ዘፍጥረት 47 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ዮሴፍ የዘመዶቹን መምጣት ለፈርዖን መናገሩ 1 ዮሴፍም ገባ፤ ለፈርዖንም እንዲህ ብሎ ነገረው፥ “አባቴና ወንድሞች በጎቻቸውም፥ ላሞቻቸውም፥ ያላቸውም ሁሉ ከከነዓን ምድር መጡ፤ እነርሱም እነሆ፥ ወደ ጌሤም ምድር ደረሱ።” 2 ከወንድሞቹም አምስት ሰዎችን ወስዶ በፈርዖን ፊት አቆማቸው። 3 ፈርዖንም የዮሴፍን ወንድሞች፥ “ሥራችሁ ምንድን ነው?” አላቸው። እነርሱም ፈርዖንን፥ “እኛ አገልጋዮችህ፥ አባታችንም ከብት ጠባቂዎች ነን” አሉት። 4 ፈርዖንንም እንዲህ አሉት፥ “በምድር ልንቀመጥ በእንግድነት መጣን፤ የአገልጋዮችህ በጎች የሚሰማሩበት ስፍራ የለምና፤ ራብም በከነዓን ምድር እጅግ ጸንቶአልና፤ አሁንም አገልጋዮችህ በጌሤም ምድር እንቀመጥ።” 5 ፈርዖንም ዮሴፍን እንዲህ ብሎ ተናገረው፥ “አባትህና ወንድሞችህ መጥተውልሃል፤ እነሆ፥ የግብፅ ምድር በፊትህ ናት፤ 6 በመልካሙ ምድር አባትህንና ወንድሞችህን አኑራቸው፤ ከእነርሱም ውስጥ ዕውቀት ያላቸውን ሰዎች ታውቅ እንደሆነ በእንስሶች ጠባቂዎች ላይ አለቆች አድርጋቸው።” 7 ዮሴፍም ያዕቆብን አባቱን አስገብቶ በፈርዖን ፊት አቆመው፤ ያዕቆብም ፈርዖንን ባረከው። 8 ፈርዖንም ያዕቆብን፥ “የኖርኸው ዘመን ስንት ነው?” አለው። 9 ያዕቆብም ለፈርዖን አለው፥ “በእንግድነት የኖርሁት የሕይወቴ ዘመንስ መቶ ሠላሳ ዓመት ነው፤ የሕይወቴም ዘመኖች ጥቂትም ክፉም ሆኑብኝ፤ አባቶች በእንግድነት የተቀመጡበትንም ዘመን አያህሉም።” 10 ያዕቆብም ፈርዖንን ባረከው፤ ከፈርዖንም ፊት ወጣ። 11 ዮሴፍም አባቱንና ወንድሞቹን አኖረ፤ ፈርዖን እንዳዘዘላቸውም በግብፅ ምድር በተሻለችው በራምሴ ምድር ርስትን ሰጣቸው። 12 ዮሴፍም ለአባቱና ለወንድሞቹ፥ ለአባቱም ቤተ ሰዎች ሁሉ ለእያንዳንዱ ሰው እየሰፈረ እህልን ለምግብ ይሰጣቸው ነበር። በግብፅ የራብ መጽናትና የዮሴፍ አመራር 13 በምድርም ሁሉ እህል አልነበረም፤ ራብ እጅግ ጸንቶአልና፤ ከራብም የተነሣ የግብፅ ምድርና የከነዓን ምድር ተጐዳ። 14 ዮሴፍም ከግብፅ ምድርና ከከነዓን ምድር በእህል ሸመታ የተገኘውን ብሩን ሁሉ አከማቸ፤ ዮሴፍም ብሩን ወደ ፈርዖን ቤት አስገባው። 15 ብሩም በግብፅ ምድርና በከነዓን ምድር አለቀ፤ የግብፅ ሰዎችም ሁሉ ወደ ዮሴፍ መጡ፤ እንዲህ ሲሉ፥ “በፊትህ እንዳንሞት እህል ስጠን፤ ብሩ አልቆብናልና።” 16 ዮሴፍም፥ “ከብቶቻችሁን አምጡልኝ፤ ብር ከአለቀባችሁ በከብቶቻችሁ ፈንታ እህል እሰጣችኋለሁ” አለ። 