2 ነገሥት 25 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)የኢየሩሳሌም በባቢሎናውያን እጅ መውደቅ ( 2ዜ.መ. 36፥13-21 ፤ ኤር. 52፥3-11 ) 1 ሴዴቅያስም በነገሠ በዘጠነኛው ዓመት በዐሥረኛው ወር ከወሩም በዐሥረኛው ቀን የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር ከሠራዊቱ ሁሉ ጋር ወደ ኢየሩሳሌም መጥቶ ሰፈረባት፤ በዙሪያዋም ዕርድ ሠራባት። 2 ከተማዪቱም እስከ ንጉሡ እስከ ሴዴቅያስ ዐሥራ አንደኛው ዓመተ መንግሥት እስከ አራተኛው ወር እስከ ዘጠነኛው ቀን ድረስ ተከብባ ነበር። 3 በከተማዪቱም ራብ ጸንቶ ነበርና ለሀገሩ ሰዎች እህል ታጣ። 4 ከተማዪቱም ተሰበረች፤ ሰልፈኞችም ሁሉ በሁለት ቅጥር መካከል ባለው በር ወደ ንጉሡ አትክልት በሚወስደው መንገድ በሌሊት ሸሹ፤ ከለዳውያንም በከተማዪቱ ዙሪያ ነበሩ፤ ወደ ምድረ በዳ በሚወስደውም መንገድ ሄዱ። 5 የከለዳውያንም ሠራዊት ንጉሡን ተከተሉ፤ በኢያሪኮም በኩል ባለው ሜዳ ያዙት፤ ሠራዊቱም ሁሉ ከእርሱ ተለይተው ተበትነው ነበር። 6 ንጉሡንም ይዘው የባቢሎን ንጉሥ ወዳለበት የኢየሩሳሌም ክፍል ወደምትሆን ወደ ዴብላታ ወሰዱት፤ ፍርድም ፈረዱበት። 7 የሴዴቅያስንም ልጆች በፊቱ ገደሉአቸው፤ የሴዴቅያስንም ዐይኖች አወጡ፤ በሰንሰለትም አሰሩት፤ ወደ ባቢሎንም ወሰዱት። 8 በባቢሎንም ንጉሥ በናቡከደነፆር በዐሥራ ዘጠነኛው ዓመት በአምስተኛው ወር ከወሩም በሰባተኛው ቀን በባቢሎን ንጉሥ ፊት የሚቆመው የአበዛዎች አለቃ ናቡዛርዳን ወደ ኢየሩሳሌም ወጣ። 9 የንጉሡም የአበዛዎች አለቃ የእግዚአብሔርን ቤትና የንጉሡን ቤት አቃጠለ። የኢየሩሳሌምንም ቤቶች ሁሉ በእሳት አቃጠለ። 10 የከለዳውያን ሠራዊት ሁሉ የኢየሩሳሌምን የአንባዋን ቅጥር ዙሪያዋን አፈረሱ። 11 የአበዛዎች አለቃ ናቡዛርዳንም በከተማዪቱ ውስጥ የቀረውን ሕዝብ፥ ሸሽተውም ወደ ባቢሎን ንጉሥ የተጠጉትን፥ የቀሩትንም ሕዝብ ሁሉ ማርኮ ወሰደ። 12 የአበዛዎችም አለቃ ከሀገሩ ድሆች ወይን ተካዮችና አራሾች እንዲሆኑ አስቀረ። 13 ከለዳውያንም በእግዚአብሔር ቤት ውስጥ የነበሩትን የናስ ዓምዶች፥ በእግዚአብሔርም ቤት የነበሩትን መቀመጫዎችና የናስ ኵሬዎች ሰባበሩ፤ ናሱንም ወደ ባቢሎን ወሰዱ። 14 ምንቸቶቹንና ማንካዎቹንም፥ መኰስተሪያዎቹንና ጭልፋዎቹንም የሚያገለግሉበትንም የናስ ዕቃ ሁሉ ወሰዱ። 15 የአበዛዎች አለቃም ጥናዎቹን ከወርቅና ከብር የተሠሩ መኰስተሪያዎችንም ወሰደ። 16 ሰሎሞንም ለእግዚአብሔር ቤት የሠራቸውን ሁለቱን ዓምዶች፥ አንዱንም ኵሬ መቀመጫዎቹንም ወሰደ፤ ለእነዚህም ዕቃዎች ሁሉ ናስ ሚዛን አልነበረውም። 