Este libro no es inspirado por Dios y no forma parte del canon cristiano ni del Tanaj judío. Se muestra solo con fines históricos y de estudio. Ver explicación completa መጽሐፈ ዕዝራ ካልእ 9 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)1 ዕዝራም ከቤተ መቅደሱ አደባባይ ተነሥቶ ወደ ናሴሩ ልጅ ወደ ዮሐናን ቤት ሄደ። 2 በዚያም ተቀምጦ ስለ ታላላቆችና ብዙዎች ኀጢአቶቻቸው እያለቀሰ እህልን አልበላም፤ ውኃንም አልጠጣም። 3 ከዚህ በኋላ ከምርኮ ለተመለሱ ሁሉ በኢየሩሳሌም ይገኙ ዘንድ፥ 4 እስከ ሁለትና እስከ ሦስት ቀን ድረስ ያልተገኙና ያልደረሱ ሁሉ እንደ ሥርዐታቸው በአለቆቻቸው ቅጣት ይቀጡ ዘንድ፥ ከብቶቻቸውም ይወረሱ ዘንድ፥ እነርሱም ከወገኖቻቸው ይለዩ ዘንድ በይሁዳና በኢየሩሳሌም ዐዋጅ ነገረላቸው። 5 የይሁዳና የብንያም ወገኖችም በዘጠነኛው ወር በሃያኛው ቀን በሦስት ቀን ውስጥ በኢየሩሳሌም ተሰበሰቡ። 6 ሁሉም በቤተ መቅደሱ አደባባይ ተቀመጡ፤ ክረምት ነበርና ስለ ውርጩ ጽናት ይንቀጠቀጡ ነበር። 7 ዕዝራም ተነሥቶ እንዲህ አላቸው፥ “ከአሕዛብ ወገን ሚስት ያገባችሁ እናንተ በደላችሁ፤ በእስራኤልም ላይ ኀጢአትን ጨመራችሁ። 8 አሁንም ለእግዚአብሔር ተናዘዙ፤ የአባቶቻችንንም አምላክ አመስግኑት። 9 ፈቃዱንም ፈጽሙ፤ ከምድር አሕዛብና ከባዕዳት ሚስቶቻችሁም ተለዩ።” 10 ሁሉም በሙሉ በታላቅ ድምፅ ጮኸው እንዲህ አሉት፥ “እሺ አንተ እንዳዘዝኸን እናደርጋለን። 11 ነገር ግን ሰዉ ብዙ ነው፤ ጊዜውም ክረምት ነው፤ ፈጥነንም እናደርገው ዘንድ አንችልም፤ ሥራውም የአንድ ቀን ወይም የሁለት ቀን ሥራ አይደለም፤ በዚህ ፈጽመን በድለናልና። 12 አሁንም ከልዩ ወገን ሚስት ያገቡ መሳፍንት ሁሉና መንደረተኞችም ተሰብስበው ይምጡ። 13 በዚህ ሥራ ያገኘን የእግዚአብሔር ቍጣ ከእኛ ይርቅ ዘንድ መንደረተኞቻቸውንና ሽማግሌዎቻቸውን፥ አለቆቻቸውንም ይቅጠሯቸው።” 14 የአዛሄል ልጅ ዮናታን፥ የታቃኑ ልጅ ኢያዝያስም መጡ፤ ሞሶላሞስ፥ ሌዊ፥ ሳባጢዎስ፥ እነርሱም እንዲህ ተባበሩ። 15 ከምርኮ የተመለሱትም ሁሉ እንዲሁ አደረጉ። 16 ካህኑ ዕዝራም ካገሮቻቸው ሽማግሌዎች፥ በያገራቸውም ከሚኖሩት ሁሉ ስማቸው ልዩ ልዩ የሆነ ሰዎችን መረጠ፤ እንዲህም ያደርጉ ዘንድ እስከ ዐሥረኛው ወር መባቻ ድረስ ተቃጠሩ። 