ኤርምያስ 45 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)እግዚአብሔር ለባሮክ የነገረው ተስፋ 1 በይሁዳ ንጉሥ በኢዮስያስ ልጅ በኢዮአቄም በአራተኛው ዓመተ መንግሥት እነዚህን ቃላት ከኤርምያስ አፍ በመጽሐፍ በጻፋቸው ጊዜ፥ ነቢዩ ኤርምያስ ለኔርዩ ልጅ ለባሮክ የተናገረው ቃል ይህ ነው። 2 “ባሮክ ሆይ! የእስራኤል አምላክ እግዚእብሔር እንዲህ ይልሃል፦ 3 አንተ፦ እግዚአብሔር በሕማሜ ላይ ኀዘንን ጨምሮብኛልና ወዮልኝ! በልቅሶዬ ጩኸት ደክሜአለሁ፤ ዕረፍትንም አላገኘሁም ብለሃል። 4 እንዲህ በለው፦ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነሆ የሠራሁትን አፈርሳለሁ፥ የተከልሁትንም እነቅላለሁ፤ ይኸውም በምድር ሁሉ ነው። 5 ለራስህ ታላላቅ ነገሮችን ትፈልጋለህን? በሥጋ ለባሽ ሁሉ ላይ እነሆ ክፉ ነገርን አመጣለሁና አትፈልጋቸው፥ ይላል እግዚአብሔር፤ ነገር ግን በሄድህበት ስፍራ ሁሉ ነፍስህን እንደ ምርኮ አድርጌ እሰጥሃለሁ።” |