ዘፀአት 25 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ለቤተ እግዚአብሔር የሚቀርብ መባ ( ዘፀ. 35፥4-9 ) 1 እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ሲል ተናገረው፦ 2 “የእስራኤልን ልጆች በልባችሁ ያሰባችሁትን ከገንዘባችሁ መባ አምጡልኝ” በላቸው። 3 ከእነርሱም የምትቀበሉት መባ ይህ ነው፤ ወርቅ፥ ብር፥ ናስም፥ 4 ሰማያዊና ሐምራዊ፥ ቀይም ድርብ ግምጃ፥ ጥሩ በፍታም፥ 5 የፍየልም ጠጕር፥ ቀይ የተለፋ የአውራ በግ ቍርበት፥ ሰማያዊ ቀለም የገባ ቍርበት፥ የማይነቅዝ ዕንጨት፥ 6 የመብራትም ዘይት፥ ለቅብዐት ዘይትና ለጣፋጭ ዕጣን ቅመም፥ 7 መረግድም፥ ለልብሰ እንግድዓና ለደረት ኪስ የሚደረግ ፈርጥ። 8 መቅደስ ትሠራልኛለህ፤ በመካከላቸውም አድራለሁ። 9 በተራራው እንዳሳየሁህ ሁሉ፥ እንደ ማደሪያው ምሳሌ፥ እንደ ዕቃውም ሁሉ ምሳሌ ለእኔ ትሠራለህ፤ እንዲሁ ትሠራለህ። የቃል ኪዳኑ ታቦት ( ዘፀ. 37፥1-9 ) 10 “ከማይነቅዝ ዕንጨትም የምስክሩን ታቦት ሥራ፤ ርዝመቱ ሁለት ክንድ ተኩል፥ ወርዱም አንድ ክንድ ተኩል፥ ቁመቱም አንድ ክንድ ተኩል ይሁን። 11 በውስጥና በውጭም በጥሩ ወርቅ ለብጠው፤ በእርሱም ላይ በዙሪያው የወርቅ አክሊል አድርግለት። 12 አራት የወርቅ ቀለበቶችም አድርግለት፤ እነርሱንም በአራቱ እግሮቹ ላይ አኑር፤ በአንድ ወገን ሁለት ቀለበቶች፥ በሌላ ወገን ሁለት ቀለበቶች ይሁኑ። 13 መሎጊያዎችንም ከማይነቅዝ ዕንጨት ሥራ፤ በወርቅም ለብጣቸው። 14 ለታቦቱ መሸከሚያ በታቦቱ ጎን ባሉት አራት ቀለበቶች መሎጊያዎቹን አግባ። 15 መሎጊያዎቹም በታቦቱ ቀለበቶች ውስጥ ተዋድደው ይኑሩ፤ ከቶም አይውጡ። 16 በታቦቱም ውስጥ እኔ የምሰጥህን ምስክር ታስቀምጣለህ። 17 ከጥሩ ወርቅም ርዝመቱ ሁለት ክንድ ተኩል፥ ወርዱም አንድ ክንድ ተኩል የሆነ የስርየት መክደኛ ሥራ። 18 ሁለት ኪሩቤል ከተቀጠቀጠ ወርቅ ሥራ፤ በስርየት መክደኛውም ላይ በሁለት ወገን ታደርጋቸዋለህ። 19 ከስርየት መክደኛውም ጋር አንዱን ኪሩብ በአንድ ወገን፥ ሁለተኛውንም ኪሩብ በሌላው ወገን አድርገህ በአንድ ላይ ትሠራዋለህ፤ ሁለቱንም ኪሩቤል እንዲሁ በሁለት ወገን ታደርጋቸዋለህ። 20 ኪሩቤልም ክንፎቻቸውን ወደ ላይ ይዘረጋሉ፤ የስርየት መክደኛውንም በክንፎቻቸው ይሸፍናሉ፤ ፊታቸውም እርስ በርሱ ይተያያል፤ የኪሩቤልም ፊቶቻቸው ወደ ስርየት መክደኛው ይሁን። 21 የስርየት መክደኛውንም በታቦቱ ላይ ታደርገዋለህ፤ እኔም የምሰጥህን ምስክር በታቦቱ ውስጥ ታኖረዋለህ። 