2 ነገሥት 17 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)የእስራኤል ንጉሥ ሆሴዕ 1 የይሁዳ ንጉሥ አካዝ በነገሠ በዐሥራ ሁለተኛው ዓመት የኤላ ልጅ ሆሴዕ በእስራኤል ላይ በሰማርያ ዘጠኝ ዓመት ነገሠ። 2 በእግዚአብሔርም ፊት ክፉ ነገር አደረገ፤ ነገር ግን ከእርሱ አስቀድሞ እንደ ነበሩት እንደ እስራኤል ነገሥታት አልሆነም። 3 የአሦርም ንጉሥ ስልምናሶር በእርሱ ላይ ዘመተ፤ ሆሴዕም ተገዛለት፤ ግብርም አመጣለት። 4 የአሦርም ንጉሥ በሆሴዕ ላይ ዐመፅ አገኘ፤ መልእክተኞችን ወደ ግብፅ ንጉሥ ወደ ሴጎር ልኮ ነበርና፤ እንደ ልማዱም በየዓመቱ ለአሦር ንጉሥ ግብር አልሰጠምና፤ ስለዚህ የአሦር ንጉሥ ተዋጋው፤ ይዞም በወህኒ ቤት አሰረው። የዐሥሩ ነገድ መንግሥት መውደቅ 5 የአሦርም ንጉሥ በምድር ሁሉ ላይ ወጣ፤ ወደ ሰማርያም ወጥቶ ሦስት ዓመት ከበባት። 6 በሆሴዕም በዘጠነኛው ዓመት የአሦር ንጉሥ ሰማርያን ያዘ፤ እስራኤልንም ወደ አሶር አፈለሰ፤ በአላሔና በአቦር፤ በጎዛንም ወንዝ፤ በሜዶንም ከተሞች አኖራቸው። 7 የእስራኤልም ልጆች ከግብፅ ንጉሥ ከፈርዖን እጅ፥ ከግብፅ ምድር ያወጣቸውን አምላካቸውን እግዚአብሔርን በድለው ነበርና፥ ሌሎችንም አማልክት አምልከው ነበርና፤ 8 እግዚአብሔርም ከእስራኤል ልጆች ፊት በአሳደዳቸው በአሕዛብ ሥርዐት፥ የእስራኤልም ነገሥታት ባደረጓት ሥርዐት ሄደው ነበርና እንደዚህ ሆነ። 9 የእስራኤልም ልጆች በአምላካቸው በእግዚአብሔር ላይ ቅን ያልሆነን ነገር በስውር አደረጉ፤ በከተሞቻቸውም ሁሉ ከዘበኞች ግንብ ጀምሮ እስከ ተመሸገች ከተማ ድረስ በከፍታዎች ላይ መስገጃዎችን ሠሩ። 10 በረጃጅሙ ኮረብታ ሁሉ ላይ፥ በለመለመውም ዛፍ ሁሉ በታች ሐውልቶችንና የማምለኪያ ዐምዶችን ተከሉ፤ 11 እግዚአብሔርም ከፊታቸው ያወጣቸው አሕዛብ እንዳደረጉት፥ በኮረብቶቹ መስገጃዎች ሁሉ ላይ ያጥኑ ነበር፤ እግዚአብሔርንም ያስቈጡ ዘንድ የማምለኪያ ዐፀዶችንና ሐውልቶችን አደረጉ፤ 12 እግዚአብሔርም፥ “በእግዚአብሔር ላይ ይህን አታድርጉ” ብሎ የከለከላቸውን ጣዖቶች አመለኩ። 13 እግዚአብሔርም፥ “ከክፉ መንገዳችሁ ተመለሱ፤ ለአባቶቻችሁም እንዳዘዝሁት፥ በባሪያዎቼ በነቢያት የላክሁላችሁን ትእዛዜንና ሥርዐቴን፥ ሕጌንም ሁሉ ጠብቁ” ብሎ በነቢዩ ሁሉና በባለ ራእዩ አፍ ሁሉ በእስራኤልና በይሁዳ መሰከረ። 