Este libro no es inspirado por Dios y no forma parte del canon cristiano ni del Tanaj judío. Se muestra solo con fines históricos y de estudio. Ver explicación completa መጽሐፈ ዕዝራ ካልእ 8 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ዕዝራ ወደ ኢየሩሳሌም እንደ መጣ 1 ከዚህም በኋላ በፋርስ ንጉሥ በአርጤክስስ መንግሥት ዕዝራ መጣ፤ እርሱም የሠራያ ልጅ፥ የአዛርያስ ልጅ፥ የኬልቅዩ ልጅ፥ የሴሎም ልጅ፤ 2 የሳዶቅ ልጅ፥ የአኪጦብ ልጅ፥ የአማርትዩ ልጅ፥ የአዝያን ልጅ፥ የቡቂ ልጅ፥ የአቢሱ ልጅ፥ የፊንሐስ ልጅ፥ የአልዓዛር ልጅ፥ የመጀመሪያው ካህን የአሮን ልጅ፤ 3 ይህም ዕዝራ ከባቢሎን መጣ፤ እርሱም የእስራኤል አምላክ የሰጠውን የሙሴን ኦሪት ሁሉ ያውቅ ነበረ፤ እርሱም ጸሓፊ ነበር። 4 ንጉሡም ክብርን ሰጠው፤ በፊቱ ባለሟልነትን አግኝትዋልና፥ በሁሉም ላይ ሹሞታልና። 5 ከእስራኤልም ልጆች፥ ከካህናቱና ከሌዋውያኑ፥ ከመዘምራኑና ከበረኞች፥ ከቤተ መቅደስ አገልጋዮችም፥ ዐያሌዎቹ ወደ ኢየሩሳሌም ወጡ። 6 በአርጤክስስ በሰባተኛው ዓመተ መንግሥቱ፥ በአምስተኛው ወር፥ በወሩ መባቻ ከባቢሎን ወጡ፤ እግዚአብሔርም መንገዳቸውን እንዳቀናላቸው በመጀመሪያው ወር መባቻ ወደ ኢየሩሳሌም ደረሱ። 7 ዕዝራም ብዙ ትምህርት የሚያውቅ ነበረ፤ ለእስራኤልም ሥርዐትንና ፍርድን ያስተምር ዘንድ ከእግዚአብሔር ሕግና ትእዛዝ የሚጐድለው አልነበረም። ንጉሥ አርጤክስስ ለዕዝራ የሚፈልገው ሁሉ እንዲደረግለት የሰጠው ትእዛዝ 8 ንጉሡ አርጤክስስም ወደ ካህኑና የእግዚአብሔርን ሕግ ወደሚጽፈው ወደ ዕዝራ ደብዳቤ ላከ። ከአርጤክስስም የእግዚአብሔርን ሕግ ወደሚጽፈው ወደ ካህኑ ዕዝራ የተላከው ደብዳቤ እንዲህ ይላል፦ 9 “ከንጉሠ ነገሥት ከአርጤክስስ ለእግዚአብሔር ሕግ ጸሓፊ፥ ለካህኑ ለዕዝራ ሰላም ለአንተ ይሁን፤ 10 እኔ ሰውን በመውደድ አስቤ ከአይሁድ ወገን በመንግሥቴ ካሉ ከካህናትና ከሌዋውያን ወደ ኢየሩሳሌም ይሄዱ ዘንድ የሚወዱትን ሁሉ ከአንተ ጋር ይሂዱ ብዬ አዝዣለሁ። 11 ወደ ኢየሩሳሌምም ይሄዱ ዘንድ የሚወዱ ሁሉ ይሁዳንና ኢየሩሳሌምን አይተው ከእናንተ ጋር ይተባበሩ። 12 እንደ እግዚአብሔር ሕግ ሄደው ያደርጉ ዘንድ እኔና ሰባቱ ባለሟሎች፥ አማካሪዎችም እንዲህ አዝዘናል። 