Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


Este libro no es inspirado por Dios y no forma parte del canon cristiano ni del Tanaj judío. Se muestra solo con fines históricos y de estudio. Ver explicación completa

መጽሐፈ ሄኖክ 38 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)

1 ጻድቃን፥ በእነዚያ ወራቶች ለመታሰቢያ ጸሎታችሁን ትቀበሉ ዘንድ ተዘጋጁ።

2 ኃጥኣን በልዑል ፊት ኀጢአትን ለመታሰቢያ እንደሚያኖሩት እናንተም በመላእክት ፊት ምስክሮች አድርጋችሁ አኑሯቸው።

3 በእነዚያም ወራቶች አሕዛብ ይታወካሉ ፥ በጥፋትም ቀን የአሕዛብ ዘመዶች ይነሣሉ።

4 በእነዚያም ወራቶች የተቸገሩ ይወጣሉ፤ ልጆቻቸውንም ይነጥቃሉ፥ ልጆቻቸውንም ይጥሏቸዋል።

5 ከእነርሱም ልጆቻቸውን ያስወርዳሉ፤ እየጠቡም ሳሉ ልጆቻቸውን ይጥሏቸዋል።

6 ወደ እነርሱም አይመለሱም፥ ለሚወዷቸውም አይራሩላቸውም።

7 ዳግመኛም ለእናንተ ለኃጥኣን እኔ እምልላችኋለሁ፥ የማይገታ ደም ለሚፈስባት ቀን ኀጢአት ተዘጋጅታለችና።

8 ለድንጋይም ይሰግዳሉ፥ የወርቁንና የብሩን፥ የእንጨቱንና የሸክላውን ምስልም ይሠራሉ።

9 ለረከሱ መናፍስትና ለክፉዎች አጋንንት፥ ለጣዖቱም ሁሉ፥ ለመስገጃውም ሁሉ ይሰግዳሉ።

10 ከእነርሱም ረድኤት ሁሉ አይገኝም፤ ስለ ልቡናቸውም ድንቍርና ይዘነጋሉ፥ በልቡናቸው ፍርሀትም ዐይኖቻቸው ይጋረዳሉ።

11 ሕልማቸውንም በማየት ይረሳሉ፥ ይፈራሉም፤ ሥራቸውን ሁሉ በሐሰት ሠርተዋልና፥ ለድንጋዩም ሰግደዋልና፥ ፈጥነውም ይጠፋሉና።

12 በእነዚያም ወራቶች የጥበብን ነገር የሚቀበሉና የሚያውቋት ሁሉ ብፁዓን ናቸው።

13 የልዑልንም ሥራዎች ይሠሯቸዋል፥ በጽድቅም መንገድ ይሄዳሉ። እነርሱ ይድናሉና ከሚዘነጉ ሰዎች ጋር አይዘነጉም።

14 ለወንድማችሁ ክፉውን የምትዘረጉ ወዮላችሁ! በሲኦል ትጠፋላችሁና።

15 የኀጢአትንና የተንኰልን መሠረት የምትሠሩ፥ በምድርም ላይ የምታሳዝኑ ወዮላችሁ! በእርሱ ትጠፋላችሁና።

16 በባዕድ ገንዘብ ቤታችሁን የምትሠሩ ወዮላችሁ! ሥራቸውም ሁሉ ጡብ ነው፥ የኀጢአትም ድንጋይ ነው፤ ሰላም እንደሌላችሁም እኔ እነግራችኋለሁ።

17 ለዘለዓለም የሚኖር የአባቶቻቸውን ድንበርና ርስት ለሚያፈርሱ ወዮላቸው! ለእነርሱም ዕረፍት አይደረግላቸውምና ልቡናቸውን ወደ ጣዖቱ ይወስዱታል።

18 ዐመፅን የምትሠሯትና ግፍን የምትረዷት፥ እስከ ታላቋ የፍርድ ቀንም ድረስ ባልንጀሮቻችሁን የምትገድሉ፥ ወዮላችሁ! ክብራችሁን ይጥላልና፤ በልቡናችሁም ክፋትን ይጨምራልና።