17 ከብቶቻቸውንም ወደ ዮሴፍ አመጡ፤ ዮሴፍም በፈረሶቻቸው፥ በበጎቻቸውም፥ በላሞቻቸውም፥ በአህዮቻቸውም ፈንታ እህልን ሰጣቸው፤ በዚያች ዓመትም ስለ ከብቶቻቸው ሁሉ ፈንታ እህልን መገባቸው። 18 ያችም ዓመት ተፈጸመች፤ በሁለተኛዋም ዓመት ወደ እርሱ መጥተው እንዲህ አሉት፥ “እኛ ለጌታችን ሞተን እንዳናልቅበት እህል ስጠን፤ ብሩ በፍጹም አለቀ፤ ንብረታችንና ከብታችንም በጌታችን ዘንድ ነው፤ ከሰውነታችንና ከምድራችን በቀር በጌታችን ፊት አንዳች የቀረን የለም፤ 19 እንግዲህ እኛ በፊትህ እንዳንሞት፥ ምድራችንም እንዳትጠፋ፥ እኛንም፥ ምድራችንንም በእህል ግዛን፤ እኛም ለፈርዖን አገልጋዮች እንሁን፤ ምድራችንም ለእርሱ ትሁን፤ እኛ እንድንድን፥ እንዳንሞትም፥ ምድራችንም እንዳትጠፋ እንዘራ ዘንድ ዘር ስጠን።” 20 ዮሴፍም የግብፅን ምድር ሁሉ ለፈርዖን ገዛ፤ የግብፅ ሰዎች ሁሉ ራብ ስለጸናባቸው ርስታቸውን ሸጠዋልና፤ ምድሪቱ ለፈርዖን ሆነች። 21 ሕዝቡንም ሁሉ ከግብፅ ዳርቻ አንሥቶ እስከ ሌላው ዳርቻዋ ድረስ አገልጋዮች አደረጋቸው። 22 ዮሴፍ የካህናትን ምድር ብቻ አልገዛም፤ ፈርዖን ለካህናቱ ድርጎ ይሰጣቸው ነበርና፥ ፈርዖንም የሰጣቸውን ድርጎ ይበሉ ነበር፤ ስለዚህም ምድራቸውን አልሸጡም። 23 ዮሴፍም የግብፅን ሰዎች ሁሉ እንዲህ አላቸው፥ “እነሆ ዛሬ እናንተንና ምድራችሁን ለፈርዖን ገዝቻችኋለሁ፤ ለእናንተ ዘር ውሰዱና ምድሪቱን ዝሩ፤ 24 በመከርም ጊዜ ፍሬውን ከአምስት እጅ አንዱን እጅ ለፈርዖን ስጡ፤ አራቱም እጅ ለእናንተ ለራሳችሁ፥ ለእርሻው ዘርና ለእናንተ ምግብ፥ ለቤተ ሰባችሁም ሁሉ ሲሳይ ይሁን።” 25 እነርሱም፥ “አንተ አዳንኸን፤ በጌታችንም ፊት ሞገስን አገኘን፤ ለፈርዖንም አገልጋዮች እንሆናለን” አሉት። 26 ዮሴፍም ለፈርዖን ካልሆነችው ከካህናቱ ምድር በቀር አምስተኛው እጅ ለፈርዖን እንዲሆን በግብፅ ምድር እስከ ዛሬ ሕግ አደረጋት። ያዕቆብ በሀገሩ እንዲቀበር ዮሴፍን መለመኑ 27 እስራኤልም በግብፅ ምድር በጌሤም ሀገር ተቀመጠ፤ እርስዋም ርስታቸው ሆነች፤ በዙ፤ እጅግም ተባዙ። 28 ያዕቆብም በግብፅ ምድር ዐሥራ ሰባት ዓመት ተቀመጠ፤ የያዕቆብም መላው የሕይወቱ ዘመን መቶ አርባ ሰባት ዓመት ሆነ። 29 የእስራኤልም የሞቱ ቀን ቀረበ፤ ልጁን ዮሴፍንም ጠርቶ እንዲህ አለው፥ “በፊትህ ሞገስን አግኝቼ እንደ ሆንሁ እጅህን በጕልበቴ ላይ አድርግ፤ በግብፅ ምድርም እንዳትቀብረኝ ምሕረትንና እውነትን አድርግልኝ፤ 30 ከአባቶችም ጋር በአንቀላፋሁ ጊዜ ከግብፅ ምድር አውጥተህ ትወስደኛለህ፤ በአባቶችም መቃብር ትቀብረኛለህ።” እርሱም፥ “እንደ ቃልህ አደርጋለሁ” አለ። እርሱም፥ “ማልልኝ” አለው። 31 ዮሴፍም ማለለት፤ እስራኤልም በአልጋው ራስ ላይ ሰገደ። |