2 ነገሥት 10 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)የአክአብ ወገኖች እንደ ተገደሉ 1 ለአክአብም በሰማርያ ሰባ ልጆች ነበሩት፤ ኢዩም ደብዳቤ ጽፎ፥ የአክአብን ልጆች ለሚያሳድጉ፥ ለሰማርያ አለቆችና ሽማግሌዎች ወደ ሰማርያ ላከ። 2 እንዲህም አለ፥ “ይህ ደብዳቤ አሁን በደረሳችሁ ጊዜ የጌታችሁ ልጆች ሰረገሎቹና ፈረሶቹም፥ የተመሸጉ ከተሞቹም፥ የጦር መሣሪያዎቹም በእናንተ ዘንድ አሉ፤ 3 ከጌታችሁ ልጆች ደስ የሚያሰኛችሁንና የሚሻላችሁን ምረጡ፤ በአባቱም ዙፋን አስቀምጡት፤ ስለ ጌታችሁም ቤት ተዋጉ።” 4 እነርሱም እጅግ ፈርተው፥ “እነሆ፥ ሁለቱ ነገሥታት በፊቱ ይቆሙ ዘንድ አልቻሉም፤ እኛስ እንዴት በፊቱ መቆም እንችላለን?” አሉ። 5 የአክአብም የቤቱ አለቆች፥ የከተማዪቱም አለቆች፥ ሽማግሌዎቹና ልጆቹንም የሚያሳድጉ፥ “እኛ አገልጋዮችህ ነን፤ ያዘዝኸንንም ሁሉ እናደርጋለን፤ የምናነግሠው ሰው የለም፤ የምትወድደውን አድርግ” ብለው ወደ ኢዩ ላኩ። 6 ከዚህም በኋላ ኢዩ፥ “ወገኖቼስ ከሆናችሁ፥ ነገሬንም ከሰማችሁ የጌታችሁን ልጆች ራስ ቍረጡ፤ ነገም በዚህ ሰዓት ወደ ኢይዝራኤል ወደ እኔ ይዛችሁ ኑ” ብሎ ሁለተኛ ደብዳቤ ጻፈላቸው። የንጉሡም ልጆች ሰባው ሰዎች በሚያሳድጓቸው በከተማዪቱ ታላላቆች ዘንድ ነበሩ። 7 ደብዳቤውም በደረሳቸው ጊዜ የሀገሩ ሰዎች የንጉሡን ልጆች ሰባውን ሰዎች ይዘው ገደሉአቸው፤ ራሳቸውንም በቅርጫት አድርገው ወደ እርሱ ወደ ኢይዝራኤል ላኩ። 8 መልእክተኛም መጥቶ፥ “የንጉሡን ልጆች ራስ ይዘው መጥተዋል” ብሎ ነገረው። ንጉሡም፥ “እስከ ነገ ድረስ በበሩ አደባባይ ሁለት ክምር አድርጋችሁ አኑሩአቸው” አለ። 9 በነጋውም ንጉሡ ወጥቶ ቆመ፤ ሕዝቡንም ሁሉ፥ “እናንተ ንጹሓን ናችሁ፤ እነሆ፥ የጌታዬን ቤት የወነጀልሁ የገደልኋቸውም እኔ ነኝ፤ እነዚህንስ ሁሉ የገደለ ማን ነው? 10 እነሆ፥ እግዚአብሔር በአክአብ ቤት ላይ ከተናገረው ከእግዚአብሔር ቃል በምድር ላይ አንዳች እንዳይወድቅ አሁን ዕወቁ፤ እግዚአብሔር በባሪያው በኤልያስ ቃል የተናገረውን አድርጎአል” አላቸው። 