19 ሁላችሁንም በሰይፍ ያጠፋችሁ ዘንድ የቍጣውን መንፈስ ያስነሣል፥ ቅዱሳንና ጻድቃን ሁሉም ኀጢአታችሁን ያስባሉ።

20 በእነዚያም ወራቶች አባቶች ከልጆቻቸው ጋር በአንድ ቦታ ይገደላሉ፤

21 ወንድሞች ከወንድሞቻቸው ጋር ደማቸው እንደ ፈሳሽ ውኃ እስኪፈስስ ድረስ በሞት ይወድቃሉ። ሰው ከልጁና ከልጅ ልጁ ይገድለው ዘንድ በመራራት እጁን አይከለክልምና።

22 ኀጢአተኛውም ከከበረ ወንድሙ እጁን አይከለክልም፥ ከንጋትም ጀምሮ ፀሐይ እስኪገባ ድረስ ይዋጋሉ።

23 ፈረስም በኃጥኣን ደም ውስጥ እስከ እምቢያጕሱ ድረስ ይሄዳል፥ ሠረገላም እስከ ራሷ ድረስ ትሰጥማለች።

24 በእነዚያም ወራቶች መላእክት ወደሚሰወሩበት ቦታ ይወርዳሉ።

25 ኀጢአትን የሚረዷትንም ሁሉ ወደ አንድ ቦታ ይመልሷቸዋል።

26 ልዑልም በኃጥኣን ሁሉ ታላቅ ፍርድ ይፈርድ ዘንድ በዚያች ቀን ይነሣል።

27 ከቅዱሳን መላእክትም በቅዱሳንና በጻድቃን ላይ ጠባቂዎችን ይሰጣል፥ እነርሱም ክፋት ሁሉ፥ ኀጢአትም ሁሉ ጨርሶ እስኪጠፋ ድረስ እንደ ዐይን ብሌን ይጠብቋቸዋል።

28 ጻድቃን ረዥም እንቅልፍን ቢተኙም የሚፈሩት ነገር የላቸውም።

29 ጠቢባን እውነተኛ ነገርን ያያሉ፤ የዚህ ዓለም ልጆችም የዚችን መጽሐፍ ነገር ሁሉ ያስተውላሉ፥ ባለጸግነታቸውም በኀጢአታቸው በሚወድቁበት ጊዜ ሊያድናቸው እንደማይችል ያውቃሉ።

30 ኃጥኣን፥ በጽኑ መከራ ቀን ጻድቃንን በምታስጨንቋቸው ጊዜ ወዮላችሁ! በእሳትም ታቃጥሏቸዋላችሁ፥ እናንተም እንደ ሥራችሁ ፍዳውን ትቀበላላችሁ።

31 ክፉውን ነገር ልብ ታደርጉ ዘንድ የምትተጉ ልበ ግልብጦች ወዮላችሁ! ፍራትም ያገኛችሁ ዘንድ አላችሁ፥ የሚረዳችሁም የለም።

32 ኃጥኣን፥ ወዮላችሁ! በአፋችሁ ነገር ላይና ሥራን በዘነጋችሁባቸው በእጆቻችሁ ሥራ ላይ በእሳት ወላፈን ትቃጠላላችሁና።

33 አሁንም ዕወቁ፥ መላእክት በሰማይ ከፀሐይና ከጨረቃ፥ ከከዋክብትም የተነሣ ስለ ኀጢአታችሁ ሥራችሁን ይመራመራሉና።

34 በምድር ላይ በጻድቃን ዘንድ ፍርድን ታደርጉባቸዋላችሁና ደመናውንና ጉሙን ሁሉ፥ ጠሉንና ዝናቡንም በእናንተ ያዳኝባችኋል፤ ወደ እናንተ እንዳይወርዱ ሁሉ ከእናንተ ይከለከላሉና፥ በኀጢአታችሁም አያስቡምና።

35 አሁንም ዝናብ ወደ እናንተ መውረድን እንዳይከለከል፥ ጠልም ከእናንተ ወርቅንና ብርን ተቀብሎ እንዲወርድ ለዝናም እጅ መንሻን ስጡ።

36 ውርጭና ዐመዳይ፥ የእነርሱም ቅዝቃዜ፥ የዐመዳይ ነፋሳትም ሁሉ፥ የእነርሱም ጭንቅ ሁሉ ቢወድቁባችሁ በእነዚያ ወራቶች በፊታቸው መቆም አይቻላችሁም።

Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos