Este libro no es inspirado por Dios y no forma parte del canon cristiano ni del Tanaj judío. Se muestra solo con fines históricos y de estudio. Ver explicación completa መጽሐፈ ሄኖክ 40 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)1 ዛሬም እኔ በታላቅ ጌትነቱና ክብሩ፥ በከበረ መንግሥቱና በገናናነቱ ለእናንተ ለጻድቃን እምላለሁ። 2 ይህንም ምሥጢር እኔ አውቃለሁና፥ በሰማይ ሰሌዳ ያለውን አንብቤአለሁና፥ ቅዱሳን የጻፉትንም አይቻለሁና እምልላችኋለሁ። 3 በጎው ነገር ሁሉ፥ ደስታውና ክብሩም ተዘጋጅቶላቸዋልና ስለ እነርሱ በውስጣቸው ተጽፎና ተቀርፆ አገኘሁ። 4 በእውነትና በቀና ነገር፥ በብዙም በጎነት ለሞቱ ሰዎች ነፍሳት ተጻፈላቸው፤ የድካማችሁም ዋጋ ይሰጣችኋል፤ እድላችሁም ከሕያዋን እድል ይበልጣል። 5 ስለ ጽድቅ የሞታችሁ የእናንተ ነፍስ ትድናለች፤ ነፍሶቻቸውም ደስ ይላቸዋል፤ ሐሤትም ያደርጋሉ። 6 መታሰቢያቸውም በእግዚአብሔር ፊት ለልጅ ልጅ ዘመን ይኖራል፤ አሁንም መከራቸውን አትፍሩት። 7 የሞታችሁ ኃጥኣን፥ በኀጢአታችሁ በምትሞቱበት ጊዜ ወዮላችሁ! 8 እንደ እናንተም ያሉ በእናንተ ላይ እንዲህ ይላሉ፤ ኃጥኣን ብፁዓን ናቸው፤ ዘመናቸውን ሁሉ አይተዋልና። 9 ዛሬም በበጎነትና በባለጠግነት ሞቱ፤ መከራውንና ሰልፉንም በሕይወታቸው አላዩም፤ በጌትነትም ሞቱ፤ በሕይወታቸውም ፍርድ አልተደረገባቸውም። 10 ነፍሶቻቸው ወደ ሲኦል እንደሚወርዱ፥ ክፋታቸውም ጽኑ መከራ እንደሚሆንባቸው አታውቋቸውምን? 11 ሰውነታችሁም በጨለማና በወጥመድ፥ በሚነድ ወላፈንም ወደ ጽኑ ፍርድ ትገባለች፤ ጽኑ ፍርድም በዓለም ትውልድ ሁሉ ትሆናለች። 12 ሰላም የላችሁምና ወዮላችሁ! በሕይወት ላሉ ለጻድቃንና ለደጋጎች እንዲህ አትበሉአቸው- “በደከምንበት ወራት ድካምን ደከምን። 13 መከራውን ሁሉ አየን፤ ብዙ መከራዎችንም ተቀበልን፤ ጨርሰን ጠፋን፤ አነስን፤ ሰውነታችንም አነሰች፤ ጠፋንም። 14 በነገርም የሚረዳን የለም፤ በሥራም ደከምን፤ ምንም አላገኘንም፥ ተጨነቅን፤ ጠፋንም፤ 15 ከዛሬ ነገ ሕይወትን እናይ ዘንድ ተስፋ አደረግን፥ ራስ ልንሆን ተስፋ አደረግን፤ ነገር ግን ጅራት ሆን፤ ስንሠራም ደከምን። 16 ነገር ግን በድካማችን ላይ ግዳጃችንን አልፈጸምንም፤ ለኃጥኣንም መብሎችን ሆን፤ ዐመፀኞችም ቀንበራቸውን አከበዱብን። 17 እኛን የሚጠሉንና የሚወጉን በእኛ ሠለጠኑብን፤ ለሚጠሉንም አንገታችንን ዝቅ አደረግን፤ እነርሱ ግን አልራሩልንም። 18 ከእነርሱ እንሸሽና እናርፍ ዘንድ እንድንሄድ ወደድን፤ ከእነርሱም ሸሽተን የምንድንበትን አላገኘንም። 19 በመከራችን ጊዜ በአለቆች ዘንድ ከሰስናቸው፤ በሚጠሉንም ላይ ጮህን፤ ጩኸታችንን ግን አልሰሙንም፤ ቃላችንንም ሊሰሙን አይወዱም። 