2 ሳሙኤል 17 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)የኩሲ ምክር የአኪጦፌልን ምክር እንደ አስለወጠ 1 አኪጦፌልም አቤሴሎምን አለው፥ “ዐሥራ ሁለት ሺህ ሰዎች ልምረጥና በዚህች ሌሊት ተነሥቼ ዳዊትን ላሳድድ። 2 ደክሞና እጁ ዝሎ ሳለ እወድቅበታለሁ፤ አስፈራውማለሁ፤ ከእርሱም ጋር ያለው ሕዝብ ሁሉ ይሸሻል፤ ንጉሡንም ብቻውን እገድለዋለሁ፤ 3 ሙሽራ ወደ ባልዋ እንደምትመለስ ሕዝቡን ሁሉ ወደ አንተ እመልሰዋለሁ፤ የአንድ ሰው ሰውነትን ብቻ ትሻለህና፤ ለሕዝቡ ሁሉ ግን ሰላም ይሆናል፤” 4 ነገሩም በአቤሴሎም ፊትና በእስራኤል ሽማግሌዎች ፊት ደስ አሰኘ። 5 አቤሴሎምም፥ “አርካዊውን ኩሲን ጥሩት፤ ደግሞም እርሱ የሚለውን እንስማ” አለ። 6 ኩሲም ወደ አቤሴሎም በመጣ ጊዜ አቤሴሎም፥ “አኪጦፌል ያለው ይህ ነው፤ ነገሩን እናደርገው ዘንድ ይገባልን? ባይሆን ግን አንተ ንገረን” ብሎ ተናገረው። 7 ኩሲም አቤሴሎምን አለው፥ “አኪጦፌል በዚህ ጊዜ የመከራት ምክር መልካም አይደለችም። ይችውም አንዲት ናት።” 8 ኩሲ ደግሞ አለ፥ “በሜዳ እንዳለች አራስ ድብና እንደ ተኳር የዱር እሪያ በልባቸው መራሮችና ኀያላን መሆናቸውን አባትህንና ሰዎቹን ታውቃለህ፤ አባትህ አርበኛ ነው፤ ሕዝቡንም አያሰናብትም። 9 በተራራው ላይ፥ ያም ባይሆን በአንድ ቦታ ተሰውሮአልና ከእነርሱ ፊተኞቹ ቢወድቁ የሚሰማው ሁሉ አቤሴሎምን የተከተለ ሕዝብ ተመታ ይላል። 10 እርሱ ኀይለኛ ሰው ነውና፥ ልቡም እንደ አንበሳ ልብ ፈጽሞ ይናደዳልና፤ እስራኤልም ሁሉ አባትህ ጽኑዕ፥ ከእርሱም ጋር ያሉት ስዎች ኀያላን እንደ ሆኑ ያውቃሉ። 11 እኔ እንዲህ እመክርሃለሁ፤ ከዳን እስከ ቤርሳቤህ ያሉ እስራኤል ሁሉ ብዛታቸው እንደ ባሕር አሸዋ ሆኖ ወደ አንተ ይሰብሰቡ፤ አንተም በመካከላቸው ትሄዳለህ። 12 እርሱንም ወደምናገኝበት ወደ አንድ ስፍራ እንደርስበታለን፤ ጠልም በምድር ላይ እንደሚወድቅ እንወርድበታለን፤ እርሱንና ከእርሱም ጋር ያሉ ሰዎችን ሁሉ አንድ ስንኳ አናስቀርም። 13 ወደ ከተማም ቢገባ እስራኤል ሁሉ ወደዚያች ከተማ ገመድ ይወስዳሉ፤ እኛም አንድ ድንጋይ እንኳን እስከማይገኝባት ድረስ ወደ ወንዙ ውስጥ እንስባታለን።” 14 አቤሴሎምና የእስራኤልም ሰዎች ሁሉ “የአርካዊው የኩሲ ምክር ከአኪጢፌል ምክር ይሻላል” አሉ። እግዚአብሔርም በአቤሴሎም ላይ ክፉ ያመጣ ዘንድ እግዚአብሔር መልካሚቱን የአኪጦፌልን ምክር እንዲበትን አዘዘ። ኩሲ ዳዊትን እንደ አስጠነቀቀው 15 አርካዊው ኩሲም ለካህናቱ ለሳዶቅና ለአብያታር፥ “አኪጦፌል ለአቤሴሎምና ለእስራኤል ሽማግሌዎች እንዲህና እንዲህ መክሮአል፤ እኔ ግን እንዲህና እንዲያ መክሬአለሁ። 