2 ነገሥት 19 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ሕዝቅያስ የኢሳይያስን ምክር እንደ ጠየቀ ( ኢሳ. 37፥1-7 ) 1 ንጉሡም ሕዝቅያስ ይህን በሰማ ጊዜ ልብሱን ቀደደ፥ ማቅም ለበሰ፥ ወደ እግዚአብሔርም ቤት ገባ። 2 የቤቱንም አዛዥ ኤልያቄምን ጸሓፊውንም ሳምናስን የካህናቱንም አለቆች ማቅ ለብሰው ወደ አሞጽ ልጅ ወደ ነቢዩ ኢሳይያስ ይሄዱ ዘንድ ላካቸው። 3 እነርሱም አሉት፥ “ሕዝቅያስ እንዲህ ይላል፦ ይህ ቀን የመከራና የተግሣጽ የዘለፋም ቀን ነው፤ ልጆች የሚወለዱበት ጊዜ ደርሶአል፤ እናትም ለማማጥ ኀይል የላትም። 4 ምናልባት በሕያው አምላክ ላይ ይገዳደር ዘንድ ጌታው የአሦር ንጉሥ የላከውን የራፋስቂስን ቃል ሁሉ አምላክህ እግዚአብሔር ይሰማ እንደሆነ፥ አምላክህ እግዚአብሔርም ስለ ሰማው ቃል ይገሥጸው እንደ ሆነ፥ ስለዚህ ለቀረው ቅሬታ ጸልይ።” 5 እንዲሁ የንጉሡ የሕዝቅያስ ብላቴኖች ወደ ኢሳይያስ መጡ። 6 ኢሳይያስም አላቸው፥ “ለጌታችሁ እንዲህ በሉት፦ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ የአሦር ንጉሥ ብላቴኖች ስለ ተሳደቡት፥ ስለ ሰማኸው ቃል አትፍራ። 7 እነሆ፥ በላዩ መንፈስን እሰድዳለሁ፤ ወሬንም ይሰማል፤ ወደ ምድሩም ይመለሳል፤ በምድሩም በሰይፍ እንዲወድቅ አደርገዋለሁ በሉት።” ሰናክሬም በሕዝቅያስ ላይ እንደ ተገዳደረ ( ኢሳ. 37፥8-20 ) 8 የአሦርም ንጉሥ ከለኪሶ እንደ ራቀ ሰምቶ ነበርና ራፋስቂስ ተመልሶ በሎምና ሲዋጋ አገኘው። 9 እርሱም፥ “የኢትዮጵያ ንጉሥ ቲርሐቅ ሊወጋህ መጥቶአል” የሚል ወሬ በሰማ ጊዜ ተመልሶ ወደ ሕዝቅያስ መልእክተኞችን ላከ፤ እንዲህ ሲል፦ 10 “ለይሁዳ ንጉሥ ለሕዝቅያስ እንዲህ ብላችሁ ንገሩት፦ ኢየሩሳሌም በአሦር ንጉሥ እጅ አትሰጥም ብሎ የምትታመንበት አምላክህ አያታልልህ። 11 እነሆ፥ የአሦር ነገሥታት በምድር ሁሉ ላይ ያደረጉትን፥ እንዴትስ እንዳጠፉአቸው ሰምተሃል፤ አንተስ ትድናለህን? 12 አባቶች ያጠፉአቸውን፥ ጎዛንን፥ ካራንን፥ ራፌስን በታኤሴቴም የነበሩትንም የዔድንን ልጆች፥ የአሕዛብ አማልክት አዳኑአቸውን? 13 የሐማት ንጉሥ፥ የአርፋድ ንጉሥ፥ የሴፋሩሄም ከተማ ንጉሥ፥ የኤናና የዓዋ ንጉሥ ወዴት አሉ?” 14 ሕዝቅያስም ደብዳቤውን ከመልእክተኞች እጅ ተቀብሎ አነበበው፤ ሕዝቅያስም ወደ እግዚአብሔር ቤት ወጥቶ በእግዚአብሔር ፊት ዘረጋው። 15 ሕዝቅያስም ወደ እግዚአብሔር እንዲህ ብሎ ጸለየ፥ “በኪሩቤል ላይ የምትቀመጥ የእስራኤል አምላክ አቤቱ፥ አንተ ብቻህን የምድር ነገሥታት ሁሉ አምላክ ነህ፤ ሰማይንና ምድርን ፈጥረሃል ። 16 አቤቱ፥ ጆሮህን አዘንብልና ስማ፥ አቤቱ፥ ዐይንህን ክፈትና እይ፤ በሕያው አምላክ ላይ ይገዳደር ዘንድ የላከውን የሰናክሬምን ቃል ስማ። 17 አቤቱ፥ በእውነት የአሦር ነገሥት አሕዛብን አጥፍተዋል፤ 18 አማልክቶቻቸውንም በእሳት ላይ ጥለዋል፤ የእንጨትና የድንጋይ የሰው እጅ ሥራ ነበሩ እንጂ አማልክት አልነበሩምና፤ ስለዚህ አጥፍተዋቸዋል። 