17 ከልዩ ወገን ሚስት ያገቡ እነዚያም ሰዎች ሁሉ “እስከ መጀመሪያው ወር መባቻ እንፈታለን” ብለው ነገራቸውን ጨረሱ። 18 ከካህናቱም ውስጥ ከባዕድ ወገን ሚስት ያገቡ ተገኙ። 19 እነርሱም የኢዮሴዴቅ ልጅ የኢያሱ ልጆችና ወንድሞቹ፥ ማቴላስ፥ አልዓዛር፥ ዮሬቦስና ዮአዳኖስም ናቸው። 20 ሚስቶቻቸውንም ፈትተው ስለ ኀጢአታቸው መሥዋዕት ይሠዉ ዘንድ ጀመሩ። 21 ከኤሞርም ልጆች ሐናንያ፥ ዘብዴዎስ፥ ሜኑስ፥ ሴሜዎስ፥ ኢያርማየልና አዛርያ ናቸው። 22 ከፌትርኤልም ልጆች ኢልዮኒስ፥ ማስያስ፥ አስማኤሎስ፥ ናትናአሎስ፥ ዎቅዲሎስና አልታሳ ናቸው። 23 ከሌዋውያንም ወገን ዮዛባዶስ፥ ሳምያስ፥ ቃሊጣስ የሚሉት ቆዮስ፥ ፋትያስ፥ ይሁዳና ዮናስ ናቸው። 24 ከመዘምራንም ወገን ኤልያሳቦስና ባካሮስ ናቸው። 25 ከበረኞችም ወገን ሴሎምና ጦልባኒስ ናቸው። 26 ከእስራኤል ከፎሮስ ልጆች ወገንም ኢየርማስ፥ ኤዝያስ፥ ሚልክያስ፥ ሚያኤሎስ፥ አልዓዛር፥ አስብያስ፥ ባኒያስ ናቸው። 27 ከኤላ ልጆች ወገን ማጣንያስ፥ ዘካርያስ፥ ኢያዚሬሎስ፥ አብድዮስ፥ ኢያሬሞትና ኤዲያስ ናቸው። 28 ከዛሞትም ልጆች ወገን ኤሊያዳስ፥ ኤሊያሲሞስ፥ ኦቶንያስ፥ ኢያሪሞስ፥ ሳባቶስ፥ ዘራሊያስ ናቸው። 29 ከቤባይም ልጆች ወገን ዮሐንስ፥ ሐናንያ፥ ዮዛብዴዎስ፥ አሜቴዎስ ናቸው። 30 ከማኒ ልጆችም ወገን ኦላሞስ፥ ማምኮስ፥ ኢያዴዎስ፥ ኢያሶቦስ፥ አስሔሎስ፥ ኢያርሞት ናቸው። 31 ከዓዲ ልጆችም ናሐቶስ፥ ሞሐስያስ፥ ለቁናስ፥ ኒዶስ፥ ቢስቀስ-ጰስሚስ ሲአቱል ባልኑስ፥ ሜናስያስ ናቸው፥ 32 ከሐናንያ ልጆችም ኢሊዮሳስ፥ አስያስ፥ ሚልክያስ፥ ስብያስ፥ ስምዖን፥ ኮሳሜዎስ ናቸው። 33 ከአሶም ልጆችም መልጠኒዎስ፥ መጣቲያስ፥ ሳባኔዎስ፥ ኤሌፍላት፥ ምናሴ፥ ሴሜይ ናቸው። 34 ከባኒ ልጆችም ኤርምያስ፥ ሞምዲስ፥ ስማኤል፥ ኢዮኤል፥ መምዲ፥ ጴዴያስ፥ አናስ፥ ቀሪባሶን፥ አናሲቦስ፥ መንጠኒሞስ፥ አልያሲስ፥ በኑስ፥ ኤልያሊ፥ ሰማይስ፥ ሰላምያስ፥ ናታንያስ ናቸው። ከኤዛርያስ ልጆችም ሴሲስ፥ ኤዝርል፥ አዛኤል፥ ሳማጢስ፥ ዘምበሪ፥ ኢዮሶፎስ ናቸው። 35 ከነሐማ ልጆችም ማዚጢያስ፥ ዘቢዲያስ፥ ኤዴስ፥ ኢዮኤል፥ በኒያስ ናቸው። 36 ከባዕዳን ከአሕዛብ ወገን ሚስት ያገቡት ሰዎች ሁሉ ሚስቶቻችውን ሁሉ ከልጆቻቸው ጋር አስወጧቸው። 