2 ነገሥት 13 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)የእስራኤል ንጉሥ ኢዮአካዝ 1 በይሁዳ ንጉሥ በአካዝያስ ልጅ በኢዮአስ በሃያ ሦስተኛው ዓመት የኢዩ ልጅ ኢዮአካዝ በሰማርያ ነገሠ፤ ዐሥራ ሰባት ዓመትም ነገሠ። 2 በእግዚአብሔርም ፊት ክፉ ነገር አደረገ፤ እስራኤልንም ያሳተውን የናባጥን ልጅ የኢዮርብዓምን ኀጢአት ተከተለ፤ ከእርስዋም አልራቀም። 3 እግዚአብሔርም በእስራኤል ላይ በጣም ተቈጣ፤ በዘመኑም ሁሉ በሶርያው ንጉሥ በአዛሄል እጅ፥ በአዛሄልም ልጅ በወልደ አዴር እጅ አሳልፎ ሰጣቸው። 4 ኢዮአካዝም እግዚአብሔርን ለመነ፤ እግዚአብሔርም የሶርያ ንጉሥ እስራኤልን ያስጨነቀበትን ጭንቀት አይቶአልና ሰማው። 5 እግዚአብሔርም ለእስራኤል ታዳጊን ሰጠ፤ ከሶርያውያንም እጅ ዳኑ፤ የእስራኤልም ልጆች እንደ ቀድሞው ጊዜ በድንኳናቸው ተቀመጡ። 6 ነገር ግን በእርስዋ ሄዱ እንጂ እስራኤልን ካሳተበት ከኢዮርብዓም ቤት ኀጢአት አልራቁም፤ ደግሞም የማምለኪያ ዐፀድ በሰማርያ ቆሞ ነበረ። 7 ለኢዮአካዝም ከኀምሳ ፈረሰኞች፥ ከዐሥርም ሰረገሎች፥ ከዐሥር ሺህም እግረኞች በቀር ሕዝብ አልቀረለትም፤ የሶርያ ንጉሥ አጥፍቶአቸዋልና፥ በአውድማም እንዳለ ዕብቅ አድቅቆአቸዋልና። 8 የቀረውም የኢዮአካዝ ነገር፥ ያደረገውም ሁሉ፥ ኀይሉም፥ እነሆ፥ በእስራኤል ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን? 9 ኢዮአካዝም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፥ በሰማርያም ቀበሩት፥ ልጁም ዮአስ በፋንታው ነገሠ። 10 በይሁዳ ንጉሥ በኢዮአስ በሠላሳ ሰባተኛው ዓመት የኢዮአካዝ ልጅ ዮአስ በእስራኤል ላይ በሰማርያ ዐሥራ ስድስት ዓመት ነገሠ። 11 በእግዚአብሔርም ፊት ክፉ ነገር አደረገ፤ እስራኤልን ካሳተው ከናባጥ ልጅ ከኢዮርብዓም ኀጢአት አልራቀም፤ ነገር ግን በእርስዋ ሄደ። 12 የቀረውም የዮአስ ነገር፥ ያደረገውም ሁሉ፥ ከይሁዳም ንጉሥ ከአሜስያስ ጋር የተዋጋበት ኀይሉ፥ እነሆ፥ በእስራኤል ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን? 13 ዮአስም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ ኢዮርብዓምም በዙፋኑ ላይ ተቀመጠ፤ ዮአስም በሰማርያ ከእስራኤል ነገሥታት ጋር ተቀበረ። የነቢዩ ኤልሳዕ ሞት 14 ኤልሳዕም በሚሞትበት በሽታ ታመመ፤ የእስራኤልም ንጉሥ ዮአስ ወደ እርሱ ወርዶ በፊቱ አለቀሰና፥ “አባቴ ሆይ፥ አባቴ ሆይ፥ የእስራኤል ሰረገላቸውና ፈረሰኛቸው” አለ። 15 ኤልሳዕም፥ “ቀስትህንና ፍላጻዎችህን ውሰድ” አለው፤ ቀስቱንና ፍላጻዎቹንም ወሰደ። 16 የእስራኤልንም ንጉሥ አለው፥ “እጅህን በቀስቱ ላይ ጫን።” ዮአስም እጁን በቀስቱ ላይ ጫነ፤ ኤልሳዕም እጁን በንጉሡ እጅ ላይ ጫነ፦ 17 “የምሥራቁንም መስኮት ክፈት” አለ፤ ከፈተውም። ኤልሳዕም፥ “ወርውር” አለው፤ ወረወረውም እርሱም፥ “የእግዚአብሔር መድኀኒት ፍላጻ ነው፤ ከሶርያ የመዳን ፍላጻ ነው፤ እስክታጠፋቸውም ድረስ ሶርያውያንን በአፌቅ ትመታለህ” አለ። 18 ኤልሳዕም ደግሞ፥ “ፍላጻዎችህን ውሰድ” አለው ወሰዳቸውም። የእስራኤልንም ንጉሥ፥ “ምድሩን ምታው” አለው። ንጉሡም ሦስት ጊዜ መትቶ ቆመ። 19 የእግዚአብሔርም ሰው አዝኖ፥ “አምስት ወይም ስድስት ጊዜ መትተኸው ቢሆን ኖሮ ሶርያውያንን እስክታጠፋቸው ድረስ በመታኻቸው ነበር፤ አሁን ግን ሦስት ጊዜ ብቻ ሶርያን ትመታለህ” አለ። 20 ኤልሳዕም ሞተ፤ ቀበሩትም። ከሞዓብም አደጋ ጣዮች በየዓመቱ መጀመሪያ ወደ ሀገሩ ይገቡ ነበር። 21 ሰዎችም አንድ ሰው ሲቀብሩ አደጋ ጣዮችን አዩ፤ ሬሳውንም በኤልሳዕ መቃብር ላይ ጣሉት፤ የኤልሳዕንም አጥንት በነካ ጊዜ ሰውዬው ድኖ በእግሩ ቆመ። 22 አዛሄልም በኢዮአካዝ ዘመን ሁሉ እስራኤልን አስጨነቀ፤ 23 እግዚአብሔር ግን ራራላቸው፤ ማራቸውም፤ ከአብርሃምና ከይስሐቅ፥ ከያዕቆብም ጋር ስላደረገው ቃል ኪዳን እነርሱን ተመለከተ፤ ሊያጠፋቸውም አልወደደም፤ ፈጽሞም ከፊቱ አልጣላቸውም። 24 የሶርያም ንጉሥ አዛሄል ሞተ፤ ልጁም ወልደ አዴር በፋንታው ነገሠ። 25 አዛሄልም ከአባቱ ከኢዮአካዝ እጅ በሰልፍ የወሰዳቸውን ከተሞች የኢዮአካዝ ልጅ ዮአስ መልሶ ከአዛሄል ልጅ ከወልደ አዴር እጅ ወሰደ። ዮአስም ሦስት ጊዜ መታው፤ የእስራኤልንም ከተሞች መለሰ። |