ዘፀአት 26 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ስለ ተቀደሰው ድንኳን ( ዘፀ. 36፥8-38 ) 1 “ለድንኳኑም ከተፈተለ ከጥሩ በፍታ፥ ከሰማያዊ፥ ከሐምራዊም፥ ከቀይም ግምጃ ዐሥር መጋረጆችን ሥራ፤ ኪሩቤልም በእነርሱ ላይ ይሁኑ፤ እንደ ሽመና ሥራም በብልሃት ትሠራቸዋለህ። 2 የእያንዳንዱ መጋረጃ ርዝመት ሃያ ስምንት ክንድ፥ ወርዱም አራት ክንድ ይሁን፤ የመጋረጆችም ሁሉ መጠን ትክክል ይሁን። 3 አምስቱ መጋረጃዎች እርስ በርሳቸው የተጋጠሙ ይሁኑ፤ ሌሎችም አምስት መጋረጃዎች እንዲሁ እርስ በርሳቸው የተጋጠሙ ይሁኑ።። 4 ከሚጋጠሙት መጋረጆች በአንደኛው መጋረጃ ዘርፍ ላይ የሰማያዊውን ግምጃ ቀለበቶች አድርግ፤ ደግሞ ከተጋጠሙት ከሌሎች በአንደኛው መጋረጃ ዘርፍ ላይ በውጭ በኩል እንዲሁ አድርግ። 5 አምሳ ቀለበቶችን በአንድ መጋረጃ አድርግ፤ አምሳውንም ቀለበቶች በሁለተኛው መጋረጃ ዘርፍ አድርግ፤ ቀለበቶቹ ሁሉ እርስ በርሳቸው ፊት ለፊት ይሆናሉ። 6 አምሳ የወርቅ መያዣዎች ሥራ፤ መጋረጃዎችን እርስ በርሳቸው በመያዣዎች አጋጥማቸው፤ ድንኳኑም አንድ ይሆናል። 7 “ከማደሪያውም በላይ ለድንኳን የሚሆኑ መጋረጃዎች ከፍየል ጠጕር አድርግ፤ ዐሥራ አንድ መጋረጃዎች ታደርጋለህ። 8 እያንዳንዱም መጋረጃ ርዝመቱ ሠላሳ ክንድ፥ እያንዳንዱም መጋረጃ ወርዱ አራት ክንድ ይሁን፤ የዐሥራ አንዱም መጋረጃዎች መጠናቸው ትክክል ይሁን። 9 አምስቱ መጋረጃዎች እርስ በርሳቸው አንድ ሆነው ይጋጠሙ፤ ስድስቱም መጋረጃዎች እርስ በርሳቸው አንድ ሆነው ይጋጠሙ፤ ስድስተኛውም መጋረጃ በድንኳኑ ፊት ይደረብ። 10 በውጭ ከተጋጠሙት መጋረጃዎች በአንደኛው መጋረጃ ዘርፍ ላይ አምሳ ቀለበቶች አድርግ፤ ደግሞ ከተጋጠሙት ከሌሎቹ በአንደኛው መጋረጃ ዘርፍ ላይ እንዲሁ አምሳ ቀለበቶች አድርግ። 11 አምሳም የናስ መያዣዎችን ሥራ፤ መያዣዎችንም ወደ ቀለበቶች አግባቸው፤ መጋረጃዎችንም አጋጥማቸው፤ አንድም ይሆናሉ። 12 ከድንኳኑ መጋረጃዎች የቀረ ትርፍ ግማሽ መጋረጃ በድንኳኑ ጀርባ ይጋረድ። 13 ድንኳኑን እንዲሸፍን ከርዝመቱ በአንድ ወገን አንድ ክንድ፤ በአንድ ወገንም አንድ ክንድ ከድንኳኑ መጋረጆች የቀረው ትርፍ በድንኳኑ ውጭ በወዲህና በወዲያ ይጋረድ። 14 ለድንኳኑም መደረቢያ ከቀይ አውራ በግ ቍርበት፥ ከዚያም በላይ ሌላ መደረቢያ ከአቆስጣ ቍርበት አድርግ። 15 “ለድንኳኑም ሳንቆችን ከማይነቅዝ ዕንጨት አድርግ። 16 የእያንዳንዱም ሳንቃ ርዝመቱ ዐሥር ክንድ፥ ወርዱም አንድ ክንድ ተኩል ይሁን። 17 ለእያንዳንዱም ሳንቃ አንዱን በአንዱ ላይ የሚያያይዙ ሁለት ማጋጠሚያዎች ይሁኑለት፤ ለድንኳኑ ሳንቆች ሁሉ እንዲሁ አድርግ። 