ኤርምያስ 41 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)1 እንዲህም ሆነ፤ በሰባተኛው ወር ከመንግሥት ወገንና ከንጉሡ ዋና ዋና አለቆች አንዱ የኤሊሳማ ልጅ የናታንያ ልጅ እስማኤል ከዐሥር ሰዎች ጋር ወደ መሴፋ ወደ አኪቃም ልጅ ወደ ጎዶልያስ መጣ፤ በዚያም በመሴፋ በአንድ ላይ እንጀራ በሉ። 2 የናታንያም ልጅ እስማኤል ከእርሱም ጋር የነበሩት ዐሥሩ ሰዎች ተነሥተው የሳፋንን ልጅ የአኪቃምን ልጅ ጎዶልያስን በሰይፍ መቱ፤ የባቢሎንም ንጉሥ በሀገሩ ላይ የሾመውን ገደሉ። 3 እስማኤልም ከጎዶልያስ ጋር በመሴፋ የነበሩትን አይሁድ ሁሉ፥ በዚያም የተገኙትን ከለዳውያንን ሁሉ፤ ሰልፈኞች ሰዎችንም ሁሉ ገደላቸው። 4 እስማኤል ማንም ሳያውቅ ጎዶልያስን ከገደለ በኋላ በሁለተኛው ቀን እንዲህ ሆነ፤ 5 ጢማቸውን ላጭተው፥ ልብሳቸውንም ቀድደው እያለቀሱ ወደ እግዚአብሔር ቤት ያቀርቡ ዘንድ የእህል ቍርባንና ዕጣን በእጃቸው የያዙ፥ ሰማንያ ሰዎች ከሴኬምና ከሴሎ፥ ከሰማርያም መጡ። 6 የናታንያም ልጅ እስማኤል ከመሴፋ ወጥቶ እያለቀሰ ሊገናኛቸው ሄደ፤ በተገናኛቸውም ጊዜ፥ “ወደ አኪቃም ልጅ ወደ ጎዶልያስ ኑ” አላቸው። 7 ወደ ከተማም መካከል በመጡ ጊዜ የናታንያ ልጅ እስማኤል፥ ከእርሱም ጋር የነበሩ ሰዎች ገደሉአቸው፤ በጕድጓድም መካከል ጣሉአቸው። 8 በዚያም የተገኙ ዐሥር ሰዎች ቀርበው እስማኤልን እንዲህ አሉት፥ “በሜዳው ድልብ አለንና፥ ገብስና ስንዴ፥ ዘይትና ማርም አለንና አትግደለን፤” እርሱም በወንድሞቻቸው መካከል እነርሱን መግደል ተወ። 9 እስማኤልም ከጎዶልያስ ጋር የገደላቸውን ሰዎች ሬሳ ሁሉ የጣለበት ጕድጓድ ንጉሡ አሳ የእስራኤልን ንጉሥ ባኦስን ስለ ፈራ የሠራው ጕድጓድ ነበረ፤ የናታንያም ልጅ እስማኤል የገደላቸውን ሞላበት። 10 እስማኤልም በመሴፋ የነበረውን የሕዝቡን ቅሬታ ሁሉ፥ የንጉሡን ሴቶች ልጆች፥ የአዛዦች አለቃ ናቡዛርዳን ለአኪቃም ልጅ ለጎዶልያስ የሰጠውን በመሴፋ የቀሩትን ሕዝብ ሁሉ መለሰ፤ የናታንያም ልጅ እስማኤል ወደ አሞን ልጆች ይሄድ ዘንድ ተነሣ። 11 የቃርሔም ልጅ ዮሐናን፥ ከእርሱም ጋር የነበሩ የጭፍራ አለቆች ሁሉ የናታንያ ልጅ እስማኤል ያደረገውን ክፋት ሁሉ ሰሙ። 12 ሠራዊቱንም ሁሉ ይዘው ከናታንያ ልጅ ከእስማኤል ጋር ሊዋጉ ሄዱ። በገባዖንም ባለው በብዙ ውኃ አጠገብ አገኙት። 13 እንዲህም ሆነ፤ ከእስማኤል ጋር የነበሩት ሕዝብ ሁሉ የቃርሔን ልጅ ዮሐናንን ከእርሱም ጋር የነበሩትን የጭፍራ አለቆችን ሁሉ ባዩ ጊዜ ደስ አላቸው። 14 እስማኤልም ከመሴፋ የማረካቸው ሕዝብ ሁሉ ተመልሰው ወደ ቃርሔም ልጅ ወደ ዮሐናን ሔዱ። 15 የናታንያ ልጅ እስማኤል ግን ከስምንት ሰዎች ጋር ከዮሐናን አመለጠ፥ ወደ አሞንም ልጆች ሄደ። 16 የቃርሔም ልጅ ዮሐናን፥ ከእርሱም ጋር የነበሩት የጭፍራ አለቆች ሁሉ የአኪቃምን ልጅ ጎዶልያስን በመሴፋ ከገደለው በኋላ ከናታንያ ልጅ ከእስማኤል ያስመለሱአቸውን የሕዝቡን ቅሬታ ሁሉ፥ ከገባዖን ያስመለሱአቸውን ኀያላን ሰልፈኞችን፥ ሴቶችንም፥ ልጆችንም፥ ጃንደረቦችንም ወሰዱ፤ 17 ተነሥተውም ወደ ግብፅ ይሄዱ ዘንድ በቤተልሔም አጠገብ በአለው በጌሮት-ከመዓም ተቀመጡ፤ 18 እስማኤል የባቢሎን ንጉሥ በሀገሩ ላይ የሾመውን የአኪቃምን ልጅ ጎዶልያስን ስለ ገደለው ከለዳውያንን ፈርተዋልና። |