13 እኔና ባለሟሎች የተሳልነውን ቍርባን፥ በባቢሎን ሀገር የተገኘውንም ወርቁንና ብሩን ሁሉ በኢየሩሳሌም ለእግዚአብሔር ያቀርቡ ዘንድ፥ 14 ሕዝቡ በኢየሩሳሌም ባለው በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ከሚያገቡት ስእለት ጋራ ወርቁንና ብሩን፥ ለበሬዎች፥ ለፍየሎችና ለበጎች መግዣ ይሰብስቡ፥ 15 እንደ ሥርዐታቸው በኢየሩሳሌም ባለው በእግዚአብሔር መሠዊያ መሥዋዕት ይሠዉ ዘንድ፥ 16 ለሚያስፈልጋቸው ሁሉ፥ ከባልንጀራህ ጋር ታደርገው ዘንድ የምትወደውን ሁሉ በዚህ ወርቅና ብር እንደ አምላክህ ፈቃድ አድርግ። 17 በኢየሩሳሌም ላለ ለአምላክህ ቤተ መቅደስ ግዳጅ የሚሆነውን ንዋያተ ቅድሳት። 18 ለአምላክህ ቤተ መቅደስ ግዳጅ የምትሻው ሌላም ቢኖር ከንጉሡ ዕቃ ቤት እሰጣለሁ። 19 “እኔ ንጉሥ አርጤክስስ የልዑል እግዚአብሔርን ሕግ የሚጽፍ ካህኑ ዕዝራ የሚጠይቀውን ሁሉ በሶርያና በፊንቂስ ካለው ዕቃ ቤት እንዲሰጡት አዘዝሁ። ስጡ፤ እንቢም አትበሉ። 20 እስከ መቶ መክሊት ብር፥ ዳግመኛም እስከ መቶ የቆሮስ መስፈሪያ ስንዴ፥ እስከ መቶም የኔባል መስፈሪያ ወይን፥ ብዙ ጨውም ቢሆን ስጡ። 21 በንጉሥ መንግሥትና በልጆቹ ላይ መከራ እንዳይመጣ በልዑል እግዚአብሔር ሕግ ይሥሩ። 22 ከካህናቱና ከሌዋውያኑ፥ ከመዘምራኑና ከበረኞቹ ግብር አትቀበሉ። ከቤተ መቅደስም አገልጋዮች፥ ተቀጥረው ቤተ መቅደስን ከሚያገለግሉ ሁሉ ምንም አትቀበሉ፥ አትግዟቸውም። 23 “አንተም ዕዝራ! እግዚአብሔር በገለጠልህ ጥበብ የአምላክን ሕግ ከሚያውቁ ወገኖች ውስጥ ሶርያንና ፊንቂስን የሚገዙ መኳንንቱንና መሳፍንቱን ሹም፤ የእግዚአብሔርን ሕግ የማያውቁትንም አስተምራቸው። 24 የአምላክህን ሕግና የንጉሡን ትእዛዝ የሚተላለፈውንም ሁሉ ቸል አትበሉ፤ ቅጡ፤ በሞትም ቢሆን፥ በግርፋትም ቢሆን፥ በባርነትም ቢሆን፥ በመውረስም ቢሆን፥ ሁሉንም በየኀጢአቱ ቅጡት።” ዕዝራ አምላኩን እንዳመሰገነ 25 ዕዝራም እንዲህ አለ፥ “በኢየሩሳሌም ያለውን የእግዚአብሔርን ቤት ያከብር ዘንድ ይህን ነገር በንጉሥ ልብ ያሳደረ እግዚአብሔር ይመስገን። 26 በነገሥታቱና በአማካሪዎቹ፥ በወዳጆቹና በመኳንንቱ ሁሉ ፊት እኔን አክብሮኛልና። 