14 ነገር ግን አምላካቸውን እግዚአብሔርን እንዳላመኑ ከአባቶቻቸው አንገት ይልቅ አንገታቸውን አደነደኑ እንጂ አልሰሙም። 15 የገባላቸውንም ቃል ኪዳን ሁሉ አልጠበቁም። ከንቱ ነገርንም ተከተሉ፤ ከንቱም ሆኑ፤ እንደ እነርሱም እንዳይሠሩ ያዘዛቸውን በዙሪያቸው ያሉትን አሕዛብ ተከተሉ። 16 የአምላካቸውንም የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ሁሉ ተዉ፤ ቀልጠው የተሠሩትንም የሁለቱን እንቦሶች ምስሎች አደረጉ፤ የማምለኪያ ዐፀድንም ተከሉ፤ ለሰማይም ሠራዊት ሁሉ ሰገዱ፤ በዓልንም አመለኩ። 17 ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸውንም በእሳት ሥዉአቸው፤ ምዋርተኞችና አስማተኞችም ሆኑ፤ ያስቈጡትም ዘንድ በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ነገር ለማድረግ ራሳቸውን ሸጡ። 18 ስለዚህም እግዚአብሔር በእስራኤል ላይ እጅግ ተቈጣ፤ ከፊቱም ጣላቸው፤ ከይሁዳም ነገድ ብቻ በቀር ማንም አልቀረም። 19 ይሁዳም ደግሞ እስራኤል ባደረጋት ሥርዐት ሄደ እንጂ የአምላኩን የእግዚአብሔርን ትእዛዝ አልጠበቀም፤ እግዚአብሔርንም ተዉት። 20 እግዚአብሔርም በእስራኤል ዘር ሁሉ ተቈጣ፤ አስጨነቃቸውም፤ ከፊቱም እስኪጥላቸው ድረስ በበዝባዦች እጅ አሳልፎ ሰጣቸው። 21 እስራኤልም ከዳዊት ቤት ተለዩ፤ የናባጥንም ልጅ ኢዮርብዓምን አነገሡ፤ ኢዮርብዓምም እግዚአብሔርን ከመከተል እስራኤልን መለሰ፤ ታላቅም ኀጢአት አሠራቸው። 22 የእስራኤልም ልጆች ኢዮርብዓም ባደረገው ኀጢአት ሁሉ ሄዱ፤ 23 እግዚአብሔርም በባሪያዎቹ በነቢያት ሁሉ አፍ እንደ ተናገረው እስራኤልን ከፊቱ እስኪያወጣ ድረስ ከእርስዋ አልራቁም። እስራኤልም እስከ ዛሬ ድረስ ከምድሩ ወደ አሦር ፈለሰ። 24 የአሦርም ንጉሥ ከባቢሎንና ከኩታ፥ ከአዋና ከሐማት፥ ከሴፌርዋይም ሰዎችን አመጣ፤ በእስራኤልም ልጆች ፋንታ በሰማርያ ከተሞች አኖራቸው፤ ሰማርያንም ወረሱአት፤ በከተሞችዋም ተቀመጡ። 25 በዚያም መቀመጥ በጀመሩ ጊዜ እግዚአብሔርን አይፈሩትም ነበር፤ እግዚአብሔርም አንበሶችን ሰደደባቸው፤ ይገድሉአቸውም ነበር። 26 ስለዚህም ለአሦር ንጉሥ፥ “ያፈለስኻቸው፥ በሰማርያም ከተሞች ያኖርኻቸው ሕዝቦች የሀገሩን አምላክ ሕግ አላወቁም፤ የሀገሩን አምላክ ሕግ አላወቁምና አንበሶችን ሰድዶባቸዋል፤ እነሆም፥ እየገደሉአቸው ነው” ብለው ተናገሩት። 