ኤርምያስ 9 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)1 ስለ ተገደሉ ስለ ሕዝቤ ሴት ልጅ ሰዎች ሌሊትና ቀን አለቅስ ዘንድ ለራሴ ውኃን፥ ለዐይኔም የዕንባን ምንጭ ማን በሰጠኝ? 2 ሁሉም አመንዝሮች፥ የዐመጸኞች ጉባኤ ናቸውና ሕዝቤን እተዋቸው ዘንድ ከእነርሱም እለይ ዘንድ በምድረ በዳ ማደሪያን ማን በሰጠኝ? 3 “ምላሳቸውን ለሐሰት እንደ ቀስት ገተሩ፤ በምድርም በረቱ፤ ነገር ግን ለእውነት አይደለም፤ ከክፋት ወደ ክፋት ይሄዳሉና፥ እኔንም አላወቁምና፥” ይላል እግዚአብሔር። 4 ወንድምም ሁሉ ያሰናክላልና፥ ባልንጀራም ሁሉ በጠማማነት ይሄዳልና እናንተ ሁሉ ከባልንጀሮቻችሁ ተጠንቀቁ፤ በወንድሞቻችሁም አትታመኑ። 5 እያንዳንዱ በባልንጀራው ላይ ይሣለቃል በእውነትም አይናገርም፤ ሐሰት መናገርንም ምላሳቸው ተምሮአል፤ በደሉ መመለስንም እንቢ አሉ። 6 አራጣንም በአራጣ ላይ ይቀበላሉ፤ ተንኰልን በተንኰል ላይ ይሠራሉ፤ “እኔንም ያውቁኝ ዘንድ እንቢ ብለዋል፥” ይላል እግዚአብሔር። 7 ስለዚህ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነሆ፥ አቀልጣቸዋለሁ፤ እፈትናቸውማለሁ፤ ስለ ሕዝቤ ሴት ልጅ ክፋት እንደዚሁ አደርጋለሁና። 8 ምላሳቸው የተሳለ ፍላጻ ነው፤ ንግግራቸው ሽንገላ ነው፤ ለባልንጀራቸው ሰላምን ይናገራሉ፤ በልባቸው ግን ጥላቻን ይይዛሉ። 9 በውኑ ስለዚህ ነገር በመቅሠፍት አልጐበኝምን? ይላል እግዚአብሔር፤ ነፍሴስ እንደዚህ ባለ ሕዝብ ላይ አትበቀልምን? 10 በተራሮቹ ላይ አልቅሱ፤ በምድረ በዳም ጎዳና ላይ እዘኑ፤ ሰው ጠፍትዋልና፤ የሚመላለስም የለምና ሙሾውንም አሙሹ፤ የሰማይ ወፍ ድምፅንም እስከ ከብት ድምፅ ድረስ አይሰሙም፤ ደንግጠውም ተማርከው ሄዱ። 11 ኢየሩሳሌምንም የፍርስራሽ ክምር፥ የቀበሮም ማደሪያ አደርጋታለሁ፤ የይሁዳንም ከተሞች ሰው እንዳይቀመጥባቸው አጠፋቸዋለሁ። 12 ይህን የሚያስተውል ጠቢብ ሰው ማን ነው? ያወራስ ዘንድ የእግዚአብሔር አፍ ለማን ተናገረ? ሰው እንዳያልፍባት ምድርስ ስለ ምን ጠፋች፤ እንደ ምድረ በዳስ ስለ ምን ተቃጠለች? 13 እግዚአብሔርም እንዲህ አለኝ፦ ሕዝቤ በፊታቸው የሰጠኋቸውን ሕጌን ትተዋል፤ ቃሌንም አልሰሙም። 14 ነገር ግን የልባቸውን ምኞትና አባቶቻቸው ያስተማሩአቸውን ጣዖት ተከትለዋል፤ 15 ስለዚህ የእስራኤል አምላክ፥ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነሆ ይህን ሕዝብ መከራን አበላዋለሁ፤ የሐሞትንም ውኃ አጠጣዋለሁ። 16 እነርሱና አባቶቻቸውም በአላወቋቸው አሕዛብ መካከል እበትናቸዋለሁ፤ እስከ አጠፋቸውም ድረስ በስተ ኋላቸው ሰይፍን እሰድድባቸዋለሁ። 17 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እንዲመጡ አልቃሾች ሴቶችን ጥሩ፤ ወደ ብልሃተኞች ሴቶችም ላኩ፤ መጥተውም ይንገሩአችሁ፤ 18 ፈጥነውም ሙሾ ያሙሹላችሁ፤ ዐይኖቻችሁም እንባን ያፍስሱ፤ ከዐይኖቻችሁም ሽፋሽፍቶች ውኃ ይፍለቅ። 19 ምድርን ትተናልና፥ ቤቶቻችንንም ጥለን ሄደናልና እንዴት ጐሰቈልን! እንዴት አፈርን! የሚል የልቅሶ ድምፅ በጽዮን ተሰምቶአል። 20 እናንተ ሴቶች ሆይ! የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ፤ ጆሮአችሁም የአፉን ቃል ትቀበል፤ ለሴቶች ልጆቻችሁም ልቅሶውን፥ እያንዳንድዋም ለባልንጀራዋ ዋይታን ታስተምር። 21 ሕፃናቱንም በመንገድ፤ ጐልማሶቹንም በአደባባዮቻችን ያጠፋ ዘንድ ሞት በመስኮቶቻችን ወደ ሀገራችን ገብቶአልና። 22 የሰዎቻችሁም ሬሳ እንደ ጕድፍ በእርሻ ላይ፥ ማንም እንደማይሰበስበው ከአጫጆች በኋላ እንደሚቀር ቃርሚያ ይወድቃል። 23 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ “ጠቢብ በጥበቡ አይመካ፤ ኀያልም በኀይሉ አይመካ፤ ባለጠጋም በብልጥግናው አይመካ፤ 24 ነገር ግን የሚመካው፦ ምሕረትንና ፍርድን፥ ጽድቅንም በምድር ላይ የማደርግ እኔ እግዚአብሔር መሆኔን በማወቁና በማስተዋሉ በዚህ ይመካ፤ ደስ የሚያሰኘኝ ይህ ነውና፥” ይላል እግዚአብሔር። 25 “እነሆ ዘመን ይመጣል፥ ይላል እግዚአብሔር። የተገረዙትንና ያልተገረዙትን ሁሉ በአንድነት እጐበኛለሁ። 26 አሕዛብ ሁሉ ያልተገረዙ ናቸውና፥ የእስራኤልም ቤት ሁሉ ልባቸው ያልተገረዘ ነውና የተገረዙትን ሁሉ፥ ግብጽንና ይሁዳን፥ ኤዶምያስንም፥ የአሞንንም ልጆች፥ ሞዓብንም፥ በምድረ በዳም የተቀመጡትን ጠጕራቸውን በዙሪያ የተላጩትንም ሁሉ የምጐበኝበት ዘመን እነሆ ይመጣል።” |