22 በዚያም እገለጥልሃለሁ፤ ለእስራኤል ልጆች የማዝዝህን ሁሉ፥ በምስክሩ ታቦት ላይ ባለው በሁለት ኪሩቤል መካከል፥ በስርየት መክደኛውም ላይ ሆኜ እነጋገርሃለሁ። ኅብስተ ገጹ የሚቀመጥበት ገበታ ( ዘፀ. 37፥10-16 ) 23 “ርዝመቱም ሁለት ክንድ፥ ወርዱም አንድ ክንድ፥ ቁመቱም አንድ ክንድ ተኩል የሆነ ገበታ ከማይነቅዝ ዕንጨት ሥራ። 24 በጥሩም ወርቅ ትለብጠዋለህ፤ በዙሪያውም የወርቅ አክሊል አድርግለት፤ 25 በዙሪያውም አንድ ጋት የሚያህል ክፈፍ አድርግለት፤ የወርቅም አክሊል በክፈፉ ዙሪያ አድርግለት። 26 አራትም የወርቅ ቀለበቶች አድርግለት፤ ቀለበቶቹንም አራት እግሮቹ ባሉበት በአራቱ ማዕዘኖች አድርግ። 27 ቀለበቶቹም ገበታውን ለመሸከም መሎጊያዎቹ እንዲሰኩባቸው በክፈፉ አቅራቢያ ይሁኑ። 28 መሎጊያዎቹንም ከማይነቅዝ ዕንጨት ሥራ፤ በንጹሕ ወርቅም ለብጣቸው፤ ገበታውም በእነርሱ ይነሣ። 29 ለማፍሰሻም ይሆኑ ዘንድ ወጭቶችዋን፥ ጭልፋዎችዋንም፥ መቅጃዎችዋንም፥ ጽዋዎችዋንም አድርግ፤ እነርሱንም ከጥሩ ወርቅ አድርጋቸው። 30 በገበታም ላይ ኅብስተ ገጹን ሁልጊዜ በፊቴ ታደርጋለህ። የቤተ እግዚአብሔር መቅረዝ ( ዘፀ. 37፥17-24 ) 31 “መቅረዝንም ከጥሩ ወርቅ አድርግ፤ የመቅረዙም እግሩና ቅርንጫፎቹ የተቀጠቀጠ ሥራ ይሁን፤ ጽዋዎቹም፥ ጕብጕቦቹም፥ አበቦቹም አንድነት በእርሱ ይደረጉበት። 32 በስተጐኑ ስድስት ቅርንጫፎች ይውጡለት፤ ሦስት የመቅረዙ ቅርንጫፎች በአንድ ወገን፥ ሦስትም የመቅረዙ ቅርንጫፎች በሌላ ወገን ይውጡ። 33 በአንደኛውም ቅርንጫፍ ጕብጕብና አበባ፥ ሦስትም የለውዝ አበባ የሚመስሉትን ጽዋዎች፤ በሁለተኛውም ቅርንጫፍ ጕብጕብና አበባ፥ ሦስትም የለውዝ አበባ የሚመስሉትን ጽዋዎች፤ እንዲሁም ከመቅረዙ ለሚወጡ ለስድስት ቅርንጫፎች አድርግ። 34 በመቅረዙም ጕብጕቦቹንና አበቦቹን፥ አራትም የለውዝ አበባ የሚመስሉትን ጽዋዎች ከእርሱ አድርግ። 35 ከመቅረዙ ለሚወጡ ለስድስቱ ቅርንጫፎች ከሁለት ቅርንጫፎች በታች አንድ ሆኖ የተሠራ አንድ ጕብጕብ፥ ከሁለቱም ቅርንጫፎች በታች አንድ ሆኖ የተሠራ አንድ ጕብጕብ፥ ደግሞ ከሁለት ቅርንጫፎች በታች አንድ ሆኖ የተሠራ አንድ ጕብጕብ ይሁን። 36 ጕብጕቦቹና ቅርንጫፎቹ ሁሉ ከእርሱ ጋር አንድ ይሁኑ፤ ሁሉም አንድ ሆኖ ከተቀጠቀጠ ከጥሩ ወርቅ ይደረግ። 37 ሰባቱንም መብራቶች ሥራ፤ በፊቱ ያበሩ ዘንድ መብራቶቹን ያቀጣጥሉአቸዋል። 38 መኰስተሪያዎችዋን፥ የኵስታሪ ማድረጊያዎችዋንም ከጥሩ ወርቅ አድርግ። 39 መቅረዙም፥ ዕቃውም ሁሉ ከአንድ መክሊት ጥሩ ወርቅ ይሠሩ። 40 በተራራ ላይ እንዳሳየሁህ ምሳሌ እንድትሠራ ተጠንቀቅ። |