2 ነገሥት 14 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)የይሁዳ ንጉሥ አሜስያስ ( 2ዜ.መ. 25፥1-24 ) 1 በእስራኤል ንጉሥ በኢዮአካዝ ልጅ በዮአስ በሁለተኛው ዓመት የይሁዳ ንጉሥ የኢዮአስ ልጅ አሜስያስ ነገሠ። 2 መንገሥም በጀመረ ጊዜ ዕድሜው ሃያ አምስት ዓመት ነበረ፤ በኢየሩሳሌምም ሃያ ዘጠኝ ዓመት ነገሠ። እናቱም ዮአድም የተባለች የኢየሩሳሌም ሴት ነበረች። 3 በእግዚአብሔርም ፊት ቅን ነገር አደረገ፤ ነገር ግን አባቱ ኢዮአስ እንዳደረገ ሁሉ እንጂ እንደ አባቱ እንደ ዳዊት አላደረገም። 4 ነገር ግን በኮረብቶቹ ላይ ያሉትን መስገጃዎች አላስወገደም፤ ሕዝቡም ገና በኮረብቶቹ ላይ ባሉት መስገጃዎች ይሠዋና ያጥን ነበር። 5 መንግሥቱም በእጁ በጸናለት ጊዜ አባቱን የገደሉትን አገልጋዮች ገደለ። 6 በሙሴ ሕግ መጽሐፍም እንደ ተጻፈ፥ እግዚአብሔርም፥ “ሁሉ በኀጢአቱ ይሙት እንጂ አባቶች ስለ ልጆች አይሙቱ፤ ልጆችም ስለ አባቶች አይሙቱ” ብሎ እንዳዘዘ የነፍሰ ገዳዮቹን ልጆች አልገደላቸውም። 7 እርሱም በጨው ሸለቆ ከኤዶምያስ ዐሥር ሺህ ሰው ገደለ፤ ሴላንም በጦርነት ወስዶ ስምዋን እስከ ዛሬ ድረስ “ዮቅትኤል” ብሎ ጠራት። 8 በዚያን ጊዜም አሜስያስ፥ “ና እርስ በርሳችን ፊት ለፊት እንተያይ” ብሎ ወደ እስራኤል ንጉሥ ወደ ኢዩ ልጅ ወደ ኢዮአካዝ ልጅ ወደ ዮአስ መልእክተኞችን ላከ። 9 የእስራኤልም ንጉሥ ዮአስ፥ “የሊባኖስ ኵርንችት፦ ልጅህን ለልጄ ሚስት አድርገህ ስጠው ብሎ ወደ ሊባኖስ ዝግባ ላከ፤ የሊባኖስም አውሬ አልፎ ኵርንችቱን ረገጠ። 10 ኤዶምያስን በእውነት መታህ፤ ልብህንም ከፍ ከፍ አደረግህ፤ በዚያ ተመካ፤ በቤትህም ተቀመጥ፤ አንተ፥ ይሁዳም ከአንተ ጋር ትወድቁ ዘንድ ስለ ምን መከራን ትሻለህ?” ብሎ ወደ ይሁዳ ንጉሥ ወደ አሜስያስ ላከ። 11 አሜስያስ ግን አልሰማም፤ የእስራኤልም ንጉሥ ዮአስ ዘመተ፤ እርሱና የይሁዳ ንጉሥ አሜስያስም በይሁዳ ባለች በቤትሳሚስ ፊት ለፊት ተያዩ። 12 ይሁዳም በእስራኤል ፊት ተመታ፤ እያንዳንዱም ወደ ድንኳኑ ሸሸ። 13 የእስራኤልም ንጉሥ ዮአስ የይሁዳን ንጉሥ የአካዝያስን ልጅ የኢዮአስን ልጅ አሜስያስን በቤትሳሚስ ይዞ ወደ ኢየሩሳሌም መጣ፤ የኢየሩሳሌምንም ቅጥር ከኤፍሬም በር ጀምሮ እስከ ማዕዘኑ በር ድረስ አራት መቶ ክንድ አፈረሰ። 14 ወርቁንና ብሩን ሁሉ፥ በእግዚአብሔርም ቤትና በንጉሥ ቤተ መዛግብት የነበሩትን ዕቃዎች ሁሉ፤ በመያዣም የተያዙትን ልጆች ወስዶ ወደ ሰማርያ ተመለሰ። 