19 እንግዲህም አምላካችን አቤቱ፥ የምድር መንግሥታት ሁሉ አንተ ብቻ እግዚአብሔር አምላክ እንደ ሆንህ ያውቁ ዘንድ ከአሦር ንጉሥ እጅ አድነን።” ኢሳይያስ ለሕዝቅያስ እንደ ላከ ( ኢሳ. 37፥21-38 ) 20 የአሞጽም ልጅ ኢሳይያስ እንዲህ ብሎ ወደ ሕዝቅያስ ላከ፥ “የሠራዊት ጌታ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ስለ አሦር ንጉሥ ስለ ሰናክሬም ወደ እኔ የለመንኸውን ሰምቻለሁ። 21 ድንግሊቱ የጽዮን ልጅ፥ ሰድቦሻልና ንቆሻልምና፥ የኢየሩሳሌም ልጅ፥ በአንቺ ላይ ራሱን ነቅንቋልና እግዚአብሔር በእርሱ ላይ የተናገረው ቃል ይህ ነው፦ 22 የተገዳደርኸው፥ የሰደብኸውስ ማን ነው? ቃልህንስ ከፍ ከፍ ያደረግኸው፥ ዐይንህንም ወደ ላይ ያነሣኸው በማን ላይ ነው? በእስራኤል ቅዱስ ላይ ነው። 23 አንተስ በመልእክተኞችህ እጅ በእግዚአብሔር ላይ ተገዳደርህ፤ እንዲህም አልህ፦ በሰረገላዬ ብዛት ወደ ተራሮች ከፍታ፥ ወደ ሊባኖስ ጥግ እወጣለሁ፤ ረጃጅሞችንም ዝግባዎች የተመረጡትንም ጥዶች እቈርጣለሁ፤ ወደ ሀገሩም ዳርቻና ወደ ቀርሜሎስ ዱር እገባለሁ። 24 ዕረፍት አደረግሁ፤ የባዕድ ውኃንም ጠጣሁ፥ የተገደበውንም ውኃ ሁሉ በእግሬ ጫማ አደርቃለሁ። 25 “እኔ ጥንቱን እንደ ሠራሁት፥ ቀድሞውንም እንዳደረግሁት አልሰማህምን? አሁንም የተመሸጉትን ከተሞች የፍርስራሽ ክምር እስኪሆኑ ድረስ እንድታፈርስ አደረግሁህ። 26 ስለዚህም የሚኖሩባቸው ሰዎች እጆቻቸው ዝለዋል፤ ደንግጠውም አፍረዋል፤ እንደ ምድረ በዳ ሣር፥ እንደ ለምለምም ቡቃያ፥ በሰገነትም ላይ እንዳለ ሣር፥ ሳይሸት ዋግ እንደ መታውም እህል ሆነዋል። 27 እኔ ግን መቀመጫህንና መውጫህን መግቢያህንም፥ በእኔም ላይ የተቈጣኸውን ቍጣ ዐውቄአለሁ። 28 ቍጣህና ትዕቢትህ ወደ ጆሮዬ ደርሶአልና ስለዚህ ስናጋዬን በአፍንጫህ፥ ልጓሜንም በከንፈርህ አደርጋለሁ፤ በመጣህበት መንገድም እመልስሃለሁ። 29 “ይህም ለአንተ ምልክት ይሆንልሃል፤ በዚህ ዓመት የገቦውን፥ በሁለተኛውም ዓመት ከገቦው የበቀለውን ትበላለህ፤ በሦስተኛውም ዓመት ትዘራለህ፤ ታጭድማለህ፥ ወይንም ትተክላለህ፤ ፍሬውንም ትበላለህ። 30 የዳነው የይሁዳ ቤት ቅሬታ ሥሩን ወደ ታች ይሰድዳል፤ ወደ ላይም ያፈራል። 31 ከኢየሩሳሌም ቅሬታ፥ ከጽዮንም ተራራ የዳነ ይወጣልና፤ የሠራዊት ጌታ የእግዚአብሔር ቅንአት ይህን ያደርጋል።” 32 እንደዚህ አይደለምን? እግዚአብሔር ስለ አሦር ንጉሥ እንዲህ ይላል፥ “ወደዚች ከተማ አይገባም፥ ፍላጻንም አይወረውርባትም፤ በጋሻም አይመጣባትም፥ የአፈርንም ድልድል አይደለድልባትም። 33 በመጣበት መንገድ በዚያ ይመለሳል እንጂ፥ ወደዚህችም ከተማ አይገባም፥ ይላል እግዚአብሔር። 34 ስለ እኔም፥ ስለ ባሪያዬ ስለ ዳዊትም ይህችን ከተማ እጋርዳታለሁ።” 35 በዚያችም ሌሊት የእግዚአብሔር መልአክ መጣ፤ ከአሦራውያንም ሰፈር መቶ ሰማንያ አምስት ሺህ ገደለ፤ ማለዳም በተነሡ ጊዜ፥ እነሆ፥ ሁሉ በድኖች ነበሩ። 36 የአሦርም ንጉሥ ሰናክሬም ተነሥቶ ሄደ፤ ተመልሶም በነነዌ ተቀመጠ። 37 በአምላኩም በሲድራክ ቤት ሲሰግድ ልጆቹ አድራሜሌክና ሶርሶር በሰይፍ ገደሉት፤ ወደ አራራትም ሀገር ኰበለሉ። ልጁም አስራዶን በእርሱ ፋንታ ነገሠ። |