Este libro no es inspirado por Dios y no forma parte del canon cristiano ni del Tanaj judío. Se muestra solo con fines históricos y de estudio. Ver explicación completa ተረፈ ባሮክ 1 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ተረፈ ባሮክ 1 ኤርምያስም ጳስኮርን እንዲህ አለው፥ “እናንተስ በዘመናችሁ ሁሉ ከአባቶቻችሁና ከእናንተ በኋላ ከሚመጡ ልጆቻችሁ ጋር ጽድቅን ትቃረኗታላችሁ። 2 እነርሱስ ከአባቶቻችሁ ይልቅ እጅግ የተናቀች ኀጢአትን ሠሩ። እነርሱም ዋጋ የማይገኝለትን ይሸጡታል፤ ሕማማትን የሚያስወግደውን እንዲታመም ያደርጉታል፤ ኀጢአትን የሚያስተሰርየውንም ይፈርዱበታል። 3 የእስራኤል ልጆች የተስማሙበትን የክቡሩን ዋጋ ሠላሳ ብር ይቀበላሉ፤ ያንም ብር ለሸክላ ሠሪ ቦታ ዋጋ አድርገው ይሰጡታል። 4 እዚአብሔርም እንዳዘዘኝ እንዲሁ እናገራለሁ። 5 ስለዚህ ንጹሕ ደምን ፈርደው አፍስሰዋልና ፍርድና ጥፋት በእነርሱ ላይ፥ ከእነርሱም በኋላ በልጆቻቸው ላይ ይወርድባቸዋል፤” 6 ወደ ባቢሎን በተማረኩ ጊዜ ስውር ያልሆነ ባሮክ ከተናገረው ነገር የቀረ ይህ ነው። 7 እንዲህም ሆነ፤ የከለዳውያን ንጉሥ የእስራኤልን ልጆች በማረካቸው ጊዜ እግዚአብሔር ኤርምያስን ተናገረው። 8 እንዲህም አለው፥ “ወዳጄ ኤርምያስ ሆይ፥ ከዚህች ከተማ ውጣ፤ ከሚኖሩባት ሰዎች ኀጢአት ብዛት የተነሣ አጠፋታለሁና አንተና ባሮክ ውጡ። 9 ልመናህ በከተማዪቱ መካከል እንደ ጽኑ ምሰሶ፥ በዙሪያዋም እንደ አድማስ ቅጥር ነውና፤ አሁንም የከለዳውያን ሠራዊት ሳይመጣና ሀገሪቱን ሳይከባት ተነሥታችሁ ሂዱ፥ ውጡም።” 10 ኤርምያስም እንዲህ ሲል ተናገረ፥ “ጌታዬ ሆይ፥ እለምንሃለሁ፤ በፊትህ ይናገር ዘንድ ባሪያህን እዘዘው።” 11 እግዚአብሔርም፥ “ወዳጄ ኤርምያስ ሆይ! ተናገር” አለው። 12 ኤርምያስም እንዲህ ሲል ተናገረ፥ “ሁሉን የምትገዛ አቤቱ፥ ንጉሡ ከሠራዊቱ ጋር ይታበይና በአምላክ ከተማ በረታሁባት ይል ዘንድ የመረጥኻትን ይህቺን ከተማ በከለዳውያን እጅ አሳልፈህ ትሰጣለህን? 13 አቤቱ፥ ይህ አይሁን፤ ከወደድህም በእጅህ አጥፋት።” 14 እግዚአብሔርም ኤርምያስን አለው፥ “በሚኖሩባት ሰዎች ኀጢአት አጠፋታለሁና አንተ ወዳጄ ስለ ሆንህ ባሮክና አንተ ተነሥታችሁ ውጡ። 15 እኔ አስቀድሜ በሮችዋን ካልከፈትሁ ንጉሡና ሠራዊቱ ወደ ሀገሪቱ መግባት አይቻላቸውም። 16 አሁንም ተነሥተህ ወደ ባሮክ ሂድ፤ ይህንም ነገር ሁሉ ንገረው፤ ከሌሊቱ ስድስት ሰዓት በሆነ ጊዜ ተነሥታችሁ ወደ ከተማዪቱ ቅጥር ኑ። 17 እኔ አሳያችኋለሁ፤ እኔም አስቀድሜ ከተማዪቱን ካላጠፋኋት ወደ እርስዋ መግባት አይችሉም።” 18 ጌታም ይህን ተናግሮ ከኤርምያስ ዘንድ ሄደ። 19 ያንጊዜም ኤርምያስ ልብሱን ቀደደ፤ በራሱም ላይ ትቢያ ነሰነሰ፤ ወደ ቤተ መቅደስም ገባ። 20 ባሮክም ኤርምያስን በራሱ ላይ ትቢያ ነስንሶ፥ ልብሶቹንም ቀድዶ ባየው ጊዜ፥ “አባቴ ኤርምያስ ሆይ፥ ምን ሆንህ? ሕዝቡስ ምን ኀጢአት ሠሩ?” ብሎ ቃሉን አሰምቶ ጮኸ። 21 ሕዝቡ በሳቱ ጊዜ ኤርምያስ ያዝን ነበርና፥ በራሱም ትቢያ ይነሰንስ ነበርና፥ የሕዝቡም በደላቸው እስኪሰረይላቸው ድረስ ለሕዝቡ ይጸልይላቸው ነበርና። 22 ባሮክም፥ “አባቴ ኤርምያስ ሆይ፥ ምን ሆንህ?” ብሎ ጠየቀው። ኤርምያስም እንዲህ አለው፥ “ልቡናችንን እንቅደድ እንጂ ልብሶቻችንን እንዳንቀድ ተጠበቅ” አለው። 23 “ከዛሬ ጀምሮ እነዚህን ወገኖች ይቅር አይሏቸውምና እንባን እስክንመላቸው ድረስ በሚገባ እናለቅስ ዘንድ ወደ ጕድጓዶች ውኃን አንጨምር” አለው። 24 ባሮክም፥ “አባቴ ኤርምያስ ሆይ፥ ምን ሆንህ?” አለ። 25 ኤርምያስም፥ “አምላክ ከተማዋን በከላውዴዎን ንጉሥ እጅ አሳልፎ ይሰጣታልና፥ ሕዝቡንም በክፉ ነገር ይማርካቸዋልና ነው፤” አለው። 26 ባሮክም ይህን ሁሉ ነገር ሰምቶ ልብሶቹን ቀደደና፥ “አባቴ ኤርምያስ ሆይ፥ ምን ላኩብህ?” አለው። 27 ኤርምያስም፥ “ነገሩን በእውነት ታውቅ ዘንድ ከሌሊቱ እስከ ስድስት ሰዓት ድረስ ከእኔ ጋር ቈይ” አለው። 28 በቤተ መቅደስም እያለቀሱ ተቀመጡ፤ ከሌሊቱም ስድስት ሰዓት በሆነ ጊዜ እግዚአብሔር ኤርምያስን ይወጣ ዘንድ ነገረው። 29 ከባሮክም ጋር ወጣ፤ ወደ ቅጽሩም ደረሱ፤ እየጸለዩም ተቀመጡ። 30 የመለከት ድምፅም ተሰማ፤ መላእክትም ከሰማያት መጡ፤ በእጃቸውም የእሳት መብራት ይዘው በቅጥሯ ቆመው ነበር። |