15 የቀረውም ያደረገው የዮአስ ነገር፥ ኀይሉም፥ ከይሁዳም ንጉሥ ከአሜስያስ ጋር እንደ ተዋጋ፥ እነሆ፥ በእስራኤል ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን? 16 ዮአስም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ በሰማርያም ከእስራኤል ነገሥታት ጋር ተቀበረ፤ ልጁም ኢዮርብዓም በፋንታው ነገሠ። 17 የይሁዳ ንጉሥ የኢዮአስ ልጅ አሜስያስ ከእስራኤል ንጉሥ ከኢዮአካዝ ልጅ ከዮአስ ሞት በኋላ ዐሥራ አምስት ዓመት ኖረ። 18 የቀረውም የአሜስያስ ነገር፥ ያደረገውም ሁሉ፥ እነሆ፥ በይሁዳ ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን? 19 በኢየሩሳሌምም የዐመፅ መሐላ አደረጉበት፤ እርሱም ወደ ለኪሶ ኮበለለ፤ ወደ ለኪሶም ተከተሉት፤ በዚያም ገደሉት። 20 በድኑንም በፈረስ ጭነው አመጡት፤ በኢየሩሳሌምም በዳዊት ከተማ ከአባቶቹ ጋር ቀበሩት። 21 የይሁዳም ሕዝብ ሁሉ የዐሥራ ስድስት ዓመት ልጅ የነበረውን ዓዛርያስን ወስደው በአባቱ በአሜስያስ ፋንታ አነገሡት። 22 ንጉሡም ከአባቶቹ ጋር ከአንቀላፋ በኋላ፥ ኤላትን ሠርቶ ወደ ይሁዳ መለሳት። የእስራኤል ንጉሥ ዳግማዊ ኢዮርብአም 23 በይሁዳ ንጉሥ በኢዮአስ ልጅ በአሜስያስ በዐሥራ አምስተኛው ዓመተ መንግሥት የእስራኤል ንጉሥ የዮአስ ልጅ ኢዮርብዓም በሰማርያ መንገሥ ጀመረ፤ አርባ አንድ ዓመትም ነገሠ። 24 በእግዚአብሔርም ፊት ክፉ ነገር አደረገ እስራኤልንም ካሳታቸው ከናባጥ ልጅ ከኢዮርብዓም ኀጢአት ሁሉ አልራቀም። 25 በጋትሔፌር በነበረው በአማቴ ልጅ በባሪያው በነቢዩ በዮናስ አፍ እንደ ተናገረው እንደ እስራኤል አምላክ እንደ እግዚአብሔር ቃል የእስራኤልን ድንበር ከሔማት መግቢያ ጀምሮ እስከ ዓረባ ባሕር ድረስ መለሰ። 26 በቍጥር እንዳነሱ፥ የታሰረውና የተለቀቀውም እንደ ጠፋ፥ እስራኤልንም የሚረዳ እንዳልነበረ እግዚአብሔር እጅግ የመረረውን የእስራኤልን ጭንቀት አየ። 27 እግዚአብሔርም የእስራኤልን ዘር ከሰማይ በታች ይደመስስ ዘንድ አልተናገረም፤ ነገር ግን በዮአስ ልጅ በኢዮርብዓም እጅ አዳናቸው። 28 የቀረውም የኢዮርብዓም ነገር፥ ያደረገውም ሁሉ፥ ኀይሉም፥ የይሁዳ የነበረውን ደማስቆንና ሔማትን ለእስራኤል እንደ መለሰ፥ እነሆ፥ በእስራኤል ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን? 29 ኢዮርብዓምም እንደ አባቶቹ እንደ እስራኤል ነገሥታት አንቀላፋ፤ ልጁም ዘካርያስ በፋንታው ነገሠ። |