2 ነገሥት 16 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)የይሁዳ ንጉሥ አካዝ ( 2ዜ.መ. 28፥1-27 ) 1 በሮሜልዩ ልጅ በፋቁሔ በዐሥራ ሰባተኛው ዓመት የይሁዳ ንጉሥ የኢዮአታም ልጅ አካዝ ነገሠ። 2 አካዝ መንገሥ በጀመረ ጊዜ የሃያ ዓመት ጐልማሳ ነበረ፤ በኢየሩሳሌምም ዐሥራ ስድስት ዓመት ነገሠ፤ እንደ አባቱም እንደ ዳዊት በአምላኩ በእግዚአብሔር ፊት በታማኝነት ቅን ነገርን አላደረገም። 3 ነገር ግን በእስራኤል ነገሥታት መንገድ ሄደ፤ ደግሞም እግዚአብሔር ከእስራኤል ልጆች ፊት እንዳሳደዳቸው እንደ አሕዛብ ርኵሰት ልጁን በእሳት ሠዋው። 4 በመስገጃዎቹና በኮረብቶቹ ላይ በለመለመውም ዛፍ ሁሉ በታች ይሠዋና ያጥን ነበር። 5 ያን ጊዜም የሶርያ ንጉሥ ረአሶንና የእስራኤል ንጉሥ የሮሜልዩ ልጅ ፋቁሔ ሊዋጉ ወደ ኢየሩሳሌም ወጡ፤ አካዝንም ከበቡት፥ ሊያሸንፉት ግን አልቻሉም። 6 በዚያም ዘመን የሶርያ ንጉሥ ረአሶን ኤላትን ወደ ሶርያ መለሰላቸው፥ አይሁድንም ከኤላት አሳደደ፤ ኤዶማውያንም ወደ ኤላት መጥተው እስከ ዛሬ ድረስ በዚያ ይኖራሉ። 7 አካዝም፥ “እኔ ባሪያህና ልጅህ ነኝ፤ መጥተህ ከተነሡብኝ ከሶርያ ንጉሥና ከእስራኤል ንጉሥ እጅ አድነኝ” ብሎ ወደ አሦር ንጉሥ ወደ ቴልጌልቴልፌልሶር መልእክተኞችን ላከ። 8 አካዝም በእግዚአብሔር ቤትና በንጉሡ ቤተ መዛግብት የተገኘውን ብርና ወርቅ ወስዶ ወደ አሦር ንጉሥ ገጸ በረከት አድርጎ ሰደደው። 9 የአሦርም ንጉሥ ሰማው፤ የአሦርም ንጉሥ ወደ ደማስቆ ወጣ፤ ያዛትም፤ ሕዝብዋንም ወደ ቂር አፈለሳቸው፤ ረአሶንንም ገደለው። 10 የይሁዳ ንጉሥ አካዝም የአሦርን ንጉሥ ቴልጌልቴልፌልሶርን ሊገናኘው ወደ ደማስቆ ሄደ፤ በደማስቆ የነበረውንም መሠዊያ አየ፤ ንጉሡም አካዝ የመሠዊያውን ምሳሌና የአሠራሩን መልክ ወደ ካህኑ ወደ ኦርያ ላከው። 11 ካህኑም ኦርያ ንጉሡ አካዝ ከደማስቆ እንደ ላከለት መሠዊያውን ሁሉ ሠራ፤ እንዲሁም ካህኑ ኦርያ ንጉሡ አካዝ ከደማስቆ እስኪመጣ ድረስ ሠራው። 12 ንጉሡም ከደማስቆ በመጣ ጊዜ መሠዊያውን አየ፤ ንጉሡም ወደ መሠዊያው ወጣ። 13 የሚቃጠለውን መሥዋዕትና የእህሉንም ቍርባን አሳረገ፤ የመጠጡንም ቍርባን አፈሰሰ፤ የደኅንነቱንም መሥዋዕት ደም በመሠዊያው ላይ ረጨ። 14 በእግዚአብሔርም ፊት የነበረውን የናሱን መሠዊያ ከእግዚአብሔር ቤት ፊት ከመሠዊያውና ከእግዚአብሔር ቤት መካከል ፈቀቅ አድርጎ በመሠዊያው አጠገብ በሰሜን በኩል አኖረው። 15 ንጉሡም አካዝ፥ “የሚቃጠለውን የጥዋት መሥዋዕት፥ የማታውንም የእህሉን ቍርባን፥ የንጉሡንም መሥዋዕትና የእህሉን ቍርባን፥ የሕዝቡንም ሁሉ የሚቃጠለውን መሥዋዕትና የእህሉን፥ የመጠጡንም ቍርባን በታላቁ መሠዊያ ላይ አቅርብ፤ የሚቃጠለውንም መሥዋዕት ደም ሁሉ፥ የሌላውንም መሥዋዕታቸውን ደም ሁሉ በእርሱ ላይ ርጭበት፤ የናሱ መሠዊያ ግን በየጥዋቱ ለእኔ ይሁን” ብሎ ካህኑን ኦርያን አዘዘው። 16 ካህኑ ኦርያም ንጉሡ አካዝ እንዳዘዘው ሁሉ እንዲሁ አደረገ። 17 ንጉሡ አካዝም የመቀመጫዎችን ክፈፍ ቈረጠ፤ ከእነርሱም የመታጠቢያውን ሰኖች ወሰደ፤ ኵሬውንም ከበታቹ ከነበሩት ከናሱ በሬዎች አወረደው፤ በጠፍጣፋውም ድንጋይ ላይ አኖረው። 18 በእግዚአብሔርም ቤት የዙፋኑን መሠረት ሠራ፤ ስለ አሦርም ንጉሥ በውጭ ያለውን የንጉሡን መግቢያ ወደ እግዚአብሔር ቤት አዞረው። 19 የቀረውም አካዝ ያደረገው ነገር እነሆ፥ በይሁዳ ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን? 20 አካዝም እንደ አባቶቹ አንቀላፋ፥ በዳዊትም ከተማ ተቀበረ፤ ልጁም ሕዝቅያስ በእርሱ ፋንታ ነገሠ። |