2 ሳሙኤል 19 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ኢዮአብ ዳዊትን እንደ ወቀሰው 1 ለኢዮአብ፥ “ንጉሡ ስለ አቤሴሎም ያዝናል፤ ያለቅሳልም” ብለው ነገሩት። 2 በዚያም ቀን፥ “ንጉሡ ስለ ልጁ አዘነ” ሲባል ሕዝቡ ሰምቶአልና በዚያው ቀን ሕይወት በሕዝቡ ሁሉ ዘንድ ወደ ኀዘን ተለወጠ። 3 ከሰልፍ በሸሸ ጊዜ ያፈረ ሕዝብ ተሰርቆ እንደሚገባ በዚያ ቀን ሕዝቡ ተሰርቀው ወደ ከተማ ገቡ። 4 ንጉሡም ፊቱን ሸፈነ፤ ንጉሡም በታላቅ ድምፅ፥ “ልጄ አቤሴሎም፥ አቤሴሎም፥ ልጄ” እያለ ይጮህ ነበር። 5 ኢዮአብም ወደ ንጉሡ ወደ ቤት ገብቶ እንዲህ አለ፥ “ዛሬ ነፍስህንና የወንዶችንና የሴቶች ልጆችህን ነፍስ፥ የሚስቶችህንና የቁባቶችህን ነፍስ ያዳኑትን የአገልጋዮችህን ሁሉ ፊት በዚች ቀን አሳፍረሃል። 6 አንተ የሚጠሉህን ትወድዳለህ፤ የሚወድዱህንም ትጠላለህ፤ አለቆችህና አገልጋዮችህ እንደማይጠቅሙህ እንደምታስብ ዛሬ ገልጠሃልና፤ አቤሴሎምም ድኖ ቢሆን ዛሬ እኛ ሁላችን እንሞት እንደ ነበር አውቃለሁ። ይህ በፊትህ ላንተ ቀና ነበረና። 7 አሁንም ተነሥተህ ወጥተህ ለአገልጋዮችህ በልባቸው የሚገባ ነገር ንገራቸው። ዛሬ ወደ እነርሱ ካልወጣህ በዚች ሌሊት አንድ ሰው ስንኳ ከአንተ ጋር የሚያድር እንዳይኖር በእግዚአብሔር እምላለሁ፤ ከሕፃንነትህ ጀምሮ እስከዚች ቀን ድረስ ካገኘህ መከራ ሁሉ ዛሬ የምታገኝህ መከራ እንድትከፋብህ እንግዲህ አንተ ለራስህ ዕወቅ” አለው። 8 ንጉሡም ተነሥቶ በበሩ ተቀመጠ፤ ሕዝቡም ሁሉ ንጉሡ በበሩ ተቀምጧል ብለው ተናገሩ፤ ሕዝቡም ሁሉ በበሩ ወደ ንጉሡ ፊት ወጡ። እስራኤልም እያንዳንዱ ወደ ድንኳኑ ሸሽቶ ገብቶ ነበር። ዳዊት ወደ ኢየሩሳሌም እንደ ተመለሰ 9 ከመላው ነገደ እስራኤል የተሰበሰቡ ሕዝብ፥ “ንጉሡ ዳዊት ከጠላቶቻችን እጅ ታድጎናል፥ ከፍልስጥኤማውያንም እጅ አድኖናል፤ አሁንም ስለ አቤሴሎም ከሀገሩና ከመንግሥቱ ሸሸ። 10 በላያችን ላይ የቀባነው አቤሴሎምም በጦርነት ሞቶአል፤ አሁንም ንጉሡን ለመመለስ ስለምን ዝም ትላላችሁ?” አሉ፤ የእስራኤልም ቃል ወደ ንጉሥ ደረሰ። 11 ንጉሡ ዳዊትም ለካህናቱ ለሳዶቅና ለአብያታር ልኮ እንዲህ አላቸው፥ “ለይሁዳ ሽማግሌዎች እንዲህ ብላችሁ ተናገሩአቸው፦ የእስራኤል ሁሉ ነገር ወደ ንጉሡ ደርሶአልና ንጉሡን ወደ ቤቱ ከመመለስ ስለምን ዘገያችሁ? 12 እናንተ ወንድሞች፥ የአጥንቴ ፍላጭና የሥጋዬ ቍራጭ ናችሁ፤ እናንተ ንጉሡን ወደ ቤቱ ከመመለስ ስለምን ዘገያችሁ? 13 ለአሚሳይም፦ አንተ የአጥንቴ ፍላጭና የሥጋዬ ቍራጭ አይደለህምን? በዘመንህም ሁሉ በኢዮአብ ፋንታ በፊቴ የሠራዊት አለቃ ሳትሆን ብትቀር ዛሬ እግዚአብሔር ይህን ያድርግብኝ፤ ይህንም ይጨምርብኝ በሉት።” 