ዘፍጥረት 44 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)የጠፋው ጽዋዕ 1 ዮሴፍም የቤቱን አዛዥ እንዲህ ብሎ አዘዘው፥ “የእነዚህ ሰዎች ዓይበቶቻቸው መያዝ የሚችሉትን ያህል እህል ሙላላቸው፤ የሁሉንም ብር በየዓይበታቸው አፍ ጨምረው፤ 2 በታናሹም ዓይበት አፍ የብሩን ጽዋዬንና የእህሉን ዋጋ ጨምረው።” እርሱም ዮሴፍ እንዳለው አደረገ። 3 ነግህ በሆነ ጊዜም ሰዎቹ አህዮቻቸውን ይዘው ይሄዱ ዘንድ አሰናበታቸው። 4 ከከተማዪቱም ወጥተው ገና ሳይርቁ ዮሴፍ ለቤቱ አዛዥ እንዲህ አለ፥ “ተነሥተህ ሰዎቹን ተከትለህ ያዛቸው፤ እንዲህም በላቸው፦ በመልካሙ ፈንታ ስለምን ክፉን መለሳችሁ? 5 ጌታዬ የሚጠጣበትን፥ ምስጢርንም የሚያውቅበትን የብር ጽዋ ለምን ሰረቃችሁ? ባደረጋችሁት ነገር በደላችሁ።” 6 እርሱም ሂዶ አገኛቸው፤ “ለምን እንዲህ አደረጋችሁ? ስለ አደረግሁላችሁ መልካም ነገር ለምን ክፉ ትከፍሉኛላችሁ? የጌታዬንስ የብር ጽዋ ለምን ሰረቃችሁኝ?” አላቸው። 7 እነርሱም አሉት፥ “ጌታችን እንደዚህ ለምን ክፉ ትናገራለህ? ይህን ነገር ያደርጉት ዘንድ ለባሪያዎችህ አግባባቸው አይደለም። 8 በየዓይበታችን አፍ ያገኘነውን ብር እንኳን ይዘን ከከነዓን ሀገር ወደ አንተ ተመልሰናል፤ ከጌታህስ ቤት ወርቅ ወይስ ብር እንዴት እንሰርቃለን? 9 አሁንም ከባሪያዎችህ ጽዋው የተገኘበት እርሱ ይሙት፤ እኛም ደግሞ ለጌታችን አገልጋዮች እንሁን።” 10 እርሱም አለ፥ “አሁንም እንዲሁ እንደ ነገራችሁ ይሁን፤ ጽዋው የተገኘበት እርሱ ለእኔ አገልጋይ ይሁነኝ፤ እናንተም ንጹሓን ትሆናላችሁ።” 11 እየራሳቸውም ፈጥነው ዓይበታቸውን ወደ ምድር አወረዱ፤ እየራሳቸውም ዓይበታቸውን ፈቱ። 12 እርሱም ከታላቁ ጀምሮ እስከ ታናሹ ድረስ በረበራቸው፤ ጽዋውንም በብንያም ዓይበት ውስጥ አገኘው። 13 ልብሳቸውንም ቀደዱ፤ ዓይበታቸውንም በየአህዮቻቸው ጭነው ወደ ከተማዪቱ ተመለሱ። 14 ይሁዳም ከወንድሞቹ ጋር ወደ ዮሴፍ ገባ፤ እርሱም ገና ከዚያው ነበረ፤ በፊቱም በምድር ላይ ወደቁ። 15 ዮሴፍም፥ “ይህ ያደረጋችሁት ነገር ምንድን ነው? እንደ እኔ ያለ ሰው ምሥጢርን እንዲያውቅ አታውቁምን?” አላቸው። 16 ይሁዳም አለ፦ “ለጌታችን ምን እንመልሳለን? ምንስ እንናገራለን? ወይስ በምን እንነጻለን? እግዚአብሔር የአገልጋዮችህን ኀጢአት ገለጠ። እነሆ፥ እኛም ጽዋው ከእርሱ ዘንድ የተገኘበትም ደግሞ ለጌታችን አገልጋዮቹ ነን።” 