27 ከዚህም በኋላ በፈጣሪዬ በእግዚአብሔር ጸጋ ታመንሁ። ከእኔም ጋር ይወጡ ዘንድ ከእስራኤል ሰዎችን ወሰድሁ።” ከምርኮ የተመለሱ 28 በንጉሡ በአርጤክስስ መንግሥት በየሀገራቸውና በየአውራጃቸው ግዛት ከእኔ ጋር ከባቢሎን የወጡ አለቆችም እነዚህ ናቸው። 29 ከፎሮስ ልጆች ጣስጣሞስ፥ ከኢዮጥማሩም ልጆች ጋሜሎስ፥ ከዳዊትም ልጆች የሴኬንያስ ልጅ አጡስ፥ 30 ከፋሬስም ልጆች ዘካርያስ፥ ከእርሱም ጋር መቶ አምሳ ሰዎች ተቈጠሩ። 31 ከፎአት ሞዓብም ልጆች የዛርያ ልጅ ኤሊዎንያ፥ ከእርሱም ጋር ሁለት መቶ ሰዎች። 32 ከዘቶይስም ልጆች የኢያሐቲሉ ልጅ ኢያኬንያስ፥ ከእርሱም ጋር ሁለት መቶ ሰዎች፥ ከአዲኑ ልጆች የዮናታን ልጅ ኦቤድ፥ ከእርሱም ጋር ሁለት መቶ አምሳ ሰዎች። 33 ከኤላም ልጆች የጎቶልያ ልጅ ኢሴይ፥ ከእርሱም ጋር ሰባ ሰዎች። 34 ከሳፋጢ ልጆች የሚካኤል ልጅ ዛርያስ፥ ከእርሱም ጋር ሰባ ሰዎች። 35 ከኢዮአብም ልጆች የኢዝኤል ልጅ ኦባድያ፥ ከእርሱም ጋር ሁለት መቶ ዐሥራ ሁለት ሰዎች። 36 ከባኒ ልጆችም የኢዮሳፌይ ልጅ አስሊሞት፥ ከእርሱም ጋር መቶ ስድሳ ሰዎች። 37 ከቤዔር ልጆችም የባቢ ልጅ ዘካርያስ፥ ከርሱም ጋር ሃያ ስምንት ሰዎች። 38 ከአሰጣያትም ልጆች የአዝጋድ ልጅ ዮሐንስ፥ ከርሱም ጋር መቶ ዐሥር ሰዎች። 39 ከአዶኒቃም ልጆች የቀሩት ሁሉ ስማቸው ይህ ነው፦ ኤሊፋሊ፥ ይዑኤል፥ ሰሚያስ፥ ከእነርሱም ጋራ ሰባ ሰዎች። 40 ከቤኑስም ልጆች የአስጣስቆሩ ልጅ ዑታይ ከእርሱም ጋራ ሰባ ሰዎች ተቈጠሩ። ዕዝራ የቤተ መቅደስ ካህናትና ሌዋውያንን እንዳገኘ 41 ቴራን ወደሚባል ወንዝም ሰበሰብኋቸው፤ በዚያም ሦስት ቀን አደርን፤ አስቈጠርኋቸውም። 42 ከውስጣቸውም ካህናትንና ሌዋውያንን አላገኘንም። 43 ወደ አልዓዛርም ላክሁ፤ ከእኔም ጋር መአስመንን፥ አንዐጣንን፥ ሰምያስን፥ ኢዮሪቦን፥ ናታንን፥ አርጦንን፥ ዘካርያስን፥ ሞሱላሞስን ወሰድሁ። 44 ከእነርሱም ጋር ከመሳፍንቶቻቸውና ከዐዋቂዎቻቸው ወሰድሁ። 45 ወደ ዕቃ ቤቱም ሹም ወደ ያድዮን ይሄዱ ዘንድ ነገርኋቸው። 46 ለእግዚአብሔርም ቤት ካህናትን እንዲልኩልን ለያድዮንና ለወንድሞቹ፥ በዚያም ቦታ ለአሉ ሰዎች ይነግሯቸው ዘንድ አዘዝኋቸው። 47 ከእስራኤል ልጅ ከሌዊ ልጅ ከሞሐሊ ልጆች ጠቢባን ሰዎችን አሲብያንና ልጆቹን፥ ዐሥራ ስምንት ወንድሞቹንም አመጡልን፥ 48 ከከዓኑ ልጆችና ከልጆቻቸውም ውስጥ የሆኑ ሃያ ሰዎች፥ 49 ዳዊት የሠራቸው የቤተ መቅደስ አገልጋዮችና አለቆቻቸው ለሌዋውያን ሥራ የተጨመሩ የካህናት ልጆች ሁለት መቶ ሃያ ናቸው፤ የሁሉም ስማቸው ተጻፈ። ዕዝራ ጾምን እንዳወጀ 50 በአምላካችን በእግዚአብሔርም ፊት ከልጆቻችን ጋራ በዚያ እንጾም ዘንድ ለልጆቻችንና ለከብቶቻችንም ይቅርታን እንለምን ዘንድ ተሳልን። 