ኤርምያስ 39 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)የኢየሩሳሌም አወዳደቅ 1 እንዲህም ሆነ፤ በይሁዳ ንጉሥ በሴዴቅያስ በዘጠነኛው ዓመተ መንግሥት በዐሥረኛው ወር የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆርና ሠራዊቱ ሁሉ ወደ ኢየሩሳሌም መጥተው ከበቡአት። 2 በሴዴቅያስም በዐሥራ አንደኛው ዓመተ መንግሥት በአራተኛው ወር፥ ከወሩም በዘጠነኛው ቀን ከተማዪቱ ተለያየች። 3 የባቢሎንም ንጉሥ አለቆች ሁሉ፥ ማርጋናሳር፥ ሳማጎት፥ ናቡሳኮር፥ ናቡሰሪስ፥ ናግራጎስናሴር፥ ረብማግ፥ ኔርጋል ሴሪአጼር፥ ከቀሩት ከባቢሎን ንጉሥ አለቆች ሁሉ ጋር ገብተው በመካከለኛው በር ውስጥ ተቀመጡ። 4 የይሁዳ ንጉሥ ሴዴቅያስና ሰልፈኞቹም ሁሉ በአዩአቸው ጊዜ፥ በሌሊት ሸሹ፤ በንጉሡም አትክልት መንገድ በሁለቱ ቅጥር መካከል በነበረው ደጅ ከከተማዪቱ ወጡ፤ በዓረባም መንገድ ወጡ። 5 የከለዳውያንም ሠራዊት ተከታተላቸው፤ ሴዴቅያስንም በኢያሪኮ ሜዳ አገኙት፤ ይዘውም በሐማት ምድር ወዳለችው ወደ ዴብላታ ወደ ባቢሎን ንጉሥ ወደ ናቡከደነፆር አመጡት፤ እርሱም ፍርድን በእርሱ ላይ ተናገረ። 6 የባቢሎንም ንጉሥ የሴዴቅያስን ልጆች በዐይኑ ፊት በዴብላታ ገደላቸው፤ የባቢሎንም ንጉሥ የይሁዳን ታላላቆች ሁሉ ገደለ። 7 የሴዴቅያስንም ዐይን አወጣ፤ በሰንሰለትም አስሮ ወደ ባቢሎን ወሰደው። 8 ከለዳውያንም የንጉሡንና የሕዝቡን ቤቶች በእሳት አቃጠሉ፤ የኢየሩሳሌምንም ቅጥር አፈረሱ። 9 የአዛዦች አለቃ ናቡዛርዳንም በከተማዪቱ የቀሩትን ሕዝብ፥ ኰብልለውም ወደ እርሱ የገቡትን ሰዎችና የቀረውንም የሕዝቡን ቅሬታ ወደ ባቢሎን ማረካቸው። 10 የአዛዦች አለቃ ናቡዛርዳን ግን አንዳች ከሌላቸው ከሕዝቡ ድሆች ከፊሎቹን በይሁዳ ሀገር ተዋቸው፤ የወይኑን ቦታና እርሻውንም በዚያ ጊዜ ሰጣቸው። ኤርምያስ እንደ ተፈታ 11 የባቢሎንም ንጉሥ ናቡከደነፆር የአዛዦች አለቃ ናቡዛርዳንን ስለ ኤርምያስ እንዲህ ሲል አዘዘው፦ 12 “ውሰደውና በመልካም ተመልከተው፤ የሚልህንም ነገር አድርግለት እንጂ ክፉን ነገር አታድርግበት።” 13 የአዛዞች አለቃ ናቡዛርዳንም ላከ፤ ናቡሻዝባንም፥ ራፋስቂስም፥ ኔርጋል ሴራአጼርም፥ ራብማግም፥ የባቢሎንም ንጉሥ አለቆች ሁሉ ላኩ። 14 ኤርምያስንም ከግዞት ቤቱ አደባባይ አወጡት፤ ወደ ቤቱም ይወስደው ዘንድ ለሳፋን ልጅ ለአኪቃም ልጅ ለጎዶልያስ ሰጡት፤ እንዲህም በሕዝብ መካከል ተቀመጠ። ለአቤሜሌክ የተሰጠ ተስፋ 15 በግዞት ቤቱ አደባባይም ታስሮ ሳለ የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል ወደ ኤርምያስ መጣ፦ 16 “ሂድ ለኢትዮጵያዊው ለአቤሜሌክ እንዲህ በለው፦ የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነሆ ለበጎነት ሳይሆን ለክፋት ቃሌን በዚች ከተማ ላይ አመጣለሁ፤ በዚያም ቀን በፊትህ ይፈጸማል። 17 በዚያም ቀን አድንሃለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር፤ ከፊታቸውም የተነሣ በምትፈራቸው ሰዎች እጅ አልሰጥህም። 18 ፈጽሜ አድንሃለሁ፤ ሰውነትህም እንደ ምርኮ ትሆንልሃለች እንጂ በሰይፍ አትወድቅም፤ በእኔ ታምነሃልና፥” ይላል እግዚአብሔር። |