17 ዮሴፍም አላቸው፥ “ይህን አደርግ ዘንድ አይገባኝም፤ ጽዋው የተገኘበት ሰው እርሱ አገልጋይ ይሁነኝ እንጂ፤ እናንተ ግን ወደ አባታችሁ በደኅና ሂዱ።” ይሁዳ ስለ ብንያም ዮሴፍን መለመኑ 18 ይሁዳም ወደ እርሱ ቀረበ፤ እንዲህም አለ፥ “ጌታዬ ሆይ፥ እኔ አገልጋይህ በፊትህ አንዲት ቃልን እንድናገር እለምናለሁ፤ እኔን አገልጋይህን አትቈጣኝ፤ አንተ ከፈርዖን ቀጥለህ ነህና። 19 ጌታዬ አገልጋዮችህን፦ አባት አላችሁን? ወይስ ወንድም? ብለህ ጠየቅሃቸው። 20 እኛም ለጌታዬ እንዲህ አልን፦ ሽማግሌ አባት አለን፤ በሽምግልናው የወለደውም ታናሽ ብላቴና አለ፤ ወንድሙ ግን ሞተ፤ ለእናቱም እርሱ ብቻውን ቀረ፤ አባቱም ይወድደዋል። 21 አንተም ለአገልጋዮችህ፦ ወደ እኔ አምጡት፤ እኔም እጠብቀዋለሁ አልህ። 22 ጌታዬንም፦ ብላቴናው አባቱን መተው አይሆንለትም፤ የተወው እንደ ሆነ አባቱ ይሞታልና አልንህ። 23 አንተ ጌታችንም አገልጋዮችህን፦ ታናሽ ወንድማችሁን ከእናንተ ጋር ከአላመጣችሁት ዳግመኛ ፊቴን አታዩም አልኸን። 24 ወደ ባሪያህ ወደ አባታችን በተመለስን ጊዜም የጌታችንን ቃል ነገርነው። 25 አባታችንም፦ ዳግመኛ ሄዳችሁ ጥቂት እህል ሸምቱልን አለን። 26 እኛም አልነው፦ ታናሹ ወንድማችን ከእኛ ጋር ካልሄደ መሄድ አንችልም፤ ታናሹ ወንድማችን ከእኛ ጋር ከሌለ የዚያን ሰው ፊት ማየት አይቻለንምና። 27 አገልጋይህ አባታችንም እንዲህ አለን፦ ሚስቴ ሁለት ወንዶች ልጆችን እንደ ወለደችልኝ እናንተ ታውቃላችሁ፤ 28 አንዱም ከእኔ ወጣ፤ አውሬ በላው አላችሁኝ፤ እስከ ዛሬም ገና አላየሁትም፤ 29 ይህንም ከእኔ ለይታችሁ ደግሞ ብትወስዱት በመንገድም ክፉ ቢያገኘው፥ እርጅናዬን በኀዘን ወደ መቃብር ታወርዱታላችሁ። 30 አሁንም እኛ ወደ አባታችን ወደ አገልጋይህ ብንሄድ፥ ብላቴናውም ከእኛ ጋር ከሌለ፥ ነፍሱ በብላቴናው ነፍስ ታስራለችና 31 ብላቴናው ከእኛ ጋር እንደሌለ በአየ ጊዜ ይሞታል፤ አገልጋዮችህም የአገልጋይህን የአባታችንን እርጅና በኀዘን ወደ መቃብር እናወርዳለን። 32 እኔ አገልጋይህ በአባቴ ዘንድ ስለ ብላቴናው እንዲህ ብዬ ተውሼአለሁና፦ እርሱንስ ወደ አንተ መልሼ በፊትህ ባላቆመው በአባቴ ዘንድ በዘመናት ሁሉ ኀጢአተኛ እሆናለሁ። 33 አሁንም እኔ በብላቴናው ፈንታ የጌታዬ አገልጋይ ሆኜ ልቀመጥ፤ ብላቴናው ግን ከወንድሞቹ ጋር ይሂድ። 34 አለዚያም ብላቴናው ከእኛ ጋር ከሌለ እኔ ወደ አባታችን እንዴት እሄዳለሁ? አባታችንን የሚያገኘውን መከራ እንዳላይ።” |