16 አሁን እንግዲህ ንጉሡና ከእርሱ ጋር ያለው ሕዝብ ሁሉ እንዳይዋጡ፥ ሳትዘገይ ዮርዳኖስን ተሻገር እንጂ በዚህች ሌሊት በምድረ በዳ ውስጥ በሜዳው አትደር ብለው ለዳዊት ይነግሩት ዘንድ ፈጥናችሁ ላኩ” አላቸው። 17 ዮናታንና አኪማሆስም በሮጌል ምንጭ አጠገብ ቆመው ሳለ አንዲት ብላቴና ሄዳ ነገረቻቸው፤ ወደ ከተማ መግባት አልተቻላቸውም ነበርና፤ እነርሱም ሄደው ለንጉሡ ለዳዊት ነገሩት። 18 አንድ ብላቴናም አይቶ ለአቤሴሎም ነገረው፤ እነርሱ ግን ፈጥነው ሄዱ፤ ወደ ባውሪምም ወደ አንድ ሰው ቤት መጡ፤ በግቢውም ውስጥ ጕድጓድ ነበረው፤ ወደዚያም ውስጥ ወረዱ፤ 19 ሴቲቱም ዳውጃ ወስዳ በጕድጓዱ አፍ ላይ ዘረጋችበት፤ የተፈተገ እህልም በላዩ አሰጣችበት፤ ያወቃቸውም የለም። 20 የአቤሴሎምም አገልጋዮች ወደ ሴቲቱ ወደ ቤት መጥተው፥ “አኪማሆስና ዮናታን የት አሉ?” አሉ፤ ሴቲቱም፥ “ፈፋውን ተሻግረው ሄዱ፤ ጥቂትም ቀደሙአችሁ” አለቻቸው። እነርሱም ፈልገው አጡአቸው፤ ወደ ኢየሩሳሌምም ተመለሱ። 21 ከሄዱም በኋላ እነርሱ ከጕድጓዱ ወጥተው ሄዱ፤ ለንጉሡም ለዳዊት ነገሩት፤ ዳዊትንም፥ “አኪጦፌል በእናንተ ላይ እንዲህ መክሮአልና ተነሡ፤ ፈጥናችሁም ውኃውን ተሻገሩ” አሉት። 22 ዳዊትና ከእርሱም ጋር የነበሩት ሁሉ ተነሥተው ዮርዳኖስን ተሻገሩ፤ እስኪነጋም ድረስ ዮርዳኖስን ሳይሻገር አንድ ሰው እንኳን አልቀረም። 23 አኪጦፌልም ምክሩ እንዳልሠራ ባየ ጊዜ አህያውን ጫነ፤ ተነሥቶም ወደ ቤቱ ወደ ከተማው ሄደ፤ ቤቱንም አደራጅቶ በገዛ እጁ ታንቆ ሞተ፤ በአባቱም መቃብር ተቀበረ። 24 ዳዊትም ወደ ምናሄም መጣ፤ አቤሴሎምም፥ ከእርሱ ጋር የእስራኤል ሰዎች ሁሉ ዮርዳኖስን ተሻገሩ። 25 አቤሴሎምም በሠራዊቱ ላይ በኢዮአብ ስፍራ አሜሳይን ሾመ፤ አሜሳይም የኢዮአብን እናት የሶርህያን እኅት የነዓሶንን ልጅ አቢግያን የአገባው የኢይዝራኤላዊው የዮቶር ልጅ ነበር። 26 እስራኤልና አቤሴሎምም በገለዓድ ምድር ሰፈሩ። 27 ዳዊትም ወደ ምናሄም በመጣ ጊዜ በአሞን ልጆች ሀገር በአራቦት የነበረ የነዓሶን ልጅ ኡኤሴብ፥ የሎዶባርም ሰው የአሜሄል ልጅ ማኪር፥ የሮጌሌምም ሰው ገለዓዳዊው ቤርዜሊ፥ 28 ዐሥር አልጋዎችና ምንጣፎች፥ ዐሥርም ጋኖችና ፊቀኖች፥ የስንዴና የገብስ ዱቄት፥ ስልቅ አተርና ምስር፥ 29 ማርና ቅቤ፥ በግና ላም ይበሉ ዘንድ ለዳዊትና ከእርሱ ጋር ላሉ ሰዎች አመጡ። ሕዝቡ በምድረ በዳ ተርበውና ተጠምተው ደክመው ነበርና። |