ዘፍጥረት 45 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ዮሴፍ ራሱን ለወንድሞቹ መግለጡ 1 ዮሴፍም በፊቱ ሰዎች ሁሉ ቆመው ሳሉ ሊታገሥ አልተቻለውም፥ “ሰዎቹንም ሁሉ ከፊቴ አስወጡልኝ” ብሎ ተናገረ፤ ዮሴፍ ለወንድሞቹ ራሱን በገለጠ ጊዜ በእርሱ ዘንድ የቆመ ማንም አልነበረም። 2 ቃሉንም ከፍ አድርጎ አለቀሰ፤ የግብፅ ሰዎችም ሰሙ፤ በፈርዖን ቤትም ተሰማ። 3 ዮሴፍም ለወንድሞቹ፥ “እኔ ወንድማችሁ ዮሴፍ ነኝ፤ አባቴ እስከ አሁን በሕይወቱ ነውን?” አላቸው። ወንድሞቹም ይመልሱለት ዘንድ አልቻሉም፤ ደንግጠው ነበርና። 4 ዮሴፍም ወንድሞቹን፥ “ወደ እኔ ቅረቡ” አላቸው። ወደ እርሱም ቀረቡ። እንዲህም አላቸው፥ “ወደ ግብፅ የሸጣችሁኝ እኔ ወንድማችሁ ዮሴፍ ነኝ። 5 አሁንም ወደዚህ ስለሸጣችሁኝ አትፍሩ፤ አትቈርቈሩም፤ እግዚአብሔር ለሕይወት ከእናንተ በፊት ልኮኛልና። 6 እነሆ፥ ይህ ሁለቱ ዓመት በምድር ላይ ራብ የሆነበት ነውና፤ የማይታረስበትና የማይታጨድበት አምስት ዓመት ገና አለ። 7 እግዚአብሔርም በምድር ላይ እንድትድኑና እንድትተርፉ እመግባችሁ ዘንድ ከእናንተ በፊት ላከኝ። 8 አሁንም እናንተ ወደዚህ የላካችሁኝ አይደላችሁም፤ እግዚአብሔር ላከኝ እንጂ፤ ለፈርዖንም እንደ አባት አደረገኝ፤ በቤቱም ሁሉ ላይ ጌታ፥ በግብፅ ምድርም ሁሉ ላይ አለቃ አደረገኝ። 9 አሁንም ፈጥናችሁ ወደ አባቴ ሂዱ፤ እንዲህም በሉት፦ ልጅህ ዮሴፍ የሚለው ነገር ይህ ነው፦ እግዚአብሔር በግብፅ ምድር ሁሉ ላይ ጌታ አደረገኝ፤ ወደ እኔ ና፤ በዚያም አትዘግይ፤ 10 በዐረብ በኩል በጌሤም ምድርም ትቀመጣለህ፤ ወደ እኔም ትቀርባለህ። አንተና ልጆችህ የልጆችህም ልጆች፥ በጎችህና ላሞችህ፥ የአንተ የሆነው ሁሉ፥ 11 በዚያም አንተና የቤትህ ሰዎች የአንተ የሆነው ሁሉ እንዳትቸገሩ እመግብሃለሁ፤ የራቡ ዘመን ገና አምስት ዓመት ቀርቶአልና፤ 12 እነሆም፥ ለእናንተ እኔ ራሴ በአፌ እንደ ተናገርሁአችሁ እናንተ በዐይኖቻችሁ አይታችኋል፤ ወንድሜ ብንያም በዐዓይኖቹ አይቶአል። 13 ለአባቴ በግብፅ ምድር ያለኝን ክብሬን ሁሉ፥ በዐይኖቻችሁ ያያችሁትንም ሁሉ ንገሩት፤ አባቴንም ወደዚህ ፈጥናችሁ አምጡት።” 14 የወንድሙን የብንያምንም አንገት አቅፎ አለቀሰ፤ ብንያምም በአንገቱ ላይ አለቀሰ። 15 ወንድሞቹን ሁሉ ሳማቸው፤ በእነርሱም ላይ አለቀሰ፤ ከዚያም በኋላ ወንድሞቹ ከእርሱ ጋር ተጨዋወቱ። 16 በፈርዖንም ቤት፥ “የዮሴፍ ወንድሞች መጡ” ተብሎ ወሬ ተሰማ፤ ፈርዖንና ቤተ ሰቡም ሁሉ ደስ አላቸው። 17 ፈርዖንም ዮሴፍን አለው፥ “ለወንድሞችህ እንዲህ ብለህ ንገራቸው፦ ይህን አድርጉ፤ ዕቃችሁን ጭናችሁ ወደ ከነዓን ምድር ሂዱ፤ 18 አባታችሁንና ንብረታችሁን ሁሉ ይዛችሁ ወደ እኔ ኑ፤ እኔም የግብፅን ምድር በረከት ሁሉ እሰጣችሁአለሁ፤ የምድሪቱንም ድልብ ትበላላችሁ። 19 አንተም ወንድሞችህን፦ እንዲህ አድርጉ በላቸው፤ ከግብፅ ምድር ለሕፃኖቻችሁ፥ ለሴቶቻችሁም ሰረገሎችን ውሰዱ፤ አባታችሁንም ይዛችሁ ኑ፤ 20 ለዕቃችሁም ዐይናችሁ ለአየውም ሁሉ አታስቡ፤ የግብፅ በረከት ሁሉ ለእናንተ ነውና።” 21 የእስራኤል ልጆችም እንደ አዘዛቸው አደረጉ፤ ዮሴፍም የግብፅ ንጉሥ ፈርዖን እንደ ነገረው ሰረገሎችንና ለመንገድ ስንቅን ሰጣቸው፤ 22 ለሁሉም ሁለት ሁለት መለወጫ ልብስ ሰጣቸው፤ ለብንያም ግን ሦስት መቶ ብርና አምስት መለወጫ ልብስ ሰጠው። 23 ለአባቱም እንደዚሁ ላከ፤ ከግብፅ በረከት ሁሉ የተጫኑ ዐሥር አህዮችን፥ ደግሞም በመንገድ ለአባቱ ስንቅ የተጫኑ ዐሥር በቅሎዎችን። 24 ዮሴፍም ወንድሞቹን አሰናበታቸው፤ እንዲህም አላቸው፥ “በመንገድ እርስ በርሳችሁ አትጣሉ።” 25 እነርሱም ከግብፅ ሀገር ወጥተው ሄዱ፤ ወደ ከነዓንም ምድር ወደ አባታቸው ወደ ያዕቆብ ደረሱ። 26 እንዲህም ብለው ነገሩት፥ “ልጅህ ዮሴፍ በሕይወቱ ነው፤ እርሱም በግብፅ ምድር ሁሉ ላይ ገዥ ሆኖአል።” ያዕቆብም ልቡ ደነገጠ፤ አላመናቸውምም፤ 27 እነርሱም ዮሴፍ ያላቸውን፥ የተናገራቸውንም ነገር ሁሉ ነገሩት፤ ይወስዱት ዘንድ ዮሴፍ የላካቸውን ሰረገሎች በአየ ጊዜ የአባታቸው የያዕቆብ ልቡ፥ መንፈሱም ታደሰ። 28 እስራኤልም፥ “ልጄ ዮሴፍ ገና በሕይወት ከሆነ ይህ ለእኔ ታላቅ ነገር ነው፤ ሳልሞት እንዳየው እሄዳለሁ” አለ። |