ዘፀአት 17 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ውኃ ከዓለት እንደ ፈለቀላቸው ( ዘዳ. 20፥1-13 ) 1 የእስራኤል ልጆች ማኅበር ሁሉ እግዚአብሔር እንዳዘዘ ከሲን ምድረ በዳ ሊጓዙ ተነሡ፤ በራፊድም ሰፈሩ፤ በዚያም ሕዝቡ የሚጠጡት ውኃ አልነበረም። 2 ሕዝቡም ሙሴን ተጣሉት፥ “የምንጠጣውን ውኃ ስጠን” አሉ። ሙሴም፥ “ለምን ትጣሉኛላችሁ? እግዚአብሔርንስ ለምን ትፈታተናላችሁ?” አላቸው። 3 ሕዝቡም በዚያ ስፍራ ውኃ ተጠሙ፥ “እኛንና ልጆቻችንን፥ ከብቶቻችንንም በጥማት ልትገድል ለምን ከግብፅ አወጣኸን?” ሲሉ በሙሴ ላይ አንጐራጐሩ። 4 ሙሴም፦ ወደ እግዚአብሔር ጮኸ፤ እንዲህም አለ፥ “ለዚህ ሕዝብ ምን ላድርግ? በድንጋይ ሊወግሩኝ ጥቂት ቀርቶአቸዋልና።” 5 እግዚአብሔርም ሙሴን፥ “በሕዝቡ ፊት እለፍ፤ ከእስራኤልም ሽማግሌዎችን ከአንተ ጋር ውሰድ፤ ወንዙንም የመታህባትን በትር በእጅህ ይዘሃት ሂድ። 6 እነሆ፥ እኔ በዚያ በኮሬብ በዓለት ላይ በፊትህ እቆማለሁ፤ ዓለቱንም ትመታለህ፤ ሕዝቡም ይጠጣ ዘንድ ከእርሱ ውኃ ይወጣል” አለው። ሙሴም በእስራኤል ልጆች ፊት እንዲሁ አደረገ። 7 ስለ እስራኤልም ልጆች ክርክር፥ “እግዚአብሔር በመካከላችን ነውን? ወይስ አይደለም?” ሲሉ እግዚአብሔርን ስለ ተፈታተኑት የዚያን ስፍራ ስም “መንሱት” ደግሞም “ጋእዝ” ብሎ ጠራው። እስራኤል ዐማሌቃውያንን ድል እንደ አደረጉ 8 ዐማሌቅም መጥቶ ከእስራኤል ጋራ በራፊድ ተዋጋ። 9 ሙሴም ኢያሱን፥ “ጐልማሶችን ለአንተ ምረጥ፤ ሲነጋም ወጥተህ ከዐማሌቅ ጋር ተዋጋ፤ እኔም በተራራው ራስ ላይ እቆማለሁ፤ የእግዚአብሔርም በትር በእጄ ናት” አለው። 10 ኢያሱም ሙሴ እንደ አለው አደረገ፤ ወጥቶም ከዐማሌቅ ጋር ተዋጋ፤ ሙሴና አሮን፥ ሖርም ወደ ኮረብታው ራስ ወጡ። 11 እንዲህም ሆነ፤ ሙሴ እጁን በአነሣ ጊዜ እስራኤል ድል ያደርግ ነበር ፤ እጁንም በአወረደ ጊዜ ዐማሌቅ ድል ያደርግ ነበር። 12 የሙሴ እጆች ግን ከብደው ነበር፤ ድንጋይም ወሰዱ፤ በበታቹም አኖሩ፤ እርሱም ተቀመጠበት፤ አሮንና ሖርም አንዱ በዚህ አንዱ በዚያ ሆነው እጆቹን ይደግፉ ነበር፤ ፀሐይም እስክትገባ ድረስ እጆቹ ተዘርግተው ነበር። 13 ኢያሱም ዐማሌቅንና ሕዝቡን በሰይፍ ስለት አሸነፈ። 14 እግዚአብሔርም ሙሴን፥ “የዐማሌቅን ዝክር ከሰማይ በታች ጨርሼ እደመስሳለሁና ይህን ለመታሰቢያ በመጽሐፍ ጻፈው፤ በኢያሱም ጆሮ ተናገር” አለው። 15 ሙሴም መሠዊያ ሠራ፤ ስሙንም “ምምሕፃን” ብሎ ጠራው፤ 16 እግዚአብሔር በተሰወረች እጅ ዐማሌቅን እስከ ልጅ ልጅ ይዋጋልና። |