17 የአንዱም ዓምድ ቁመት ዐሥራ ስምንት ክንድ ነበረ፥ የናስም ጕልላት ነበረበት፤ የጕልላቱም ርዝመት ሦስት ክንድ ነበረ፥ በጕልላቱም ላይ በዙሪያው የናስ መርበብና ሮማኖች ነበሩ፤ እንዲሁም ደግሞ በሁለተኛው ዓምድ ላይ መርበብ ነበረበት። የይሁዳ ሕዝብ ወደ ባቢሎን መማረክ ( ኤር. 52፥24-27 ) 18 የአበዛዎችም አለቃ ታላቁን ካህን ሠራያን ሁለተኛውንም ካህን ሶፎንያስን ሦስቱንም በረኞች ማርኮ ወሰደ። 19 ከከተማዪቱም በሰልፈኞች ላይ ተሾመው ከነበሩት አንዱን ጃንደረባ፥ በከተማዪቱም የተገኙትን በንጉሡ ፊት የሚቆሙትን አምስቱን ሰዎች፥ የሀገሩንም ሕዝብ የሚያሰልፍ የሠራዊቱን አለቃ ጸሓፊ፥ በከተማዪቱም ከተገኙት ከሀገሩ ሕዝብ ስድሳ ሰዎችን ወሰደ። 20 የአበዛዎቹም አለቃ ናቡዛርዳን ማርኮ የባቢሎን ንጉሥ ወዳለበት ወደ ዴብላታ አመጣቸው። 21 የባቢሎንም ንጉሥ መታቸው፥ በኤማትም ምድር ባለችው በዴብላታ ገደላቸው። እንዲሁም ይሁዳ ከሀገሩ ተማረከ። ጎዶልያ የይሁዳ ገዥ መሆኑ ( ኤር. 40፥7-9 ፤ 41፥1-3 ) 22 የባቢሎንም ንጉሥ ናቡከደነፆር በይሁዳ ምድር በቀረው ሕዝብ ላይ የሳፋንን ልጅ የአኪቃምን ልጅ ጎዶልያን ሾመው። 23 የሠራዊቱም አለቆች ሁሉ ሰዎቻቸውም፥ የናታንዩ ልጅ እስማኤል፥ የቃሬያን ልጅ ዮሐናን፥ የነጦፋዊውም የተንሑሜት ልጅ ሴሪያ፥ የማዕካታዊው ልጅ አዛንያ፥ ሰዎቻቸውም የባቢሎን ንጉሥ ጎዶልያን እንደ ሾመው በሰሙ ጊዜ ወደ ጎዶልያ ወደ መሴፋ መጡ። 24 ጎዶልያም፥ “ከከለዳውያን ሎሌዎች የተነሣ አትፍሩ፤ በሀገሩ ተቀመጡ፤ ለባቢሎንም ንጉሥ ተገዙ፤ መልካምም ይሆንላችኋል” ብሎ ለእነርሱና ለሰዎቻቸው ማለላቸው። 25 በሰባተኛው ወር ግን የመንግሥት ዘር የነበረ የኤልሴማ ልጅ የናታንዩ ልጅ እስማኤል መጣ፤ ከእርሱም ጋር ዐሥር ሰዎች ነበሩ፤ ጎዶልያንም መታው፤ ሞተም፤ ከእርሱም ጋር በመሴፋ የነበሩትን አይሁድንና ከለዳውያንንም ገደላቸው። 26 ከለዳውያንንም ፈርተው ነበርና ከታናሹ ጀምሮ እስከ ታላቁ ድረስ ሕዝቡ ሁሉ፥ የሠራዊቱም አለቆች ተነሥተው ወደ ግብፅ ገቡ። የዮአኪን ከእስር መፈታት ( ኤር. 52፥11-34 ) 27 እንዲህም ሆነ፤ የይሁዳ ንጉሥ ዮአኪን በተማረከ በሠላሳ ሰባተኛው ዓመት በዐሥራ ሁለተኛው ወር ከወሩም በሃያ ሰባተኛው ቀን የባቢሎን ንጉሥ ዮርማሮዴቅ በነገሠ በአንደኛው ዓመት የይሁዳን ንጉሥ ዮአኪንን ከፍ አደረገው፤ ከወህኒ ቤትም አወጣው፤ 28 መልካም ነገርንም ተናገረው፥ ዙፋኑንም ከእርሱ ጋር በባቢሎን ከነበሩት ነገሥታት ዙፋን በላይ አደረገለት። 29 በወህኒም ውስጥ ለብሶት የነበረውን ልብስ ለወጠለት፤ ዮአኪንም በሕይወቱ ዘመን ሁሉ በፊቱ ሁልጊዜ እንጀራ ይበላ ነበር። 30 ቀለቡንም ሁልጊዜ ከንጉሡ ቤት ይቀበል ነበር፤ በሕይወቱም ዘመን ሁሉ የዘወትር ቀለቡን ዕለት ዕለት ይሰጡት ነበር። |