11 ኢዩም ከአክአብ ቤት በኢይዝራኤል የቀረውን ሁሉ፥ ታላላቆቹንም ሁሉ፥ ወዳጆቹንና ካህናቱን ሁሉ ገደላቸው፤ ከእነርሱ አንድስ እንኳ አላስቀረም። የአካዝያስ ዘመዶች እንደ ተገደሉ 12 ተነሥቶም ወደ ሰማርያ ሄደ፤ በመንገድም ወዳለው ወደ በግ ጠባቂዎች ቤት በደረሰ ጊዜ፥ 13 ኢዩ ከይሁዳ ንጉሥ ከአካዝያስ ወንድሞች ጋር ተገናኝቶ፥ “እናንተ እነማን ናችሁ?” አለ፤ እነርሱም፥ “እኛ የይሁዳ ንጉሥ የአካዝያስ ወንድሞች ነን፤ የንጉሡንና የእቴጌዪቱን ልጆች ደኅንነት እንነግረው ዘንድ ወረድን” አሉት። 14 እርሱም፥ “በሕይወታቸው ያዙአቸው” ብሎ አዘዘ። በበግ ጠባቂዎች ቤትም አጠገብ አርባ ሁለቱን ሰዎች ገደሉአቸው፤ ከእነርሱም አንድ ሰው እንኳ አላስቀረም። 15 ከዚያም በሄደ ጊዜ የሬካብን ልጅ ኢዮናዳብን በመንገድ አገኘው፤ ተቀብሎም መረቀው፤ ኢዩም፥ “ልቤ ከልብህ ጋር ቅን እንደ ሆነ ያህል ልብህ ከልቤ ጋር በቅንነት ነውን?” አለው። ኢዮናዳብም፥ “አዎን” አለው። ኢዩም፥ “እውነትህስ ከሆነ እጅህን ስጠኝ” አለ። እጁንም ሰጠው፤ ወደ እርሱም ወደ ሰረገላው አወጣው። 16 “ከእኔ ጋር ና፥ ለሠራዊት ጌታ ለእግዚአብሔርም እንደምቀና ታያለህ” አለው። ከእርሱም ጋር በሰረገላው አስቀመጠው። 17 ወደ ሰማርያም ገብቶ ለኤልያስ እንደ ተናገረው እንደ እግዚአብሔር ቃል እስኪያጠፋው ድረስ በሰማርያ የቀረውን የአክአብን ሰው ገደለ። በዓልን የሚያመልኩ ሁሉ እንደ ተገደሉ 18 ኢዩም ሕዝቡን ሁሉ ሰብስቦ፥ “አክአብ በዓልን በጥቂቱ አመለከው፤ ኢዩ ግን በብዙ ያመልከዋል። 19 አሁንም የበዓልን ነቢያት ሁሉ፥ አገልጋዮቹንም ሁሉ፥ ካህናቱንም ሁሉ ወደ እኔ ጥሩ፤ ማንም እንዳይቀር፤ ለበዓል ታላቅ መሥዋዕት አቀርባለሁ፤ የቀረውም ሁሉ በሕይወት አይኖርም” አላቸው። ኢዩ ግን የበዓልን አገልጋዮች ያጠፋ ዘንድ በተንኮል ይህን አደረገ። 20 ኢዩም፥ “ለበዓል መሥዋዕታችሁን አንጹ” አላቸው፤ እነርሱም አዋጅ ነገሩ። 21 ኢዩም ወደ እስራኤል ሀገሮች ሁሉ ላከ፤ የበዓልም አገልጋዮች ሁሉ፥ ካህናቱም ሁሉ፥ ነቢያቶቹም ሁሉ መጡ፤ ከእነርሱም ሳይመጣ የቀረ አንድ ሰው እንኳ አልነበረም። ሁሉም ወደ በዓል ቤት ገቡ፤ የበዓልንም ቤት ከዳር እስከ ዳር ድረስ ሞሉት። 22 የዕቃ ቤቱንም ሹም፥ “ለበዓል አገልጋዮች ሁሉ ልብስን አውጣ” አለው። የሚያለብሳቸውንም ልብሱን አወጣላቸው። 