ዘፍጥረት 50 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)1 ዮሴፍም በአባቱ ፊት ወደቀ፤ በእርሱም ላይ አለቀሰ፤ ሳመውም። 2 ዮሴፍም ባለ መድኀኒቶች አገልጋዮቹ አባቱን በሽቱ ያሹት ዘንድ አዘዘ፤ ባለ መድኀኒቶችም እስራኤልን በሽቱ አሹት። 3 አርባ ቀንም ፈጸሙለት፤ ሽቱ የሚቀቡበትን ቀን እንዲሁ ይቈጥራሉና፤ የግብፅም ሰዎች ሰባ ቀን አለቀሱለት። 4 የልቅሶውም ወራት ከተፈጸመ በኋላ ዮሴፍ ለፈርዖን መኳንንት እንዲህ ብሎ ተናገረ፥ “እኔ በፊታችሁ ሞገስን አግኝቼ እንደ ሆንሁ ለፈርዖን እንዲህ ብላችሁ ስለ እኔ ንገሩት፦ 5 አባቴ ሳይሞት አምሎኛል፤ እንዲህ ሲል፦ ‘እነሆ እኔ እሞታለሁ፤ በቈፈርሁት መቃብር በከነዓን ምድር በዚያ ቅበረኝ።’ አሁንም ወጥቼ አባቴን ልቅበርና ልመለስ።” 6 ፈርዖንም ዮሴፍን አለው፥ “ውጣ፤ አባትህንም እንዳማለህ ቅበረው።” 7 ዮሴፍም አባቱን ሊቀብር ወጣ፤ የፈርዖን ሎሌዎችም ሁሉ፥ የቤቱ ሽማግሌዎችም ሁሉ፥ የግብፅ ምድር ሽማግሌዎችም ሁሉ ከእርሱ ጋር ወጡ፤ 8 የዮሴፍም ቤተ ሰቦች ሁሉ፥ ወንድሞቹም፥ የአባቱም ቤተ ሰቦች ወጡ፤ ልጆቻቸውንና በጎቻቸውን፥ ከብቶቻቸውንም ብቻ በጌሤም ተዉ። 9 ሰረገሎችም፥ ፈረሰኞችም ከእርሱ ጋር ወጡ፤ ሠራዊቱም ብዙ ነበር። 10 በዮርዳኖስ ማዶ ወዳለችው ወደ አጣድ አውድማ ደረሱ፤ እጅግ ታላቅ በሆነ በጽኑ ልቅሶም አለቀሱለት፤ ለአባቱም ሰባት ቀን ልቅሶ አደረገለት። 11 በዚያች ምድር የሚኖሩ የከነዓን ሰዎችም በአጣድ አውድማ የሆነውን ልቅሶ በአዩ ጊዜ፥ “የግብፅ ልቅሶ እንዲህ ታላቅ ነውን?” አሉ፤ ስለዚህም የዚያን ቦታ ስም “ላሐ ግብፅ” ብለው ጠሩት፤ እርሱም በዮርዳኖስ ማዶ ነው። 12 ልጆቹም እንዳዘዛቸው እንደዚያው አደረጉለት፤ 13 ልጆቹም ወደ ከነዓን ምድር መለሱት፤ ባለ ሁለት ክፍል በሆነች ዋሻም ቀበሩት፤ እርስዋም በመምሬ ፊት ያለች፥ አብርሃም ለመቃብር ርስት ከኬጢያዊው ከኤፍሮን ከእርሻው ጋር የገዛት ዋሻ ናት። 14 ዮሴፍና ወንድሞቹ፥ አባቱንም ሊቀብሩ ከእርሱ ጋር የወጡት ሰዎች ሁሉ አባቱን ከቀበረ በኋላ ወደ ግብፅ ተመለሱ። ዮሴፍ ወንድሞቹን ማረጋጋቱ 15 የዮሴፍም ወንድሞች አባታቸው እንደ ሞተ በአዩ ጊዜ እንዲህ አሉ፥ “ምናልባት ዮሴፍ ያደረግንበትን ክፋት ያስብብን ይሆናል፤ ባደረግንበትም ክፋት ሁሉ ብድራት ይመልስብን ይሆናል።” 16 ወደ ዮሴፍም መጡ፤ እንዲህም አሉት፥ “አባትህ ገና ሳይሞት እንዲህ ብሎ አዝዟል፦ 17 ‘ዮሴፍን እንዲህ በሉት፦ እባክህ የወንድሞችህን በደል ኀጢአታቸውንም ይቅር በል፤ እነርሱ በአንተ ክፉ አድርገውብሃልና፤’ አሁንም እባክህ የአባትህ አምላክ ባሪያዎች የበደሉህን ይቅር በል።” 18 ዮሴፍም ይህን ሲሉት አለቀሰ። ወንድሞቹ ደግሞ መጡ፤ “እነሆ፥ እኛ ለአንተ አገልጋዮችህ ነን” አሉት። 19 ዮሴፍም አላቸው፥ “አትፍሩ፤ ይህ ከእግዚአብሔር ዘንድ ሆኖአልና። 20 እናንተ በእኔ ላይ ክፉ መከራችሁ፤ እግዚአብሔር ግን ዛሬ እንደ ሆነው ብዙ ሕዝብ እንዲመገብ ለማድረግ ለእኔ መልካም መከረ። 21 አሁንም አትፍሩ፤ እኔ እናንተንና ቤተ ሰቦቻችሁን እመግባችኋለሁ።” አጽናናቸውም፤ በልባቸው የሚገባ ነገርም ነገራቸው። የዮሴፍ ሞት 22 ዮሴፍም በግብፅ ሀገር ተቀመጠ፤ እርሱና ወንድሞቹ የአባቱም ቤተ ሰብ፤ ዮሴፍም መቶ ዐሥር ዓመት ኖረ። 23 ዮሴፍም የኤፍሬምን ልጆች እስከ ሦስት ትውልድ አየ። የምናሴ ልጅ የማኪር ልጆችም በዮሴፍ ጭን ላይ ተወለዱ። 24 ዮሴፍም ወንድሞቹን አላቸው፥ “እኔ እሞታለሁ፤ እግዚአብሔርም መጐብኘትን ይጐበኛችኋል፤ ከዚህችም ምድር ያወጣችኋል። ለአባቶቻችን ለአብርሃምና ለይስሐቅ ለያዕቆብም ወደ ማለላቸው ምድር ያገባችኋል።” 25 ዮሴፍም የእስራኤልን ልጆች፥ “እግዚአብሔር በጐበኛችሁ ጊዜ አጥንቴን ከዚህ አንሥታችሁ ከእናንተ ጋር አውጡ” ብሎ አማላቸው። 26 ዮሴፍም በመቶ ዐሥር ዓመት ዕድሜው ሞተ፤ በሽቱም አሹት፤ በግብፅ ምድርም በሣጥን ውስጥ አኖሩት። |