37 ካህናትና ሌዋውያንም፥ ብዙዎች እስራኤልም በሰባተኛው ወር መባቻ በኢየሩሳሌም በያገራቸው ተቀመጡ፤ የእስራኤልም ልጆች በየአውራጃቸው ተመለሱ። 38 በቤተ መቅደሱ በር በምሥራቃዊው አደባባይ ሁሉም በአንድነት ተሰበሰቡ። 39 ካህኑንና ጸሓፊዉን ዕዝራንም የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር የሰጠውን የሙሴን ሕግ ያመጣ ዘንድ ነገሩት። 40 የካህናት አለቃ ዕዝራም በሰባተኛው ወር መባቻ ለሕዝቡ፥ ለወንዶችም፥ ለሴቶችም ለካህናቱም ሁሉ ሕጉን ይሰሙ ዘንድ አነበበላቸው። 41 በቤተ መቅደሱም በር ባለው አደባባይ በወንዶቹና በሴቶቹ ፊት ከነግህ ጀምሮ እስከ ቀትር ድረስ አነበበላቸው፤ ሁሉም በፍጹም ልባቸው ሕጉን አደመጡ። 42 ካህኑና የሕጉ ጸሓፊ ዕዝራም ከእንጨት በተሠራ መረባርብ ላይ ቆመ። 43 ከእርሱም ጋር፦ መተጢያስን፥ ሳሙስን፥ ሐናንያን፥ አዛርያን፥ ኡርያስን፥ ሕዝቅያስን፥ በአልስሞስንም በቀኙ አቆማቸው። 44 በግራውም በኩል ፈሐልዴዎስን፥ ሚሳኤልን፥ ሚልክያስን፥ ሎታሳብስን፥ ናባሪያንና ዘካርያስን አቆመ። 45 ዕዝራም ያን መጽሐፍ ይዞ በሕዝቡ ፊት ተቀመጠ፤ ሕዝቡም ሁሉ ያከብሩት ነበር። 46 የሕጉንም መጽሐፍ በገለጠ ጊዜ ሕዝቡ ሁሉ ተነሥተው ቆሙ፤ አዛርያም ሁሉን የሚገዛ ልዑል እግዚአብሔርን አመሰገነው። 47 ሁሉም በሙሉ፥ “አሜን፥ አሜን” ብለው መለሱለት፤ እጆቻቸውንም ወደ ላይ አንሥተው በምድር ወድቀው ለእግዚአብሔር ሰገዱ። 48 ሌዋውያኑም ኢያሱ፥ አኑሲ፥ ሰራቢያስ፥ ኢያዲኖስ፥ ኢያቆብስ፥ ሳብጣያስ፥ አውጥያስ፥ ሚሐና፥ ቀሊጦስ፥ አዛርያ፥ ጠዛብዶስ፥ ሐኒያስ፥ ፈልጣስ የእግዚአብሔርን ሕግ አስተማሯቸው። 49 ባነበበላቸውም ጊዜ ሁሉም በአንድነት ሆነው ሰሙ። 50 አጠራጢም የካህናቱን አለቃና ጸሓፊውን ዕዝራን፥ ለሁሉ የሚያስተምሩ ሌዋውያንንም እንዲህ አላቸው፦ 51 “ይቺ ቀን ለእግዚአብሔር የተቀደሰች ናት፥” ሁሉም ሕጉን በሰሙ ጊዜ አለቀሱ። 52 እንዲህም ተባባሉ፥ “ሂዱና ምሳችሁን ብሉ፤ ጠጡም፤ ለሌላቸውም ሰዎች ምጽዋትን ላኩ። ይቺ ቀን ለእግዚአብሔር የተቀደሰች ናትና፥ አትዘኑም፤ እግዚአብሔር አይጥላችሁምና።” 53 ሌዋውያንም ሕዝቡን ሁሉ እንዲህ ብለው አዘዙ “ይቺ ቀን የተቀደሰች ናትና አትዘኑ።” 54 ሁሉም ሊበሉና ሊጠጡ፥ ደስታም ሊያደርጉ፥ ለሌላቸውም ሰዎች ምጽዋትን ሊሰጡ ሄዱ። 55 በተሰበሰቡበት ቦታም ያስተማሯቸውን ቃል በሰሙ ጊዜ ታላቅ ደስታን አደረጉ። |