Este libro no es inspirado por Dios y no forma parte del canon cristiano ni del Tanaj judío. Se muestra solo con fines históricos y de estudio. Ver explicación completa መጽሐፈ ዕዝራ ካልእ 3 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)የሦስቱ ጠባቂዎች ውድድር 1 ንጉሡ ዳርዮስም በመንግሥቱ ላሉ ሁሉ ለቤተ ሰዎቹ፥ ለሜዶንና ለፋርስ መኳንንት ሁሉ፥ 2 ለመሳፍንቱ ሁሉ፥ በሥሩ ለሚገኙ ከሕንድ እስከ ኢትዮጵያ ባሉ መቶ ሃያ ሰባት ግዛቶች ላሉ አዛዦችና ሹሞች ሁሉ ታላቅ በዓል አደረገ። 3 በልተውና ጠጥተውም ጠገቡ፤ ከዚህም በኋላ ወደ ቤታቸው ገቡ፤ ንጉሡ ዳርዮስም ወደ እልፍኙ ገብቶ ተኛ። 4 ንጉሡንም የሚጠብቁት ሦስት ጐልማሶች ራስ ጠባቂዎች ነበሩ። እርስ በርሳቸውም እንዲህ ተባባሉ፦ 5 “ሁላችን የሚያስጐመጅና የሚወደድ አንዳንድ ቃል አሻሽለን እንናገር ዘንድ ኑ፤ ነገሩ በጥበብ ከባልንጀራው ለተሻለለት ንጉሡ ዳርዮስ ብዙ ስጦታ ይስጠው፤ የአሸናፊነቱንም ዋጋ ይስጠው። 6 ነጭ ሐርም ያልብሰው፤ በወርቅ ጽዋም ይጠጣ፤ በወርቅ አልጋም ይተኛ፤ በወርቅ ሰረገላም ላይ ይቀመጥ፤ ከተልባ እግርም የተሠራ መጠምጠሚያ በራሱ ላይ ያድርግ፤ በአንገቱም ላይ ዝርግፍ ወርቅ ይሰር። 7 ስለ ጥበቡም ከንጉሡ ቀጥሎ ይቀመጥ፤ የንጉሡም ዘመድ ይሁን።” 8 ከዚህም በኋላ ሁሉም የየራሳቸውን ቃል ጻፉ፤ አትመውም ከንጉሡ ከዳርዮስ መከዳ በታች አኖሩት። 9 እንዲህም አሉ፥ “ንጉሡ ከዕንቅልፉ በነቃ ጊዜ ይህቺን ደብዳቤ እንሰጠዋለን፤ ንጉሡና ሦስቱ የፋርስ ሹሞቹም በቃሉ ለተወደደውና ብልህ ለሆነው ይፍረዱለት።” 10 አንደኛው “ወይን ያሸንፋል” ብሎ ጻፈ። 11 ሁለተኛውም “ንጉሥ ያሸንፋል” ብሎ ጻፈ። 12 ሦስተኛውም “ሴቶች ያሸንፋሉ፤ ከሁሉም ይልቅ እውነት ታሸንፋለች” ብሎ ጻፈ። 13 ከዚህም በኋላ ዳርዮስ በነቃ ጊዜ ያቺን መጽሐፍ አንሥተው ሰጡት፤ አነበባትም። 14 በሜዶንና በፋርስ ያሉ አዛዦችን ሁሉ፥ መሳፍንቱንና ሹሞቹን፥ አለቆቹንና መኳንንቱንም ወደ አዳራሹ ይጠሩ ዘንድ ላከ፤ 15 በአጠገቡም ተቀምጠው ያችን መጽሐፍ በፊታቸው አስነበቧት። 16 እርሱም፥ “እነዚያን ጐልማሶች ሰዎች ጥሯቸው፤ እነርሱ ራሳቸው ነገራቸውን ይናገሩ” አለ፤ ጠርተውም አገቡአቸው። ስለ ወይን አሸናፊነት የቀረበው ሐተታ 17 እንዲህም አላቸው፥ “ነገራችሁን ተናገሩ፥” ወይን ያሸንፋል ብሎ መጀመሪያ የተናገረውም ይናገር ጀመር። 18 እንዲህም አለ፥ “እናንተ ሰዎች፥ ወይን የሚጠጣውን ሰው ሁሉ እንደሚያሸንፈው፥ አእምሮውንም እንደሚያሳጣው አስተውሉ። 19 የንጉሡንና የድኃ አደጉን፥ የባሪያዉንና የነጻዉን፥ የድኃውንና የባለጸጋውን ልቡና አንድ ያደርገዋል። 20 የሰውን ሁሉ ልቡና ወደ ደስታ መልሶ ደስ ያሰኛቸዋል፤ ኀዘኑንም ሁሉ አያስቡትም፤ ጭንቀቱንም ሁሉ አያስቡትም። 21 የሰውን ሁሉ ልቡና ባለ ጸጋ ያደርገዋል፤ ንጉሡንም አያስቡትም፤ ፈጣሪያቸውንም አያስቡትም ሰውንም ሁሉ ከባድ ነገር ያናግረዋል። 22 በጠጡትም ጊዜ ወዳጅ ወዳጁን፥ ወንድምም ወንድሙን ይረሳዋል፥ ሾተላቸውንም ያማዝዛቸዋል። 23 ከስካራቸውም በነቁ ጊዜ ያደረጉትን አያስቡትም። 24 እናንተ ሰዎች፥ በግድ እንዲህ የሚያደርገው ወይን አያሸንፍምን?” ከዚህም በኋላ እርሱ እንዲህ ብሎ ተናግሮ ዝም አለ። |