ዘፍጥረት 40 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ዮሴፍ የእስረኞችን ሕልም እንደ ተረጐመ 1 ከዚህ ነገር በኋላም እንዲህ ሆነ፤ የግብፅ ንጉሥ የጠጅ አሳላፊዎች አለቃና የእንጀራ አበዛዎች አለቃ ጌታቸውን የግብፅ ንጉሥን በደሉ። 2 ፈርዖንም በሁለቱ ሹሞች በጠጅ አሳላፊዎቹ አለቃና በእንጀራ አበዛዎቹ አለቃ ላይ ተቈጣ፤ 3 በእስር ቤት ውስጥም ዮሴፍ ታስሮ በነበረበት የግዞት ስፍራ አጋዛቸው። 4 የእስር ቤቱ ዘበኞች አለቃም ለዮሴፍ አሳልፎ ሰጣቸው፤ እርሱም ያገለግላቸው ነበር፤ በግዞት ቤትም አንድ ዓመት ተቀመጡ። 5 ሁለቱም በአንዲት ሌሊት ሕልምን አለሙ። በግዞት ቤት የነበሩት የግብፅ ንጉሥ ጠጅ አሳላፊዎች አለቃና የእንጀራ አበዛዎች አለቃ ሁለቱም እየራሳቸው ሕልምን አለሙ። 6 ዮሴፍም ማልዶ ወደ እነርሱ ገባ፤ እነሆም፥ አዝነው አያቸው። 7 በጌታው ቤት ከእርሱ ጋር በግዞት የነበሩትንም የፈርዖን ሹሞች እንዲህ ብሎ ጠየቃቸው፥ “እናንት ዛሬ ስለምን አዝናችኋል?” 8 እነርሱም፥ “ሕልምን አልመን የሚተረጕምልን አጣን” አሉት። ዮሴፍም አላቸው፥ “ሕልምን የሚተረጕም እግዚአብሔር የሰጠው አይደለምን? እስቲ ንገሩኝ፤ ሕልማችሁ ምንድን ነው?” 9 የጠጅ አሳላፊዎች አለቃም ለዮሴፍ ሕልሙን እንዲህ ብሎ ነገረው፥ “በሕልሜ የወይን ሐረግ በፊቴ ሆና አየሁ፥ 10 በሐረጉም ሦስት ቅርንጫፎች ወጡ፤ እርስዋም ቅጠልና አበባ አወጣች፤ ዘለላም አንጠለጠለች፤ የዘለላዋም ፍሬ በሰለ፤ 11 የፈርዖንም ጽዋ በእጄ ነበር፤ ፍሬውንም ወስጄ በፈርዖን ጽዋ ጨመቅሁት፤ ጽዋዉንም ለፈርዖን በእጁ ሰጠሁት።” 12 ዮሴፍም አለው፥ “የሕልምህ ትርጓሜው ይህ ነው፤ ሦስት ቅርንጫፎች ሦስት ቀኖች ናቸው። 13 እስከ ሦስት ቀንም ድረስ ፈርዖን ሹመትህን ያስባል፤ ወደ ጠጅ አሳላፊዎች አለቃነትህም ይመልስሃል፤ ጠጅ አሳላፊ በነበርህበት ጊዜ ስታደርገው እንደ ነበረው እንደ ቀድሞው ሹመትህም የፈርዖንን ጽዋ በእጁ ትሰጣለህ። 14 ነገር ግን በጎ ነገር በተደረገልህ ጊዜ እኔን ዐስበኝ፤ ምሕረትንም አድርግልኝ፤ ስለ እኔም ለፈርዖን አሳስበህ ከዚህ እስር ቤት አውጣኝ፤ 15 ሌቦች በስውር ከዕብራውያን ሀገር ሰርቀውኛልና፤ በዚህም ደግሞ ምንም ያደረግሁት ሳይኖር በግዞት ቤት አኑረውኛልና።” 16 የእንጀራ አበዛዎቹ አለቃም ሕልሙን በመልካም እንደ ተረጐመለት በአየ ጊዜ ዮሴፍን እንዲህ አለው፥ “እኔም ደግሞ ሕልም አይች ነበር፤ እነሆም፥ ሦስት መሶብ ነጭ እንጀራ በራሴ ላይ ነበረ፤ 17 በላይኛውም መሶብ ፈርዖን የሚበላው ጋጋሪው በያይነቱ የሠራው መብል ነበረበት፤ ወፎችም በራሴ ላይ ከመሶቡ ይበሉ ነበር።” 18 ዮሴፍም መልሶ እንዲህ አለው፥ “የሕልምህ ትርጓሜው ይህ ነው፤ ሦስቱ መሶብ ሦስት ቀን ነው፤ 19 እስከ ሦስት ቀን ድረስ ፈርዖን ራስህን ይቈርጥሃል፤ በዕንጨትም ላይ ይሰቅልሃል፤ የሰማይ ወፎችም ሥጋህን ይበሉታል።” 20 እንዲህም ሆነ፤ በሦስተኛው ቀን ፈርዖን የተወለደበት ዕለት ነበር፤ ለሠራዊቱም ሁሉ ግብር አደረገ፤ የጠጅ አሳላፊዎቹን አለቃና የእንጀራ አበዛዎቹን አለቃ በአሽከሮቹ መካከል ዐሰበ። 21 የጠጅ አሳላፊዎቹንም አለቃ ወደ ሹመቱ መለሰው፤ ጽዋውንም በፈርዖን እጅ ሰጠ፤ 22 የእንጀራ አበዛዎቹንም አለቃ በዕንጨት ላይ ሰቀለው፤ ዮሴፍ እንደ ተረጐመላቸው። 23 የጠጅ አሳላፊዎች አለቃ ግን ዮሴፍን አላሰበውም፤ ረሳው እንጂ። |