ዘፀአት 21 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ስለ ባሪያዎች የተሰጠ ሕግ ( ዘዳ. 15፥12-18 ) 1 “በፊታቸው የምታደርገው ሥርዐት ይህ ነው። 2 ዕብራዊ ባሪያ የገዛህ እንደ ሆነ ስድስት ዓመት ያገልግልህ፤ በሰባተኛውም ዓመት በነጻ አርነት ይውጣ። 3 ብቻውን መጥቶ እንደ ሆነ ብቻውን ይውጣ፤ ከሚስቱም ጋር መጥቶ እንደ ሆነ ሚስቱ ከእርሱ ጋር ትውጣ። 4 ጌታው ሚስት አጋብቶት እንደ ሆነ ወንዶች ወይም ሴቶች ልጆች ብትወልድለት፥ ሚስቱና ልጆቹ ለጌታው ይገዙ፤ እርሱም ብቻውን ነጻ ይውጣ። 5 ባሪያውም፦ ጌታዬን፥ ሚስቴን፥ ልጆችንም እወድዳለሁ፤ አርነትም አልወጣም ብሎ ቢናገር፥ 6 ጌታው ወደ ቤተ እግዚአብሔር ፈራጆች ይውሰደው፤ ወደ ደጁም፥ ወደ መቃኑም አቅርቦ አፍንጫውን በወስፌ ይብሳው፤ ለዘለዓለምም ባሪያው ይሁነው። 7 “ሴት ልጁን ለባርነት አሳልፎ የሰጠ ቢኖር ሴቶች ባሪያዎች አርነት እንደሚወጡ እርስዋ ትውጣ። 8 ለእርሱ ከታጨች በኋላ ጌታዋን ደስ ባታሰኘው በዎጆ ይስደዳት፤ ነገር ግን ለሌላ ወገን ይሸጣት ዘንድ አይገባውም። እርሱ አርክሶአታልና። 9 ለልጁም ሊድራት ቢወድድ፥ ለሴት ልጆች የሚገባውን ያድርግላት፤ 10 ከእርስዋም ሌላ ቢያገባ፥ ቀለብዋን፥ ልብስዋንም፥ ለጋብቻዋም ተገቢውን ይስጣት፤ እንዳልበደላትም ምስክር ያሰማባት። 11 ይህንም ሦስት ነገር ባያደርግላት ያለ ገንዘብ ነጻ ትውጣ። ዐመፀኞች የሚቀጡበት ሕግ 12 “ሰው ሰውን ቢመታ፥ ቢሞትም፥ የመታው ፈጽሞ ይገደል። 13 ሳይፈቅድ ቢመታው፥ ባይሸምቅበትም፥ ነገር ግን እግዚአብሔር ድንገት በእጁ ቢጥለው፥ ገዳዩ የሚሸሽበትን ስፍራ እኔ አደርግልሃለሁ። 14 ሰው ግን ቢሸምቅ ጠላቱንም በተንኰል ቢገድለውና ቢማፀን፥ እንዲገደል ከመሠዊያዬ አውጥተህ ውሰደው። 15 “አባቱን ወይም እናቱን የሚማታ ይገደል። 16 “አባቱን ወይም እናቱን የሚሰድብ በሞት ይቀጣ። 17 “ከእስራኤል ልጆች አንዱን የሰረቀ ወይም ግፍ የፈጸመበት፥ ወይም አሳልፎ ቢሰጠው፥ ወይም በእርሱ ዘንድ ቢገኝ፥ እርሱ ይገደል። 18 “ሁለት ሰዎችም እርስ በርሳቸው ቢጣሉ፥ አንዱም ሌላውን በድንጋይ ወይም በጡጫ ቢመታ፥ ያም ባይሞት ነገር ግን በአልጋው ላይ ቢተኛ፥ 19 ተነሥቶም በምርኩዝ ወደ ሜዳ ቢወጣ፥ የመታው ንጹሕ ነው፤ ነገር ግን ተግባሩን ስላስፈታው ገንዘብ ይክፈለው፤ ለባለ መድኀኒትም ይክፈልለት። 