14 የይሁዳንም ሰዎች ሁሉ ልብ እንደ አንድ ሰው ልብ አድርጎ አዘነበለ፤ ወደ ንጉሡም፥ “አንተና ብላቴኖችህ፥ አገልጋዮችህም ሁሉ ተመለሱ” ብለው ላኩበት። 15 ንጉሡም ተመልሶ እስከ ዮርዳኖስ ድረስ መጣ። የይሁዳ ሰዎችም ንጉሡን ሊቀበሉ፥ ንጉሡንም ዮርዳኖስን ሊያሻግሩ ወደ ጌልገላ መጡ። 16 ከባውሪም ሀገር የነበረው የኢያሚን ልጅ የጌራ ልጅ ሳሚም ከይሁዳ ሰዎች ጋር ንጉሥ ዳዊትን ሊቀበል ፈጥኖ ወረደ። 17 ከእርሱም ጋራ ከብንያም ወገን የሆኑ ሺህ ሰዎች ነበሩ፤ የሳኦልም ቤት አገልጋይ ሲባ ከእርሱም ጋር ዐሥራ አምስቱ ልጆቹና ሃያው አገልጋዮቹ ነበሩ፤ በንጉሡም ፊት በቀጥታ ወደ ዮርዳኖስ ሄዱ። 18 ንጉሡንም የማሻገር ሥራ ሠሩ። የንጉሡንም ቤተ ሰብእ ያነሡ ዘንድ፥ በፊቱም የቀና ሥራን ይሠሩ ዘንድ ወደ ማዶ ተሻገሩ። ንጉሡም ዮርዳኖስን ከተሻገረ በኋላ የጌራ ልጅ ሳሚ በንጉሡ ፊት፦ በግንባሩ ወደቀ። ዳዊት ለሳሚ ይቅርታ እንደ አደረገለት 19 እርሱም ንጉሡን አለው፥ “ጌታዬ! ኀጢአቴን አትቍጠርብኝ፤ ጌታዬ ንጉሡ ከኢየሩሳሌም በወጣህ ቀን ባሪያህ የበደልሁህን አታስብብኝ፤ ጌታዬ ንጉሡም በልብህ አታኑርብኝ። 20 እኔ አገልጋይህ በደለኛ እንደ ሆንሁ አውቄአለሁና እነሆ፥ ከዮሴፍ ቤት ሁሉ አስቀድሜ ዛሬ መጣሁ፤ ጌታዬንም ንጉሡን ልቀበል ወረድሁ።” 21 የሶርህያ ልጅ አቢሳ ግን፥ “ሳሚ እግዚአብሔር የቀባውን ሰድቦአልና እንግዲህ ሞት የተገባው አይደለምን?” ብሎ መለሰ። 22 ዳዊትም፥ “እናንተ የሶርህያ ልጆች! ዛሬ ታስቱኝ ዘንድ በእኔና በእናንተ መካከል ምን አለኝ? ዛሬስ ከእስራኤል የሚሞት አንድ ሰው የለም። ዛሬስ በእስራኤል ላይ እንደ ነገሥሁ አላውቅምን?” 23 ንጉሡም ሳሚን፥ “አትሞትም” አለው። ንጉሡም ማለለት። ዳዊት ለሜምፌቡስቴ ይቅርታ እንደ አደረገለት 24 የሳኦልም የልጅ ልጅ ሜምፌቡስቴ ንጉሡን ሊቀበል ወረደ፤ ንጉሡም ከሄደበት ቀን ጀምሮ በሰላም እስከ ተመለሰበት ቀን ድረስ እግሩን አላነጻም፤ ጥፍሩንም አልቈረጠም፤ ጢሙንም አልላጨም፤ ልብሱንም አላጠበም ነበር። 25 ከዚህም በኋላ ንጉሡን ሊቀበለው ከኢየሩሳሌም በመጣ ጊዜ ንጉሡ፥ “ሜምፌቡስቴ፥ ከእኔ ጋር ስለምን አልወጣህም?” አለው። 26 ሜምፌቡስቴም አለ፥ “ጌታዬ፥ ንጉሥ፥ አገልጋዬ አታለለኝ፥ እኔ ባሪያህ አንካሳ ነኝና፦ ከንጉሡ ጋር እሄድ ዘንድ አህያዬን ጫንልኝ፤ እኔም እቀመጥበታለሁ አልሁት። 27 እርሱም በእኔ በባሪያህ ላይ ክፉ አደረገ፤ አንተ ጌታዬ ንጉሥ ግን እንደ እግዚአብሔር መልአክ ነህ፤ በፊትህም ደስ ያሰኘህን አድርግ። 28 የአባቴ ቤት ሁሉ በጌታዬ በንጉሥ ዘንድ ሞት የሚገባቸው ነበሩ፤ አንተ ግን እኔን ባሪያህን በገበታህ በሚበሉ መካከል አስቀመጥኸኝ፤ ለንጉሥ ደግሞ ለመናገር ምን መብት አለኝ?” 29 ንጉሡም፥ “ነገርህን ለምን ታበዛለህ? አንተና ሲባ የሳኦልን እርሻውን ትካፈሉ ዘንድ ብያለሁ” አለው። 