ዘፀአት 24 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)እግዚአብሔር ቃል ኪዳኑን እንደ አጸና 1 እግዚአብሔርም ሙሴን አለው፥ “አንተ፥ አሮንም፥ ናዳብም፥ አብዩድም፥ ከእስራኤልም ሰባ ሽማግሌዎች ወደ እግዚአብሔር ውጡ፤ በሩቁም ለእግዚአብሔር ስገዱ፤ 2 ሙሴም ብቻውን ወደ እግዚአብሔር ይቅረብ፤ እነርሱ ግን አይቅረቡ፤ ሕዝቡም ከእነርሱ ጋር አይውጡ።” 3 ሙሴም ገባ፤ ለሕዝቡም የእግዚአብሔርን ቃሎች ሁሉ፥ ሥርዐቱንም ሁሉ ነገረ፤ ሕዝቡም ሁሉ በአንድ ድምፅ፥ “እግዚአብሔር የተናገራቸውን ቃሎች ሁሉ እንሰማለን፤ እናደርጋለንም” ብለው መለሱ። 4 ሙሴም የእግዚአብሔርን ቃሎች ጻፈ፤ ማለዳም ተነሣ፤ ከተራራውም በታች መሠዊያን ሠራ፤ ዐሥራ ሁለትም ድንጋዮችን ለዐሥራ ሁለቱ የእስራኤል ነገድ አቆመ። 5 የእስራኤልንም ልጆች ጐልማሶች ላከ፤ የሚቃጠል መሥዋዕትንም አቀረቡ፤ ለእግዚአብሔርም ስለ ደኅንነት መሥዋዕት በሬዎችን ሠዉ። 6 ሙሴም የደሙን እኵሌታ ወስዶ በቆሬ ውስጥ አደረገው፤ የደሙንም እኵሌታ በመሠዊያው ረጨው። 7 የቃል ኪዳኑንም መጽሐፍ ወስዶ ለሕዝቡ አነበበላቸው፤ እነርሱም፥ “እግዚአብሔር ያለውን ሁሉ እንሰማለን፤ እናደርጋለንም” አሉ። 8 ሙሴም ደሙን ወስዶ በሕዝቡ ላይ ረጨው፤ በዚህ ቃል ሁሉ “እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር ያደረገው የቃል ኪዳኑ ደም እነሆ” አለ። 9 ሙሴም፥ አሮንም፥ ናዳብም፥ አብዩድም፥ ከእስራኤልም ሰባ ሽማግሌዎች ወጡ፤ 10 የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔርም የቆመበትን ቦታ አዩ፤ ከእግሩም በታች እንደ ሰማይ መልክ የሚያበራ፥ እንደ ብሩህ ሰንፔር ድንጋይ የሚመስል ወለል ነበረ። 11 የሚመስላቸው የሌለ የእስራኤል ምርጦችም በእግዚአብሔር ቦታ ታዩ፤ በሉም፤ ጠጡም። ሙሴ በሲና ተራራ ላይ 12 እግዚአብሔርም ሙሴን፥ “ወደ እኔ ወደ ተራራው ውጣ፤ በዚያም ሁን፤ እኔ የጻፍሁትን ሕግና ትእዛዝ፥ የድንጋይም ጽላት እሰጥሃለሁ፤ ሕግንም ትሠራላቸዋለህ” አለው። 13 ሙሴም ከኢያሱ ጋር ተነሣ፤ ወደ እግዚአብሔር ተራራም ወጡ። 14 ሽማግሌዎችንም፥ “ወደ እናንተ እስክንመለስ ድረስ በዚህ ቈዩን፤ ግርግር አትበሉ፤ አሮንና ሆርም እነሆ፥ ከእናንተ ጋር ናቸው፤ ነገረተኛም ቢኖር ወደ እነርሱ ይሂድ” አላቸው። 15 ሙሴም ከኢያሱ ጋር ወደ ተራራ ወጣ፤ ደመናውም ተራራውን ሸፈነው። 16 የእግዚአብሔርም ክብር በሲና ተራራ ላይ ወረደ፤ ደመናውም ስድስት ቀን ሸፈነው፤ በሰባተኛውም ቀን እግዚአብሔር ከደመናው ውስጥ ሙሴን ጠራው። 17 በተራራውም ራስ ላይ በእስራኤል ልጆች ፊት የእግዚአብሔር ክብር መታየት እንደሚያቃጥል እሳት ነበረ። 18 ሙሴም ወደ ደመናው ውስጥ ገባ፤ ወደ ተራራውም ወጣ፤ ሙሴም በተራራው ላይ አርባ ቀን፥ አርባ ሌሊትም ቈየ። |