20 “ሰውም ወንድ ባሪያውን ወይም ሴት ባሪያውን በበትር ቢመታ፥ በእጁ ቢሞትበትም፥ ፈጽሞ ይቀጣ፤ 21 የተመታው ግን አንድ ወይም ሁለት ቀን ቢቈይ ገንዘቡ ነውና አይቀጣ። 22 “ሁለት ሰዎች እርስ በርሳቸው ቢጣሉ፥ ያረገዘችንም ሴት ቢያቈስሉ ተሥዕሎተ መልክእ ያልተፈጸመለት ፅንስም ቢያስወርዳት፥ የሴቲቱ ባል የጣለበትን ያህል ካሳ ይክፈል፤ 23 ተሥዕሎተ መልክእ የተፈጸመለት ፅንስ ቢያስወርዳት ግን ሕይወት በሕይወት፥ 24 ዐይን በዐይን፥ ጥርስ በጥርስ፥ እጅ በእጅ፥ እግር በእግር፥ 25 መቃጠል በመቃጠል፥ ቍስል በቍስል፥ ግርፋት በግርፋት ይክፈል። 26 “ሰውም የባሪያውን ዐይን ወይም የባሪያዪቱን ዐይን ቢመታ፥ ቢያጠፋውም፥ ስለ ዐይናቸው አርነት ያውጣቸው። 27 የባሪያውን ጥርስ ወይም የባሪያዪቱን ጥርስ ቢሰብር፥ ስለ ጥርሳቸው አርነት ያውጣቸው። ስለ ንብረት የተሰጠ ሕግ 28 “በሬም ወንድን ወይም ሴትን ቢወጋ ቢሞቱም፥ በሬው በድንጋይ ይወገር፤ ሥጋውም አይበላ፤ የበሬው ባለቤት ግን ንጹሕ ነው። 29 በሬው ግን ከትናንትና ከትናንት ወዲያ ተዋጊ ቢሆን፥ ሰዎችም ለባለቤቱ ቢመሰክሩለት ባያስወግደውም፥ ወንድን ወይም ሴትን ቢገድል፥ በሬው ይወገር፤ ባለቤቱ ደግሞ ይገደል። 30 ከእርሱ ግን ካሳ ቢፈልጉ፥ የሕይወቱን ካሳ የጫኑበትን ያህል ይስጥ። 31 በሬው ወንድን ልጅ ቢወጋ፥ ሴትንም ልጅ ቢወጋ ይህንኑ ፍርድ ያድርጉበት። 32 በሬው ወንድ ባሪያ ወይም ሴት ባሪያ ቢወጋ፥ የበሬው ባለቤት ሠላሳ የብር ሰቅል ለጌታቸው ይስጥ፤ በሬውም ይወገር። 33 “ሰውም ጕድጓድ ቢከፍት ወይም ጕድጓድ ቢቈፍር ባይከድነውም፥ በሬም ወይም አህያ፤ ቢወድቅበት፥ 34 የጕድጓዱ ባለቤት ዋጋቸውን ለባለቤታቸው ይክፈል፤ የሞተውም ለእርሱ ይሁን። 35 “የሰው በሬ የሌላውን በሬ ቢወጋ፥ ቢሞትም፥ ደኅናውን በሬ ይሽጡ፤ ዋጋውንም በትክክል ይካፈሉ፤ የሞተውንም ደግሞ በትክክል ይካፈሉ። 36 በሬውም ትናንትና ከትናንት ወዲያ ተዋጊ መሆኑ ቢታወቅ ለባለቤቱም ቢመሰክሩለት፥ ባለቤቱም ባያስወግደው በሬውን በበሬው ፋንታ ይስጥ፤ የሞተውም ለእርሱ ይሁነው። |