51 ሀገራችንን የሚያጸኑና ከጠላቶቻችን ጋራ የሚመካከቱ እግረኞችንና ፈረሰኞችን እንዲሰጠን ለንጉሡ እልክ ዘንድ አፍሬአለሁና። 52 ሥራውን ሁሉ ያቀናላቸው ዘንድ ከሚፈልጉት ሰዎች ጋራ የጌታችን ከሃሊነት እንደሚኖር ለንጉሡ ነግረነው ነበርና። 53 ዳግመኛም ስለዚህ ሁሉ ወደ እግዚአብሔር ለመን፤ እርሱም ይቅር አለን። ለቤተ መቅደስ ሥራ የቀረበ መባእ 54 ከሕዝቡና ከካህናቱ ሹሞች ዐሥራ ሁለቱን ሰዎች፥ ኤሴርያንና አሴሚያን፥ ከእነርሱም ጋር ከወንድሞቻቸው መካከል ዐሥር ሰዎችን ለየሁ። 55 ንጉሡና መኳንንቱ፥ አማካሪዎቹም እስራኤልም ሁሉ የሰጡንን ወርቁንና ብሩን የእግዚአብሔርንም ቤት ንዋየ ቅድሳት መዝኜ ሰጠኋቸው። 56 ስድስት መቶ አምሳ መክሊት ብርም መዝኜ ሰጠኋቸው። 57 መቶ መክሊት የብር ዕቃ፥ መቶ መክሊትም ወርቅ፥ ሃያ መክሊትም የወርቅ ዕቃ፥ የሚወደድ እንደ ወርቅም የጠራና የጠነከረ ዐሥራ ሁለት የናስ ዕቃ መዝኜ ሰጠኋቸው። 58 እንዲህም አልኋቸው፥ “እናንተም ለእግዚአብሔር ተለዩ፥ ለአባቶቻችን ፈጣሪ ለእግዚአብሔር ስእለት የሆነውን የብሩንና የወርቁን ንዋየ ቅድሳትም ለዩ። 59 ለመሳፍንቱና ለመኳንንቱ፥ ለካህናቱ አለቆችና ለሌዋውያኑ፥ ለእስራኤልም ሀገሮች አለቆች በኢየሩሳሌም በአምላካችን ቤት አዳራሽ ውስጥ እስክትሰጧቸው ድረስ ተግታችሁ ጠብቁ።” 60 ካህናቱና ሌዋውያኑም የተቀበሉትን ወርቁንና ብሩን፥ የኢየሩሳሌምንም ንዋየ ቅድሳት ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ አገቡ። ወደ ኢየሩሳሌም የተመለሱት ሕዝብ 61 በመጀመሪያው ወር በዐሥራ ሁለተኛው ቀን ቴራን ከሚባል ሀገር ተነሡ፤ ከጠላቶቻችን ሁሉ ባዳነን፥ በፈጣሪያችን ከእኛ ጋር ባለች ጽንዕት እጅም ወደ ኢየሩሳሌም ደረሱ። 62 በደረሱ በሦስተኛውም ቀን ወርቁንና ብሩን መዝነውና ቈጥረው በቤተ እግዚአብሔር ለኦርያ ልጅ ለካህኑ ለመርሞቲዮራ ሰጡት። 63 የሁሉም ልኩ፥ ሚዛኑም ያንጊዜ ተጻፈ። 64 ከእርሱም ጋር የፊንሐስ ልጅ አልዓዛር ነበረ፤ ከእነርሱም ጋር ሌዋውያኑ የኢያሱ ልጅ የዘባትና የብኑ ልጅ ሞኢተስ ነበሩ። 