ዘፍጥረት 38 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ይሁዳና ትዕማር 1 በዚያም ወራት እንዲህ ሆነ፤ ይሁዳ ከወንድሞቹ ተለይቶ ወረደ፤ ስሙ ኤራስ በሚባል በዓዶሎማዊውም ሰው ዘንድ አደረ። 2 ከዚያም ይሁዳ ያንድ ከነዓናዊ ሰው ሴት ልጅን አየ፤ ስምዋም ሴዋ ይባላል። ወሰዳትም፤ ወደ እርስዋም ገባ። 3 ፀነሰችም፤ ወንድ ልጅንም ወለደች፤ ስሙንም ዔር ብላ ጠራችው። 4 ደግሞም ፀነሰች፤ ወንድ ልጅንም ወለደች፤ ስሙንም አውናን ብላ ጠራችው። 5 እንደገና ደግሞ ወንድ ልጅን ወለደች፤ ስሙንም ሴሎም ብላ ጠራችው፤ እነርሱንም በወለደች ጊዜ ኬሴቢ በሚባል ሀገር ነበረች። 6 ይሁዳም ለበኵር ልጁ ለዔር ትዕማር የምትባል ሚስት አጋባው። 7 የይሁዳም የበኵር ልጅ ዔር በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ነበረ፤ እግዚአብሔርም ቀሠፈው። 8 ይሁዳም አውናንን፥ “ወደ ወንድምህ ሚስት ግባ፤ አግባትም፤ ለወንድምህም ዘርን አቁምለት” አለው። 9 አውናንም ዘሩ ለእርሱ እንዳይሆን ዐወቀ፤ ወደ ወንድሙ ሚስትም በገባ ጊዜ ለወንድሙ ዘር እንዳይተካ ዘሩን በምድር ያፈስሰው ነበር። 10 ይህም ሥራው በእግዚአብሔር ዘንድ ክፉ ሆነበት፤ እንዲህ አድርጎአልና እርሱንም ደግሞ ቀሠፈው። 11 ይሁዳም ምራቱን ትዕማርን፥ “ልጄ ሴሎም እስኪያድግ ድረስ በአባትሽ ቤት መበለት ሆነሽ ተቀመጪ” አላት፤ እርሱ ደግሞ እንደ ወንድሞቹ እንዳይሞትብኝ ብሎአልና። ትዕማርም ሄዳ በአባቷ ቤት ተቀመጠች። 12 ዘመንዋም በተፈጸመ ጊዜ የይሁዳ ሚስት ሴዋ ሞተች፤ ይሁዳም ተጽናና፤ የበጎቹን ጠጕር ወደሚሸልቱት ሰዎችም ወደ ተምና ወጣ፤ እርሱም ዓዶሎማዊው በግ ጠባቂው ኤራስም። 13 ለምራቱ ትዕማርም፥ “እነሆ፥ አማትሽ ይሁዳ የበጎቹን ጠጕር ይሸልት ዘንድ ወደ ተምና ይወጣል” ብለው ነገሩአት። 14 እርስዋም የመበለትነቷን ልብስ አወለቀች፤ መጐናጸፊያዋንም ለበሰች፤ ተሸፈነችም፤ ወደ ተምናም በሚወስደው መንገድ ዳር በኤናይም ደጅ ተቀመጠች፤ ሴሎም እንደ አደገ፥ ሚስትም ትሆነው ዘንድ እርስዋን ሊሰጠው እንዳልፈለገ አይታለችና። 15 ይሁዳም በአያት ጊዜ ዘማ መሰለችው፤ ፊቷን ተሸፍና ነበርና አላወቃትም። 16 ወደ እርስዋም አዘነበለ፥ “እባክሽ ወደ አንቺ ልግባ አላት፤” እርስዋ ምራቱ እንደ ሆነች አላወቀም ነበርና። እርስዋም፥ “ወደ እኔ ብትገባ ምን ትሰጠኛለህ?” አለችው። 17 “የፍየል ጠቦት ከመንጋዬ እልክልሻለሁ” አላት። እርስዋም፥ “እስክትልክልኝ ድረስ መያዣ ስጠኝ” አለችው። 18 እርሱም፥ “ምን መያዣ ልስጥሽ?” አላት። እርስዋም፥ “ቀለበትህን፥ ኩፌትህን፥ በእጅህ ያለውን በትር” አለች። እርሱም ሰጣትና ከእርስዋ ደረሰ፤ እርስዋም ፀነሰችለት። 19 እርስዋም ተነሥታ ሄደች፤ መጐናጸፊያዋንም አውልቃ የመበለትነቷን ልብስ ለበሰች። 20 ይሁዳም መያዣውን ከሴቲቱ እጅ ይቀበል ዘንድ በበግ ጠባቂው በዓዶሎማዊው እጅ የፍየሉን ጠቦት ላከላት፤ እርስዋንም አላገኛትም። 21 እርሱም የሀገሩን ሰዎች፥ “በኤናይም በመንገድ ዳር ተቀምጣ የነበረች ዘማ ወዴት ናት?” ብሎ ጠየቃቸው። እነርሱም፥ “በዚህ ዘማ አልነበረችም” አሉት። 22 ወደ ይሁዳም ተመልሶ እንዲህ አለው፥ “አላገኘኋትም፤ የሀገሩ ሰዎች ደግሞ፦ ከዚህ ዘማ የለችም” አሉኝ። 23 ይሁዳም፥ “እኛ መዘበቻ እንዳንሆን ትውሰደው፤ እነሆ፥ የፍየሉን ጠቦት ላክሁላት፤ አንተም አላገኘሃትም” አለ። 24 እንዲህም ሆነ፤ ከሦስት ወር በኋላ ለይሁዳ፥ “ምራትህ ትዕማር ሴሰነች፤ እነሆ፥ በዝሙት ፀነሰች” ብለው ነገሩት። ይሁዳም፥ “አውጡአትና በእሳት ትቃጠል” አለ። 25 እርስዋም ሲወስዱአት ወደ አማቷ እንዲህ ብላ ላከች፤ “ተመልከት፦ ይህ ቀለበት፥ ይህ ኩፌት፥ ይህ በትር የማን ነው? ይህስ ፅንስ የማን ነው?” 26 ይሁዳም አይቶ “ከእኔ ይልቅ ትዕማር እውነተኛ ሆነች፤ ልጄን ሴሎምን አልሰጠኋትምና” አለ። ትገደል ማለትንም ተወ፤ ደግሞም አላወቃትም። 27 መውለጃዋም በደረሰ ጊዜ እነሆ፥ መንታ ልጆች በሆድዋ ነበሩ። 28 ስትወልድም አንዱ እጁን አወጣ፤ አዋላጂቱም ቀይ ፈትል ወስዳ በእጁ አሰረች፥ “ይህ መጀመሪያ ይወጣል” አለች። 29 እንዲህም ሆነ፤ እጁን በመለሰ ጊዜ እነሆ፥ ወንድሙ ወጣ፤ እርስዋም፥ “ለምን ጥሰህ ወጣህ? ስትል ስሙን ፋሬስ” ብላ ጠራችው። 30 ከእርሱም በኋላ ቀይ ፈትል በእጁ ያለበት ወንድሙ ወጣ፤ ስሙም ዛራ ተባለ። |