ዘፍጥረት 7 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ማየ አይኅ 1 እግዚአብሔር አምላክም ኖኅን አለው፥ “አንተ ቤተሰቦችህን ሁሉ ይዘህ ወደ መርከብ ግባ፤ በዚህ ትውልድ በፊቴ ጻድቅ ሆነህ አይችሃለሁና። 2 ከንጹሕ እንስሳ ሁሉ ሰባት ስባት ተባትና እንስት፥ ንጹሕ ካልሆነም እንስሳ ሁለት ሁለት ተባትና እንስት፤ 3 ከንጹሕ የሰማይ ወፍ ደግሞ ሰባት ሰባት ተባትና እንስት፥ ንጹሕ ካልሆነ የሰማይ ወፍም ሁለት ሁለት ተባትና እንስት እያደረግህ በምድር ላይ ለምግብና ለዘር ይቀር ዘንድ ለአንተ ትወስዳለህ። 4 ከሰባት ቀን በኋላ አርባ ቀንና አርባ ሌሊት በምድር ላይ ዝናብ አዘንባለሁና፤ የፈጠርሁትንም ፍጥረት ሁሉ ከምድር ሁሉ ላይ አጠፋለሁና።” 5 ኖኅም እግዚአብሔር አምላክ ያዘዘውን ሁሉ አደረገ። 6 ኖኅም የጥፋት ውኃ በምድር ላይ በሆነ ጊዜ የስድስት መቶ ዓመት ዕድሜ ነበረ። 7 ኖኅም ስለ ጥፋት ውኃ ልጆቹንና ሚስቱን፥ የልጆቹንም ሚስቶች ይዞ ወደ መርከብ ገባ። 8 ከንጹሓን ወፎችና ንጹሓን ካልሆኑ ወፎች፥ ከንጹሕ እንስሳ፥ ንጹሕም ካልሆነው እንስሳ፥ በምድር ላይ ከሚንቀሳቀሰው ሁሉ፥ 9 እግዚአብሔር ኖኅን እንዳዘዘው፥ ሁለት ሁለት ተባትና እንስት እየሆኑ ወደ ኖኅ ወደ መርከብ ውስጥ ገቡ። 10 ከሰባት ቀን በኋላም የጥፋት ውኃ በምድር ላይ ሆነ። 11 በኖኅ ዕድሜ በስድስተኛው መቶ ዓመት በሁለተኛው ወር ከወሩም በዐሥራ ሰባተኛው ዕለት፥ በዚያው ቀን የታላቁ ቀላይ ምንጮች ሁሉ ተነደሉ፤ የሰማይ መስኮቶችም ተከፈቱ፤ 12 ዝናቡም አርባ ቀንና አርባ ሌሊት በምድር ላይ ሆነ። 13 በዚያውም ቀን ኖኅ ወደ መርከብ ገባ፤ የኖኅ ልጆችም ሴም፥ ካም፥ ያፌትና የኖኅ ሚስት፥ ሦስቱም የልጆቹ ሚስቶች ከእርሱ ጋር ገቡ። 14 አራዊትም ሁሉ በየወገናቸው፥ እንስሳትም ሁሉ በየወገናቸው፥ በምድር ላይ የሚንቀሳቀሱ ተንቀሳቃሾችም ሁሉ በየወገናቸው፥ ወፎችም ሁሉ በየወገናቸው፥ የሚበሩ ወፎችም ሁሉ፥ 15 ሥጋ ያላቸው ሕያዋን ሁሉ ሁለት ሁለት እየሆኑ ወደ ኖኅ መርከብ ውስጥ ገቡ። 16 ሥጋ ካለው ሁሉ የገቡትም ተባትና እንስት እግዚአብሔር ኖኅን እንዳዘዘው ገቡ፤ እግዚአብሔር አምላክም መርከብዋን በስተውጭ ዘጋት። 17 የጥፋት ውኃ በምድር ላይ አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ነበረ፤ ውኃውም በዛ፤ መርከቢቱንም አነሣ፤ ከምድርም ወደ ላይ ከፍ ከፍ አለች። 18 ውኃውም አሸነፈ፤ በምድር ላይም እጅግ በዛ፤ መርከቢቱም በውኃ ላይ ተንሳፈፈች። 19 ውኃውም በምድር ላይ እጅግ በጣም አሸነፈ፤ ከሰማይ በታች ያሉ ረዣዥም ተራሮችን ሁሉ ሸፈነ። 20 ውኃው ወደ ላይ ዐሥራ አምስት ክንድ ከፍ ከፍ አለ፤ ረዣዥም ተራሮችንም ሸፈነ። 21 በምድር ላይ ሥጋ ያለው የሚንቀሳቀሰው ሁሉ ወፉም፥ እንስሳውም፥ አራዊቱም፥ በምድር ላይ የሚርመሰመሰው ተንቀሳቃሹምሁሉ፥ ሰውም ሁሉ ጠፋ። 22 የሕይወት እስትንፋስ ያለው ሁሉ፥ በየብስም ያለው ሁሉ ሞተ። 23 በምድር ላይ የነበረውም ሁሉ ከሰው ጀምሮ እስከ እንስሳ፥ እስከሚርመሰመሰውም ሁሉ ድረስ፥ እስከ ሰማይ ወፍም ድረስ ተደመሰሰ፤ ከምድርም ተደመሰሱ። ኖኅም አብረውት በመርከብ ከነበሩት ጋር ብቻውን ቀረ። 24 ውኃውም መቶ አምሳ ቀን በምድር ላይ ሞላ። |