65 ከምርኮ የተመለሱትም ለእስራኤል አምላክ ለእግዚአብሔር መሥዋዕት አቀረቡ። ዐሥራ ሁለት ኮርማዎችን፥ ዘጠና ስድስት በጎችን፥ 66 ስለ ድኅነትም ሰባ ስድስት ሙክቶችን፥ ዐሥራ ሁለት የበግ ጠቦቶችን፥ ሁሉንም ለእግዚአብሔር ሰዉ። 67 ከዚህም በኋላ ለንጉሡ ዕቃ ቤት ሹሞች፥ ለሶርያና ለፊንቂ ገዦችም ከንጉሡ የመጣውን ደብዳቤ ሰጧቸው፤ ሕዝቡንና የእግዚአብሔርንም መቅደስ አከበሩ። ዕዝራ ከአሕዛብ ጋር የተደረገውን ጋብቻ እንደ ተቃወመ 68 ከዚህም በኋላ ሹሞች መጥተው የሠሩትን ነገሩኝ። 69 እንዲህም አሉኝ፥ “የእስራኤል ወገኖች፥ መኳንንቶቻቸውም፥ ካህኖቻቸውም፥ ሌዋውያኑም ከሌሎች የምድር አሕዛብ ከከናኔዎን፥ ከፌሬዜዎን፥ ከኬጤዎንም፥ ከኢያቡሴዎን፥ ከሞዓባውያን፥ ከግብፃውያንና ከኤዶሜዎን ርኵሰት አልተለዩም። 70 ሴቶች ልጆቻቸውን አገቡ፤ እነርሱና ልጆቻቸውም የከበረውን ዘር ከባዕዳን የምድር አሕዛብ ጋር ቀላቀሉ፤ መሳፍንቶቻቸውና መኳንንቶቻቸውም ከመጀመሪያው ሥራቸው ጀምሮ በዚያች ኀጢአት አንድ ሆኑ።” 71 ከዚህም በኋላ ይህን በሰማሁ ጊዜ ልብሴንና ልብሰ ተክህኖዬን ቀደድሁ፤ የራሴን ጠጕርና ጢሜንም ነጨሁ፤ ተክዤና አዝኜም ተቀመጥሁ። 72 እኔም በዚያች ኀጢአት አዝኜና ተክዤ ተቀምጬ ሳለሁ የእስራኤል ፈጣሪ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ የሚፈሩ ሁሉ ወደ እኔ ተሰበሰቡ። 73 ከዚህም በኋላ በሠርኩ መሥዋዕት ጊዜ ጾመኛ እንደ ሆንሁ ልብሴና የክህነት ልብሴ እንደ ተቀደደ ሆኖ ተነሣሁ፤ በጉልበቴም ተንበረከክሁ፤ እጆችንም ወደ እግዚአብሔር ዘረጋሁ። 74 እንዲህም አልሁ፥ “አቤቱ ጌታዬ ከፊትህ የተነሣ አፍራለሁ፤ እፈራለሁም። 75 ኀጢአታችን በዝትዋልና፥ ከራሳችንም ከፍ ከፍ ብሏልና፥ አለማወቃችንም እስከ ሰማይ ደርሷልና። 76 ከአባቶቻችን ዘመን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ በታላቅ ኀጢአት ላይ ኖረናል። 77 በእኛ ኀጢአትና በአባቶቻችንም ኀጢአት የምድር ነገሥታት ከወንድሞቻችንና ከንጉሦቻችን፥ ከካህኖቻችንም ጋር ማረኩን፤ በጦራቸውም ዘረፉን፤ እስከ ዛሬም ድረስ አፈርን። 78 አሁን ግን በዚያች በተቀደሰችው ቦታህ ሥርንና ስምን ትተውልን ዘንድ እግዚአብሔር ሆይ ቸርነትህ በእኛ ላይ በዝታ ተደረገችልን። 79 በአንተም በአምላካችን ቤት ብርሃን ተገለጠልን፤ ተገዥዎችም በሆንን ጊዜ ምግባችንን ሰጠኸን። 