27 የአሦርም ንጉሥ፥ “ከዚያ ካመጣኋቸው ካህናት አንዱን ውሰዱ፤ ሄዶም በዚያ ይቀመጥ፤ የሀገሩንም አምላክ ሕግ ያስተምራቸው” ብሎ አዘዘ። 28 ከሰማርያም ካፈለሱአቸው ካህናት አንዱን ወስደው በቤቴል አኖሩት፤ ያም ካህን እግዚአብሔርን እንዴት እንደሚፈሩት ያስተምራቸው ነበር። 29 በየሕዝባቸውም አምላኮቻቸውን አደረጉ፤ ሳምራውያንም በሠሯቸው በኮረብታው መስገጃዎች ሕዝቡ ሁሉ በሚኖሩባቸው ከተሞቻቸው አኖሩአቸው። 30 የባቢሎንም ሰዎች ሴኬቤቴናሆምን ሠሩ፤ የኩታም ሰዎች ኤርጌትን ሠሩ፤ 31 የሐማትም ሰዎች አሲማትን ሠሩ፤ አዋውያንም ኤልባዝርንና ተርታቅን ሠሩ፤ የሴፌርዋይም ሰዎች ለሴፌርዋይም አማልክት ለአድራሜሌክና ለአኔሜሌክ ልጆቻቸውን በእሳት ይሠዉ ነበር። 32 እግዚአብሔርንም ይፈሩ ነበር፤ ሕዝቡም ሁሉ በሚኖሩበት ከተማ በሰማርያ በሠሩት በከፍታው ቦታ ጣዖቶቻቸውን አኖሩ። እግዚአብሔርንም ይፈሩ ነበር፤ ከመካከላቸውም ለኮረብታው መስገጃዎች ካህናትን አደረጉ፤ በኮረብታውም መስገጃዎች ይሠዉ ነበር። 33 እግዚአብሔርንም ሲፈሩ ከመካከላቸው እንደ ፈለሱት እንደ አሕዛብ ልማድ አምላካቸውን ያመልኩ ነበር። 34 እስከ ዛሬም ድረስ እንደ ልማዳቸው ያደርጋሉ፤ እግዚአብሔርንም ይፈራሉ፤ እግዚአብሔርም እስራኤል ብሎ የጠራውን የያዕቆብን ልጆች እንዳዘዛቸው ሥርዐትና ፍርድ፥ ሕግና ትእዛዝም ያደርጋሉ። 35 እግዚአብሔርም ከእነርሱ ጋር ቃል ኪዳን አደረገ፤ እንዲህም ብሎ አዘዛቸው፥ “ሌሎችን አማልክት አትፍሩአቸው፤ አትስገዱላቸውም፤ አታምልኩአቸውም፤ አትሠዉላቸውም። 36 ነገር ግን በታላቅ ኀይል በተዘረጋችም ክንድ ከግብፅ ምድር ያወጣችሁን እግዚአብሔርን እርሱን ፍሩ፤ ለእርሱም ስገዱ፤ ለእርሱም ሠዉ። 37 የጻፈላችሁንም ሥርዐትና ፍርድ፥ ሕግና ትእዛዝም ለዘለዓለም ታደርጉ ዘንድ ጠብቁ፤ ሌሎችንም አማልክት አትፍሩ። 38 ከእናንተም ጋር ያደረገውን ቃል ኪዳን አትርሱ፤ ሌሎችንም አማልክት አትፍሩ። 39 ነገር ግን አምላካችሁን እግዚአብሔርን ፍሩ፤ እርሱም ከጠላቶቻቸሁ ሁሉ እጅ ያድናችኋል። 40 ነገር ግን እነርሱ እንደሚያደርጉት ልማዳቸውን አትስሙ። 41 እነዚህም አሕዛብ እግዚአብሔርን ይፈሩ ነበር፤ ደግሞም የተቀረጹ ምስሎቻቸውን ያመልኩ ነበር፤ ልጆቻቸውም፥ የልጅ ልጆቻቸውም አባቶቻቸው እንዳደረጉ እስከ ዛሬ ድረስ እንዲሁ ያደርጋሉ።” |