23 ኢዩና የሬካብ ልጅ ኢዮናዳብም ወደ በዓል ቤት ገቡ። የበዓልንም አገልጋዮች፥ “መርምሩ፥ ከበዓል አገልጋዮች ብቻ በቀር እግዚአብሔርን ከሚያመልኩ ወገን በእናንተ ዘንድ አንድ እንኳ እንዳይኖር ተመልከቱ” አላቸው። 24 የሚቃጠል መሥዋዕትና ሌላ መሥዋዕትም ያቀርቡ ዘንድ ገቡ፤ ኢዩም፥ “በእጃችሁ አሳልፌ ከምሰጣችሁ ሰዎች አንድ ሰው ያመለጠ እንደ ሆነ ነፍሱ በዚያ እንዲያመልጥ ባደረገው ሰው ነፍስ ፋንታ ትሆናለች” ብሎ በውጭ ሰማንያ ሰዎችን አዘጋጅቶ ነበር። 25 የሚቃጠለውንም መሥዋዕት አቅርበው በፈጸሙ ጊዜ ኢዩ ዘበኞቹንና አለቆቹን፥ “ግቡና ግደሉአቸው፤ አንድም አያምልጥ” አላቸው። በሰይፍም ስለት ገደሉአቸው፤ ዘበኞችና አለቆችም ወደ ውጭ ጣሉአቸው፤ ወደ በዓልም ቤት ከተማ ሄዱ። 26 ከበዓልም ቤት ሐውልቶቹን አወጡ፤ አቃጠሉአቸውም። 27 የበዓልን ሐውልት ቀጠቀጡ፤ የበዓልንም ቤት አፈረሱ፤ እስከ ዛሬም ድረስ የውዳቂ መጣያ አደረጉት። 28 እንዲሁም ኢዩ በዓልን ከእስራኤል አጠፋ። 29 ነገር ግን እስራኤልን ካሳተው ከናባጥ ልጅ ከኢዮርብዓም ኀጢአት ኢዩ አልራቀም፥ በቤቴልና በዳን የነበሩትን የወርቅ እንቦሶችንም፥ አላስወገደም። 30 እግዚአብሔርም ኢዩን፥ “በፊቴ ቅን ነገር አድርገሃልና፥ በልቤም ያለውን ሁሉ በአክአብ ቤት ላይ አድርገሃልና ልጆችህ እስከ አራት ትውልድ ድረስ በእስራኤል ዙፋን ላይ ይቀመጣሉ” አለው። 31 ኢዩ ግን በእስራኤል አምላክ በእግዚአብሔር ሕግ በፍጹም ልቡ ይሄድ ዘንድ አልተጠነቀቀም፤ እስራኤልንም ካሳተው ከኢዮርብዓም ኀጢአት አልራቀም። 32 በዚያም ወራት እዚአብሔር እስራኤልን ያጠፋ ጀመረ፤ አዛሄልም በእስራኤል ዳርቻ ሁሉ መታቸው። 33 በዮርዳኖስ ምሥራቅ ያለውን የገለዓድን ሀገር ሁሉ፥ በአርኖን ወንዝ አጠገብ ካለችው ከአሮዔር ጀምሮ የጋድንና የሮቤልን የምናሴንም ሀገር፥ ገለዓድንና ባሳንን መታ። 34 የቀረውም የኢዩ ነገር፥ የሠራውም ሥራ ሁሉ፥ ኀይሉም ሁሉ፥ የገደለውም ሁሉ እነሆ፥ በእስራኤል ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን? 35 ኢዩም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ በሰማርያም ቀበሩት። በፋንታውም ልጁ ኢዩአካዝ ነገሠ። 36 ኢዩም በሰማርያ በእስራኤል ላይ የነገሠበት ዘመን ሃያ ስምንት ዓመት ነበረ። |