80 በተገዛንም ጊዜ አንተ አምላካችን አልተውኸንም፤ በፋርስ ነገሥታትም ፊት ሞገስን ሰጠኸን፤ ምግባችንን ይሰጡን ዘንድ፥ 81 ቤተ መቅደሳችንንም ያከብሩ ዘንድ፥ የጽዮንንም ፍራሿን ይሠሩ ዘንድ፥ በይሁዳና በኢየሩሳሌምም ኀይልን ይሰጡን ዘንድ አልተውኸንም። 82 “አቤቱ፥ አሁንስ ይህ በእኛ ላይ ሳለ ምን እንላለን? በባሮችህ በነቢያትም እጅ እንዲህ ስትል የሰጠኸውን ትእዛዝህን ካድን። 83 ትወርሷት ዘንድ ወደ እርሷ ትገባላችሁ ያልሃቸው ያች ምድር በምድር አሕዛብ ርኵሰት የተዳደፈች ምድር ናት፤ ርኵሰታቸውንም መሏት። 84 ሴቶች ልጆቻችሁን ለወንዶች ልጆቻቸው አታጋቡ፤ ሴቶች ልጆቻቸውንም ለወንዶች ልጆቻችሁ አታጋቡ፤ 85 ድል ትነሷቸው ዘንድ፥ የምድርንም በረከት ትበሉ ዘንድ፥ ለልጆቻችሁ ለዘለዓለሙ ታወርሷት ዘንድ በዘመናችሁ ሁሉ ከእነርሱ ጋር አትስማሙ። 86 ይህችም ያገኘችን ሁሉ ስለ ሥራችን ክፋትና ስለ ኀጢአታችን ብዛት ነው። 87 አቤቱ አንተ ግን ኀጢአታችንን ታገሥህ፤ እንመለስም ዘንድ ሥርን ሰጠኸን፤ ዳግመኛም ሕግህን አፍርሰን ከምድር አሕዛብ ርኩሰት ጋር አንድ እንሆን ዘንድ ይገባናልን? 88 ብትቈጣንስ ሥርንና ዘርን፥ ስማችንንም እስከማታስቀር ድረስ ባጠፋኸን ነበር። 89 አቤቱ የእስራኤል አምላክ አንተ፥ እውነተኛ ነህ፥ ዛሬ ሥርን ትተህልናልና። 90 አሁንም በፊትህ በኀጢአታችን አለን። ስለዚህ በፊትህ እንቆም ዘንድ አይገባንም።” 91 ዕዝራም በቤተ መቅደሱ አንጻር ተንበርክኮ እያለቀሰ በጸለየና በተናዘዘ ጊዜ በኢየሩሳሌም ያሉ ብዙ ሰዎች ሴቶችና ወንዶች፥ ቆነጃጅቱም ወደ እርሱ ተሰበሰቡ፤ በሁሉም ላይ ታላቅ ልቅሶ ሆነ። 92 ከእስራኤልም ልጆች ውስጥ የኢያኤል ልጅ ኢኮንያስ ዕዝራን ጠርቶ እንዲህ አለው፥ “ልዩ ከሚሆኑ ከምድር አሕዛብ ወገን ሚስት ያገባን እኛ እግዚአብሔርን በድለናል፤ አሁንም ይህ ሁሉ በእስራኤል ዘንድ አለ። 93 ነገር ግን እንደ ፍርድህ ልዩ ከሚሆኑ ከምድር አሕዛብ ወገን ያገባናቸውን ሚስቶቻችንን ሁሉ ከልጆቻቸው ጋራ ከእኛ እናስወጣቸው ዘንድ በእግዚአብሔር ስም እንማማል። 94 የእግዚአብሔርን ሕግ የሚወዱ ሰዎችንም ሁሉ ተነሥተህ አምላቸው። 95 ይህ ሥራ ባንተ ላይ ነውና፥ እኛም ካንተ ጋር ነንና፥ እንረዳሃለንምና።” 96 ዕዝራም ተነሥቶ የሕዝቡን ሹሞችና ካህናቱን፥ ሌዋውያኑንም፥ እስራኤልንም ሁሉ እንዲሁ ያደርጉ ዘንድ አማላቸው፤ እነርሱም ማሉ። |