ዘፍጥረት 34 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)የኤሞር ልጅ ዲናን እንደ አስነወራት 1 ለያዕቆብ የተወለደች የልያ ልጅ ዲናም የዚያን ሀገር ሴቶች ልጆችን ለማየት ወጣች። 2 የሀገሩ አለቃ የኤዊያዊው ሰው የኤሞር ልጅ ሴኬም አያት፤ ወሰዳትም፤ ከእርስዋም ጋር ተኛ፤ አስነወራትም። 3 ልቡናውም በያዕቆብ ልጅ በዲና ፍቅር ተነደፈ፤ ብላቴናዪቱንም ወደዳት፤ ልብዋንም ደስ በሚያሰኛት ነገር ተናገራት። 4 ሴኬምም አባቱን ኤሞርን፥ “ይህችን ብላቴና አጋባኝ” ብሎ ነገረው። 5 ያዕቆብም ልጁን ዲናን የኤሞር ልጅ እንዳስነወራት ሰማ፤ ልጆቹም ከከብቶቻቸው ጋር በምድረ በዳ ነበሩ፤ ያዕቆብም ልጆቹ እስኪመጡ ድረስ ዝም አለ። 6 የሴኬም አባት ኤሞርም ይነግረው ዘንድ ወደ ያዕቆብ መጣ። 7 የያዕቆብም ልጆች ከምድረ በዳ መጡ፤ ይህንም በሰሙ ጊዜ ፈጽመው ደነገጡ፤ የያዕቆብን ልጅ በመተኛቱ በእስራኤል ላይ ኀፍረትን ስላደረገ አዘኑ፤ እጅግም ተቈጡ፤ እንዲህ አይደረግምና። 8 ኤሞርም እንዲህ ብሎ ነገራቸው፥ “ልጄ ሴኬም ልጃችሁን ወዶአታልና ሚስት እንድትሆነው እርስዋን ስጡት። 9 ጋብቾችም ሁኑን፤ ሴቶች ልጆቻችሁን ስጡን፤ እናንተም የእኛን ሴቶች ልጆች ለልጆቻችሁ ውሰዱ። 10 ከእኛም ጋር ተቀመጡ፤ ምድራችንም በፊታችሁ ሰፊ ናት፤ ኑሩባት፤ ነግዱም፤ ግዙአትም።” 11 ሴኬምም አባቷንና ወንድሞችዋን እንዲህ አለ፥ “በፊታችሁ ሞገስን በአገኝ የምትሉትን ሁሉ እሰጣለሁ። 12 ብዙ ማጫ አምጣ በሉኝ፤ በምትጠይቁኝም መጠን እሰጣለሁ፤ ይህችን ብላቴና ግን ሚስት ትሆነኝ ዘንድ ስጡኝ።” 13 የያዕቆብም ልጆች ለሴኬምና ለአባቱ ለኤሞር በተንኰል መለሱ፤ እኅታቸውን ዲናን አስነውሮአታልና፤ 14 የዲና ወንድሞች ስምዖንና ሌዊም እንዲህ አሉአቸው፥ “እኅታችንን ላልተገረዘ ሰው ለመስጠት ይህን ነገር እናደርግ ዘንድ አይቻለንም፤ ይህ ነውር ይሆንብናልና። 15 እናንተም እንደ እኛ ወንዶቻችሁን ሁሉ ብትገርዙ በዚህ ብቻ እንመስላችኋለን፤ ከእናንተም ጋር እንኖራለን፤ 16 ሴቶች ልጆቻችንንም እንሰጣችኋለን፤ የእናንተንም ሴቶች ልጆች ለሚስትነት እንወስዳለን፤ አንድ ሕዝብም ሆነን ከእናንተ ጋር እንኖራለን። 17 ትገረዙ ዘንድ እኛን ባትሰሙ ግን ልጃችንን ይዘን እንሄዳለን።” 18 ነገራቸውም ኤሞርንና የኤሞርን ልጅ ሴኬምን ደስ አሰኛቸው። 19 ብላቴናውም ይህን ነገር ያደርግ ዘንድ አልዘገየም፤ የያዕቆብን ልጅ ወድዶአልና፤ እርሱም ከአባቱ ቤተ ሰብእ ሁሉ የከበረ ነበረ። 20 ኤሞርና ልጁ ሴኬምም ሄዱና ወደ ከተማቸው በር ደረሱ፤ ለከተማቸውም ሰዎች ሁሉ እንዲህ ብለው ነገሩ፦ 21 “እነዚህ ሰዎች በእኛ ዘንድ የሰላም ሰዎች ናቸው፤ በምድራችን ይቀመጡ፤ ይነግዱባትም፤ እነሆም፥ ምድሪቱ ሰፊ ናት፤ ሴቶች ልጆቻቸውን ለሚስትነት እንውሰድ፤ ለእነርሱም ሴቶች ልጆቻችንን እንስጥ። 22 እነርሱ እንደ እኛ ይሆኑ ዘንድ በዚህ ብቻ እንምሰላቸው። አንድ ወገንም እንሁን፤ እነርሱ እንደሚገርዙ ወንዶቻችንን ሁሉ እንገርዛለን። 23 መንጋቸውም፥ የጋማ ከብቶቻቸውም፥ ገንዘባቸውም ሁሉ ለእኛ አይደሉምን? ነገር ግን በዚህ ብቻ ከመሰልናቸው ከእኛ ጋር ይቀመጣሉ።” 24 በከተማዪቱም በር የሚገቡ ሁሉ ኤሞርንና ልጁን ሴኬምን እሺ አሉ፤ ወንዶችም ሁሉ የሰውነታቸውን ሸለፈት ተገረዙ። የዲና ወንድሞች በቀል 25 እንዲህም ሆነ፤ በሦስተኛው ቀን እጅግ ቈስለው ሳሉ ሁለቱ የያዕቆብ ልጆች የዲና ወንድሞች ስምዖንና ሌዊ እየራሳቸው ሰይፋቸውን ይዘው ተደፋፍረው ወደ ከተማ ገቡ፤ ወንዱንም ሁሉ ገደሉ፤ 26 ኤሞርንና ልጁን ሴኬምንም በሰይፍ ገደሉ፤ እኅታቸው ዲናንም ከሴኬም ቤት ይዘው ወጡ። 27 የያዕቆብ ልጆችም ወደ ሞቱት ገብተው እኅታቸው ዲናን ያስነወሩባትን ከተማዪቱን ዘረፉ፤ 28 ላሞቻቸውንም፥ በጎቻቸውንም፥ አህዮቻቸውንም በሜዳም፥ በከተማም ያለውን ወሰዱ ። 29 ሎሌዎቻቸውንና ሚስቶቻቸውን፥ የቤታቸውንም ቈሳቍስ ሁሉ ማረኩ፤ በቤትና በከተማ ያለውንም ሁሉ ዘረፉ። 30 ያዕቆብም ስምዖንንና ሌዊን እንዲህ አላቸው፥ “ክፉ አደረጋችሁብኝ፤ በዚች ሀገር በሚኖሩ በከነዓናውያንና በፌርዜዎናውያን ሰዎች ዘንድ አስጠላችሁኝ። እኔ በቍጥር ጥቂት ነኝ፤ እነርሱ በእኔ ላይ ይሰበሰቡና ይወጉኛል፤ እኔና ቤቴም እንጠፋለን።” 31 እነርሱም፥ “እኅታችንን እንደ አመንዝራ አድርገው ለምን አዋረዷት?” አሉት። |