ዘዳግም 21 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ባልታወቀ ሰው ስለ ተፈጸመ ግድያ 1 “አምላክህ እግዚአብሔር ትወርሳት ዘንድ በሚሰጥህ ምድር የተገደለ ሰው በሜዳ ወድቆ ቢገኝ፥ ገዳዩም ባይታወቅ፥ 2 ሽማግሌዎችህና ፈራጆችህ ወጥተው በተገደለው ሰው ዙሪያ እስካሉት ከተሞች ድረስ በስፍር ይለኩ፤ 3 ለተገደለውም ሰው አቅራቢያ የሆነች የከተማዪቱ ሽማግሌዎች ከላሞች ለሥራ ያልደረሰችውን፥ ቀንበርም ያልተጫነባትን ጊደር ይውሰዱ፤ 4 የዚያችም ከተማ ሽማግሌዎች ጊደሪቱን ይዘው ፈሳሽ ውኃ ወዳለበት ወዳልታረሰና ዘርም ወዳልተዘራበት ሽለቆ ይሄዳሉ፤ በዚያም በሸለቆው ውስጥ የጊደሪቱን ቋንጃዋን ይቈርጣሉ። 5 የሌዊ ልጆች ካህናትም ይቀርባሉ፤ በፊቱ እንዲያገለግሉ፥ በስሙም እንዲባርኩ አምላክህ እግዚአብሔር መርጦአቸዋልና፤ በእነርሱም ቃል ክርክር ሁሉ ጕዳትም ሁሉ ይቆማልና፤ 6 ወደ ተገደለው ሰው አቅራቢያ የሆነችው የከተማዪቱ ሽማግሌዎች በሸለቆው ውስጥ ቋንጃዋ በተቈረጠው ጊደር ራስ ላይ እጃቸውን ይታጠቡ፦ 7 ‘እጆቻችን ይህን ደም አላፈሰሱም፤ ዐይኖቻችንም አላዩም፤ 8 አቤቱ፥ ከግብፅ ምድር የተቤዠኸውን ሕዝብህን እስራኤልን ይቅር በል፤ በሕዝብህም በእስራኤል ላይ የንጹሑን ደም በደል አትቍጠር’ ብለው ይናገሩ፤ ስለ ደሙም ይሰረይላቸዋል። 9 አንተም በእግዚአብሔር ፊት መልካምና ጥሩ የሆነውን ባደረግህ ጊዜ የንጹሑን ደም በደል ከመካከላቸው ታርቃለህ። በጦርነት ስለ ተማረኩ ሴቶች 10 “ጠላቶችህን ልትወጋ በወጣህ ጊዜ አምላክህም እግዚአብሔር በእጅህ አሳልፎ በሰጣቸውና በማረክሃቸው ጊዜ፥ 11 በምርኮው ውስጥ የተዋበች ሴት ብታይ፥ ብትመኛትም፥ ሚስትም ልታደርጋት ብትወድድ፥ 12 ወደ ቤትህ ታመጣታለህ፤ ራስዋንም ትላጫታለህ፤ ጥፍርዋንም ትቈርጥላታለህ፤ 13 የተማረከችበትንም ልብስ ታወልቅላታለህ፤ በቤትህም ታስቀምጣታለህ፤ ስለ አባቷና ስለ እናቷ አንድ ወር ሙሉ ታለቅሳለች፤ ከዚያም በኋላ ትደርስባታለህ፤ ባልም ትሆናታለህ፤ እርስዋም ሚስት ትሆንልሃለች። 14 ከዚያም በኋላ በእርስዋ ደስ ባይልህ አርነት አውጥተህ ትለቅቃታለህ፤ በዋጋ ግን አትሸጣትም፤ አግብተሃታልና እንደባሪያ አትቍጠራት። ስለ በኵር ልጅ መብት 15 “ለአንድ ሰው አንዲቱ የተወደደች፥ አንዲቱም የተጠላች ሁለት ሚስቶች ቢኖሩት፥ ለእርሱም የተወደደችው፥ ደግሞም የተጠላችው ልጆችን ቢወልዱ፥ በኵሩም ከተጠላችው ሚስት የተወለደው ልጅ ቢሆን፥ 16 ለልጆቹ ከብቱን በሚያወርስበት ቀን ከተጠላችው ሚስት በተወለደው በበኵሩ ፊት ከተወደደችው ሚስት የተወለደውን ልጅ በኵር ያደርገው ዘንድ አይገባውም፤ 17 ነገር ግን ከከብቱ ሁለት እጥፍ ለእርሱ በመስጠት ከተጠላችው ሚስት የተወለደው ልጅ በኵር እንደ ሆነ ያስታውቅ። የኀይሉ መጀመሪያ ነውና በኵርነቱ የእርሱ ነው። ስለማይታዘዙ ልጆች 18 “ማንም ሰው ለአባቱ ቃልና ለእናቱ ቃል የማይታዘዝ፥ ቢገሥጹትም የማይሰማቸው ትዕቢተኛና ዐመፀኛ ልጅ ቢኖረው፥ 19 አባቱና እናቱ ይዘው ወደ ከተማዉ ሽማግሌዎች፥ ወደሚኖርበትም ስፍራ በር ይውሰዱት፤ 20 የከተማዉንም ሰዎች፦ ‘ይህ ልጃችን ትዕቢተኛና ዐመፀኛ ነው፥ ቃላችንንም አይሰማም፤ ስስታምና ሰካራም ነው’ ይበሉአቸው። 21 የከተማዉም ሰዎች ሁሉ በድንጋይ ደብድበው ይግደሉት፤ እንዲህም ክፉውን ነገር ከመካከልህ ታርቃለህ፤ እስራኤልም ሁሉ ሰምተው ይፈራሉ። ልዩ ልዩ ሕጎች 22 “ማንም ሰው ለሞት የሚያበቃውን ኀጢአት ቢሠራ፥ እንዲሞትም ቢፈረድበት፥ በእንጨትም ላይ ብትሰቅለው፥ 23 በእንጨት ላይ የተሰቀለ በእግዚአብሔር ዘንድ የተረገመ ነውና ሥጋው በእንጨት ላይ አይደር፤ ነገር ግን አምላክህ እግዚአብሔር ርስት አድርጎ የሰጠህን ምድር እንዳታረክስ በእርግጥ በዚያው ቀን ቅበረው። |