18 ለድንኳኑም በደቡብ በኩል ሃያ ሳንቆችን አድርግ። 19 ከሃያውም ሳንቆች በታች አርባ የብር እግሮችን አድርግ፤ ከእያንዳንዱ ሳንቃ በታች ለሁለት ማጋጠሚያዎች ሁለት እግሮች ይሁኑ። ከሌላውም ሳንቃ በታች ለሁለት ማጋጠሚያዎች ሁለት እግሮች ይሁኑ። 20 ለድንኳኑ ለሁለተኛው ወገን በሰሜን በኩል ሃያ ሳንቆች፥ 21 ለእነርሱም አርባ የብር እግሮች ይሁኑ፤ ከእያንዳንዱም ሳንቃ በታች ሁለት እግሮች ይሁኑ። 22 ለድንኳኑም በምዕራቡ በኩል በስተኋላ ስድስት ሳንቆች አድርግ። 23 ለድንኳኑም ለሁለቱ ማዕዘን በስተኋላ ሁለት ሳንቆች አድርግ። 24 ከታችም እኩል ይሁኑ፤ ከላይ እስከ አንደኛው መጋጠሚያ ድረስ እንደ አንደኛ ክፍል እኩል ይሁኑ፤ እንዲሁም ለሁለቱ ማዕዘን አድርግ፤ እኩልም ይሁኑ። 25 ስምንት ሳንቆችና ዐሥራ ስድስት የብር እግሮቻቸው ይሁኑ፤ ከእያንዳንዱም ሳንቃ በታች በሁለቱም መጋጠሚያዎች ሁለት ሁለት እግሮች ይሆናሉ። 26 “ከማይነቅዝ ዕንጨት መወርወሪያዎችን ሥራ፤ በድንኳኑ በአንደኛው ገጽ ላሉ ሳንቆች አምስት መወርወሪያዎችን፥ 27 በድንኳኑ በሁለተኛ ወገን ላሉት ሳንቆች አምስት መወርወሪያዎችን፥ በድንኳኑም በስተኋላ በምዕራብ በኩል ላሉት ሳንቆች አምስት መወርወሪያዎችን አድርግ። 28 መካከለኛውም መወርወሪያ በሳንቆቹ መካከል ከዳር እስከ ዳር ይለፍ። 29 ሳንቆቹን በወርቅ ለብጣቸው፤ ቀለበቶቻቸውንም የመወርወሪያ ቤት እንዲሆኑላቸው ከወርቅ ሥራቸው፤ መወርወሪያዎችንም በወርቅ ለብጣቸው። 30 ድንኳኑንም በተራራው ላይ በአሳየሁህ ምሳሌ ሥራ። 31 “መጋረጃውንም ከሰማያዊ፥ ከሐምራዊም፥ ከቀይም ግምጃ ከተፈተለ ከጥሩ በፍታም አድርግ፤ በሽመና ሥራም ኪሩቤልን ሥራ። 32 በወርቅ በተለበጡት፥ ከማይነቅዝ ዕንጨትም በተሠሩት በአራቱ ምሰሶዎች ላይ ስቀለው፤ ኩላቦቻቸውም ከወርቅ፥ አራቱም እግሮቻቸው ከብር የተሠሩ ይሁኑ። 33 መጋረጃውንም በምሰሶዎች ላይ ስቀለው፤ በመጋረጃውም ውስጥ የምስክሩን ታቦት አግባው፤ መጋረጃውም በቅድስቱና በቅድስተ ቅዱሳኑ መካከል መለያ ይሁናችሁ። 34 መጋረጃውም የምስክሩን ታቦት በቅድስተ ቅዱሳኑ ውስጥ ይጋርድ። 35 ገበታውንም በመጋረጃው ውጭ፥ መቅረዙንም በገበታው ፊት ለፊት በድንኳኑ በደቡብ ወገን አድርግ፤ ገበታውንም በድንኳኑ በሰሜን ወገን አድርገው። 36 ለድንኳኑ ደጃፍም ከሰማያዊ፥ ከሐምራዊም፥ ከቀይ ግምጃም ከተፈተለ ከጥሩ በፍምታም በጥልፍ አሠራር የተሠራ መጋረጃ አድርግለት። 37 ለመጋረጃውም አምስት ምሰሶዎች ከማይነቅዝ ዕንጨት አድርግ፤ በወርቅም ለብጣቸው፤ ኩላቦቻቸውም ከወርቅ የተሠሩ ይሁኑ፤ አምስትም የናስ እግሮች አድርግላቸው። |