20 የሚቀሙንን፥ የሚበሉብንን፥ ያጐደሉብንንም ይረዷቸዋል፤ ግፋቸውንም ይሰውሩላቸዋል፤ ቀንበራቸውን ከእኛ አያወጡም፤ ነገር ግን ይበሉናል። 21 ይበትኑናል፤ ይገድሉናል፤ ሞታችንንም ይሰውራሉ፤ እጃቸውንም ከእኛ ላይ ያነሡ ዘንድ አላሰቡም።” 22 ጻድቃን! እምልላችኋለሁ፤ መላእክት በገናናው ጌትነት ፊት በሰማይ ስለ እናንተ በጎ ያስባሉና። 23 ስሞቻችሁም በገናናው ጌትነት ፊት ይጻፋሉ። አስቀድሞ በክፋትና በድካም ጐስቍላችኋልና ተስፋ አድርጉ። 24 አሁንም እንደ ሰማይ ብርሃን አብርታችሁ ትታያላችሁ፤ የሰማይ ደጃፍም ይከፈትላችኋል። 25 ጩኸታችሁ ይሰማል፤ ለፍርድ ጩኹ፤ ይገለጥላችሁማል፤ ችግራችሁም ሁሉ ከመላእክትና የሚነጥቋችሁን ከሚረዷቸው ሁሉ ይመረመራልና። 26 እንደ መላእክት በሰማይ ታደርጓት ዘንድ ታላቅ ደስታ ትሆንላችኋለችና ተስፋ አድርጉ፤ ተስፋችሁንም አትተዉ፥ በታላቋ የፍርድ ቀንም ትሰወሩ ዘንድ ያላችሁ አይደለም። 27 እንደ ኃጥኣንም ሁናችሁ አትገኙም፤ ከእናንተ ወዲያ የዘለዓለም ፍርድ ለዓለም ትውልድ ሁሉ ትሆናለች። 28 አሁንም ጻድቃን! ኃጥኣንን በፈቃዳቸው ጸንተውና ተዘጋጅተው በምታይዋቸው ጊዜ አትፍሩ። 29 ከሰማይ ሠራዊት ጋር አንድ ትሆኑ ዘንድ አላችሁና ከእነርሱ ግፍ ራቁ እንጂ ከእነርሱ ጋራ አትተባበሩ። 30 እናንተ ኃጥኣን! ኀጢአታችን ሁሉ አይመረመርም፤ አይጻፍብንም፥ ትላላችሁ፥ ነገር ግን ኃጢአቶቻችሁ ሁሉ በየቀኑ ይጻፉ ዘንድ አላቸው። 31 አሁንም ብርሃንና ጨለማ፥ ቀንና ሌሊት ኀጢአታችሁን ሁሉ ይገልጡባችኋልና እኔ አሳያችኋለሁ፤ በልቡናችሁም አትዘንጉ፤ አቷሹም። 32 የፍርድንም ነገር አትመልሱት፤ የቅዱሱንና የገናናውንም ነገር ሐሰት አታድርጉት፤ ጣዖታችሁንም አታክብሩት፥ ሐሰታችሁ ሁሉ፥ ዝንጋታችሁም ሁሉ ለታላቅ ኀጢኣት እንጂ ለጽድቅ አይደለችምና። 33 ዛሬም እኔ ይህን ምሥጢር ዐውቀዋለሁ፤ ብዙዎች ኃጥኣን የፍርድን ነገር ይመልሳሉና፥ ይገለብጡማልና። 34 ክፉዎችንም ነገሮች ይናገራሉ፤ ታላላቅ ልብ ወለድንም በሐሰት ፈጥረው ይናገራሉ፤ በነገራቸውም ላይ መጻፎችን ይጽፋሉ። 35 ነገር ግን ነገሮቼን ሁሉ በቅንነት በአንደበቶቻቸው ቢጽፉ ኖሮ፥ ከነገሮቼም በአይለውጡና በአያጐድሉም ስለ እነርሱ አስቀድሜ ያዳኘሁባቸውን ሁሉ በቅንነት በጻፉ ነበር። 36 ሌላ ምሥጢርንም ዐውቃለሁ፤ ለጻድቃንና ለጠቢባን ስለ ደስታና ስለ ቅን ፍርድ፥ ስለ ብዙ ጥበብም መጻሕፍት ይሰጧቸዋልና፤ 37 ለእነርሱም መጻሕፍት ይሰጣሉ፤ እነርሱም ያምኑባቸዋል፤ በእነርሱም ደስ ይላቸዋል፤ ሐሤትም ያደርጋሉ፤ ከእነርሱም የእውነት መንገዶችን ሁሉ ያወቁ ጻድቃን ሁሉ ዋጋቸውን ያገኛሉ። 38 በእነዚያም ወራቶች ጌታ እንዲጠሯቸውና ጥበባቸውን ለምድር ልጆች እንዲያሰሙ እንዲህ አለ- 39 “እናንተ መሪዎቻቸው ናችሁና፥ በምድርም ሁሉ ላይ ስጦታዎች ናችሁና አሳዩአቸው። 40 እኔና ልጄ በእውነት መንገዶች በሕይወታቸው ከእነርሱ ጋር ለዘለዓለም አንድ እንሆናለን፤ ሰላምም ይሆንላችኋል፤ የእውነት ልጆች! በእውነት ደስ ይበላችሁ።” |