30 ሜምፌቡስቴም ንጉሡን፥ “ጌታዬ ንጉሡ በደኅና ወደ ቤቱ ከተመለሰ እርሱ ሁሉን ይውሰደው” አለው። 31 ገለዓዳዊውም ቤርዜሊ ከሮግሊም ወረደ፤ በዮርዳኖስም ሊሸኘው ከንጉሡ ጋር ዮርዳኖስን ተሻገረ። 32 ቤርዜሊም እጅግ ያረጀ የሰማንያ ዓመት ሽማግሌ ነበረ፤ እጅግም ትልቅ ሰው ነበረና ንጉሡ በመናሄም ሳለ ይቀልበው ነበር። 33 ንጉሡም ቤርዜሊን፥ “አንተ ከእኔ ጋር ዮርዳኖስን ትሻገራለህ፤ በኢየሩሳሌምም ያረጀ ሰውነትህን ከእኔ ጋር እጦረዋለሁ” አለው። 34 ቤርዜሊም ንጉሡን አለው፥ “ከንጉሡ ጋር ወደ ኢየሩሳሌም እወጣ ዘንድ ከሕይወቴ ዘመን ምን ያህል ቀረኝ? 35 ዛሬ የሰማንያ ዓመት ሽማግሌ ነኝ፥ መልካሙንና ክፉውን መለየት እችላለሁን? እኔ ባሪያህ የምበላውንና የምጠጣውን ጣዕሙን መለየት እችላለሁን? የወንዱንና የሴቲቱን ዘፈን ድምፅ መስማትስ እችላለሁን? እኔ ባሪያህ በጌታዬ በንጉሡ ላይ ለምን እከብድብሃለሁ? 36 እኔ ባሪያህ ዮርዳኖስን ተሻግሬ ከንጉሡ ጋር ጥቂት ልሄድ ነበር፤ ንጉሡ እንዲህ ያለ ወረታ ለምን ይመልስልኛል? 37 እኔ ባሪያህ ተመልሼ በከተማዬ በአባቴና በእናቴ መቃብር አጠገብ እባክህ! ልሙት፤ ነገር ግን ባሪያህ ከመዓም ከጌታዬ ከንጉሡ ጋር ይሻገር፤ በዐይኖችህ ፊት ደስ የሚያሰኝህንም ለእርሱ አድርግ።” 38 ንጉሡም፥ “ከመዓም ከእኔ ጋር ይሻገር፤ በፊቴ ደስ የሚያሰኘኝንም አደርግለታለሁ፤ አንተም ከእኔ የምትሻውን ነገር ሁሉ አደርግልሃለሁ” አለው። 39 ሕዝቡም ሁሉ ዮርዳኖስን ተሻገሩ፤ ንጉሡም ዮርዳኖስን ተሻገረ፤ ንጉሡም ቤርዜሊን አቅፎ ሳመው፤ መረቀውም፤ ወደ ስፍራውም ተመለሰ። 40 ንጉሡም ወደ ጌልገላ ተሻገረ፤ ከመዓምም ከእርሱ ጋር ተሻገረ፤ የይሁዳም ሕዝብ ሁሉ፥ ደግሞም የእስራኤል ሕዝብ እኩሌታ ከንጉሡ ጋር ተሻገሩ። 41 እነሆም፥ የእስራኤል ሰዎች ሁሉ ወደ ንጉሡ መጡ፤ ንጉሡንም፥ “ወንድሞቻችን የይሁዳ ሰዎች ለምን ሰረቁህ? ንጉሡንም ቤተ ሰቡንም ዮርዳኖስን አሻገሩ። የዳዊትም ሰዎች ሁሉ ከእርሱ ጋር ነበሩ” አሉት። 42 የይሁዳም ሰዎች ሁሉ ለእስራኤል ሰዎች መልሰው፥ “ንጉሡ ለእኛ ቅርባችን ነው፤ ስለምን በዚህ ነገር ትቈጣላችሁ? በውኑ ከንጉሡ አንዳች በልተናልን? ወይስ እርሱ በረከት ሰጥቶናልን? ወይስ ጭፍራ አድርጎ ሾመንን?” አሉ። 43 የእስራኤልም ሰዎች ለይሁዳ ሰዎች መልሰው፥ “በንጉሡ ዘንድ ለእኛ ዐሥር ክፍል አለን፤ ከእናንተም እኛ እንቀድማለን፤ እኛም በኵር ነን፤ ለዳዊትም ከእናንተ እኛ እንቀርባለን፤ ስለምን ናቃችሁን? ንጉሡንስ እንመልሰው ዘንድ ከእናንተ የእኛ ቃል አይቀድምምን?” አሏቸው። የይሁዳም ሰዎች ቃል ከእስራኤል ሰዎች ቃል ይልቅ ጠነከረ። |