ዘፍጥረት 23 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)የሣራ መሞትና አብርሃም የመቃብር ቦታ መግዛቱ 1 የሣራም ዕድሜ መቶ ሃያ ሰባት ዓመት ሆነ። 2 ሣራም በቈላ ውስጥ ባለች አርባቅ በምትባል ከተማ ሞተች፤ እርስዋም በከነዓን ምድር ያለች ኬብሮን ናት፤ አብርሃምም ለሣራ ሊያዝንላትና ሊያለቅስላት ተነሣ። 3 አብርሃምም ከሬሳው አጠገብ ተነሣ፤ ለኬጢ ልጆችም እንዲህ ሲል ተናገረ፦ 4 “እኔ በእናንተ ዘንድ ስደተኛና መጻተኛ ነኝ፤ በእናንተ ዘንድ እንድገዛ የመቃብር ርስት ስጡኝ፤ ሬሳዬንም እንደ እናንተ ልቅበር።” 5 የኬጢ ልጆችም ለአብርሃም መለሱ፤ አሉትም፦ 6 “አይሆንም፥ ጌታ ሆይ፥ ስማን፤ አንተ ከእግዚአብሔር ዘንድ ለእኛ ንጉሥ ነህና ከመቃብር ስፍራችን በመረጥኸው ቦታ ሬሳህን ቅበር፤ ሬሳህን በዚያ ትቀብር ዘንድ ከእኛ መቃብሩን የሚከለክልህ የለም።” 7 አብርሃምም ተነሣ፤ በሀገሩ ሕዝብ ፊትም ለኬጢ ልጆች ሰገደ። 8 እንዲህም አላቸው፥ “ሬሳዬን ከፊቴ አርቄ እንድቀብር ከወደዳችሁስ ስሙኝ፤ ለሰዓር ልጅ ለኤፍሮንም ስለ እኔ ንገሩት፤ 9 በእርሻው ዳር ያለችውን ድርብ ክፍል ያላትን ዋሻውን ይስጠኝ፤ መቃብሩ የእኔ ርስት እንዲሆን በሚገባው ዋጋ በመካከላችሁ ይስጠኝ፤ ከእርሱም እገዛለሁ።” 10 ኤፍሮንም በኬጢ ልጆች መካከል ተቀምጦ ነበር፤ የኬጢ ሰው ኤፍሮንም የኬጢ ልጆችና ወደ ከተማ የሚገቡ ሁሉ ሲሰሙ ለአብርሃም እንዲህ ሲል መለሰለት፦ 11 “አይደለም፥ ጌታዬ፥ ቀርበህ ስማኝ፤ እርሻውን፥ በውስጡም ያለውን ዋሻውን ሰጥቼሃለሁ፤ በወገኔ ልጆች ፊት ሰጥቼሃለሁ፤ ሬሳህን ቅበር።” 12 አብርሃምም በሀገሩ ሕዝብ ሁሉ ፊት ሰገደ፤ 13 የሀገሩ ሕዝብም ሲሰሙ ለኤፍሮን እንዲህ ሲል ተናገረ፥ “ከእኔ ቅርብ ነህና ስማኝ፤ የእርሻህንም ዋጋ ከእኔ ውሰድ፤ ሬሳዬንም በዚያ እቀብራለሁ።” 14 ኤፍሮንም ለአብርሃም እንዲህ ሲል መለሰለት፥ “አይሆንም፤ ጌታዬ ሆይ፥ እኔን ስማኝ፤ 15 የአራት መቶ ምዝምዝ ብር ዋጋ ምድር በእኔና በአንተ መካከል ምንድን ነው? እንግዲህ ሬሳህን በዚያ ቅበር።” 16 አብርሃምም የኤፍሮንን ነገር ሰማ፤ አብርሃምም በኬጢ ልጆች ፊት የነገረውንና ተቀባይነት ያለውን ግብዝ ያይደለ አራት መቶ ምዝምዝ ብር መዝኖ ለኤፍሮን ሰጠው። 17 በመምሬ ፊት ያለው ባለ ድርብ ክፍል የሆነው የኤፍሮን እርሻም ለአብርሃም ጸና፤ እርሻው፥ በእርሱም ያለ ዋሻው፥ በእርሻውም ውስጥ በዙሪያውም ያለው ዕንጨት ሁሉ፤ 18 በኬጢ ልጆችና በከተማዪቱ በር በሚገቡ ሁሉ ፊት ለአብርሃም ርስቱ ሆነ። 19 ከዚህም በኋላ አብርሃም ኬብሮን በምትባል በመምሬ ፊት በከነዓን ምድር ባለው እርሻ ባለ ድርብ ክፍል በሆነው ዋሻ ውስጥ ሚስቱን ሣራን ቀበረ። 20 እርሻውና በእርሱ ያለው ዋሻም በኬጢ ልጆች ዘንድ ለአብርሃም የመቃብር ርስት ሆኖ ጸና። |