተቀምጠው አገኘ። 15 የገመድም ጅራፍ አበጀ፤ በጎችንና በሬዎችን፥ ሁሉንም ከቤተ መቅደስ አስወጣ፤ የለዋጮችንም ገንዘብ በተነ፤ ገበታዎቻቸውንም ገለበጠ። 16 ርግብ ሻጮችንም፥ “ይህን ከዚህ አውጡ፤ የአባቴን ቤት የንግድ ቤት አታድርጉ” አላቸው። 17 ደቀ መዛሙርቱም፥ “የቤትህ ቅናት በላኝ” የሚል ቃል ተጽፎ እንዳለ ዐሰቡ። ስለ መሞቱና ስለ መነሣቱ 18 አይሁድም መልሰው፥ “ይህን የምታደርግ ምን ምልክት ታሳያለህ?” አሉት። 19 ጌታችን ኢየሱስም፥ “ይህን ቤተ መቅደስ አፍርሱት፤ በሦስተኛውም ቀን አነሣዋለሁ” ብሎ መለሰላቸው። 20 አይሁድም፥ “ይህ ቤተ መቅደስ በአርባ ስድስት ዓመት ተሠራ፤ አንተስ በሦስት ቀኖች ውስጥ ታነሣዋለህን?” አሉት። 21 እርሱ ግን ይህን የተናገረው ቤተ መቅደስ ስለ ተባለ ሰውነቱ ነበር። 22 ከሙታን በተነሣ ጊዜም ደቀ መዛሙርቱ ስለዚህ እንደ ነገራቸው ዐሰቡ፤ በመጻሕፍት ቃልና ጌታችን ኢየሱስ በነገራቸውም ነገር አመኑ። በበዓሉ ውስጥ ብዙዎቹ ስለ ማመናቸው 23 ጌታችን ኢየሱስም በፋሲካ በዓል በኢየሩሳሌም ሳለ ብዙ ሰዎች ያደረገውን ተአምራት ባዩ ጊዜ በስሙ አመኑ። 24 እርሱ ጌታችን ኢየሱስ ግን አያምናቸውም ነበር፤ ሁሉን እያንዳንዱን ያውቀዋልና። 25 የሰውንም ግብሩን ሊነግሩት አይሻም፤ እርሱ በሰው ያለውን ያውቅ ነበርና። |