ዘፀአት 31 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ደብተራ ኦሪትን የሠሩ ባስልኤልና ኤልያብ ( ዘፀ. 35፥30—36፥1 ) 1 እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ 2 “እይ! ከይሁዳ ነገድ የሚሆን የሆር የልጅ ልጅ የኡሪ ልጅ ባስልኤልን በስሙ ጠርቼዋለሁ። 3 በሥራ ሁሉ ያስተውል ዘንድ በጥበብም፥ በማስተዋልም፥ በዕውቀትም የእግዚአብሔርን መንፈስ ሞላሁበት፤ 4 የአናጺዎች አለቃ ይሆን ዘንድ ወርቅንና ብርን፥ ናስንም፥ ብጫና ሰማያዊ፥ እጥፍ ሆኖ የተፈተለ ነጭና ቀይ ሐርን ይሠራ ዘንድ፤ 5 በሥራውም ሁሉ የሚደረገውን የድንጋይ ማለዘብን፥ ከዕንጨትም የሚጠረበውን ይሠራ ዘንድ። 6 እኔም እነሆ፥ ከዳን ነገድ የሚሆን የአሂሳሚክን ልጅ ኤልያብን ሰጠሁ፤ ያዘዝሁህን ሁሉ ያደርጉ ዘንድ በልባቸው ጥበበኞች ለሆኑት ሁሉ ዕውቅትን ሰጠሁ። 7 የምስክሩን ድንኳን፥ የቃል ኪዳኑንም ታቦት፥ በእርሱም ላይ ያለውን የስርየት መክደኛውን፥ የድንኳኑንም ዕቃ ሁሉ፤ 8 የዕጣን መሠዊያውን፥ ገበታውንም፥ ዕቃውንም፥ ከዕቃው ሁሉ የነጻውን መቅረዝ፥ 9 ለሚቃጠል መሥዋዕት የሚሆነውን መሠዊያ፥ ዕቃውንም ሁሉ፥ የመታጠቢያውን ሰንና መቀመጫውንም፥ 10 በክህነት እኔን የሚያገለግሉበትን የካህኑን የአሮንን ልብሰ ተክህኖና የልጆቹን ልብስ፥ 11 የሚቀቡትን የቅብዐቱንም ዘይት፥ ለመቅደሱ የሚያጥኑትን ዕጣን እንዳዘዝሁህ ሁሉ ያድርጉ።” የሰንበት ሕግ 12 እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ሲል ተናገረው፦ 13 “ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ንገራቸው፦ እኔ የምቀድሳችሁ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቁ ዘንድ በእኔና በእናንተ ዘንድ ለልጅ ልጃችሁ ምልክት ነውና ሰንበቴን ፈጽሞ ጠብቁ። 14 ለእናንተ በእግዚአብሔር የተቀደሰች ናትና ሰንበቴን ጠብቁ፤ የሚያረክሳትም ሰው ሁሉ ፈጽሞ ይገደል፤ ሥራንም በእርስዋ የሠራ ሰው ሁሉ ያች ነፍስ ከሕዝብዋ መካከል ተለይታ ትጥፋ። 15 ስድስት ቀን ሥራህን ሥራ፤ ሰባተኛዋ ቀን ግን ለእግዚአብሔር የተቀደስች የዕረፍት ሰንበት ናት፤ በሰንበት ቀን የሚሠራ ሁሉ ፈጽሞ ይገደል። 16 የእስራኤልም ልጆች ለልጅ ልጃቸው ለዘለዓለም ቃል ኪዳን ዕረፍት ያደርጉ ዘንድ ሰንበትን ይጠብቁ። 17 እግዚአብሔር ሰማይንና ምድርን በስድስት ቀን ስለ ፈጠረ፥ በሰባተኛውም ቀን ሥራውን ፈጽሞ ስላረፈ፥ በእኔና በእስራኤል ልጆች ዘንድ የዘለዓለም ምልክት ነው።” 18 እግዚአብሔርም ከእርሱ ጋር በሲና ተራራ የተናገረውን በፈጸመ ጊዜ ሁለቱን የምስክር ጽላት፥ በእግዚአብሔር ጣት የተጻፈባቸውን የድንጋይ ጽላት ለሙሴ ሰጠው። |