Este libro no es inspirado por Dios y no forma parte del canon cristiano ni del Tanaj judío. Se muestra solo con fines históricos y de estudio. Ver explicación completa መጽሐፈ ዕዝራ ካልእ 2 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)1 በፋርስ ንጉሥ በቂሮስ መንግሥት በመጀመሪያዪቱ ዓመት እግዚአብሔር በነቢዩ በኤርምያስ አፍ የተናገረው ቃል ደረሰ። 2 እግዚአብሔርም የፋርስን ንጉሥ የቂሮስን መንፈስ አነሣሣ፤ በመንግሥቱም ሁሉ ዐዋጅ ነገረ፤ እንዲህም ብሎ ጻፈ። 3 የፋርስ ንጉሥ ቂሮስ እንዲህ ይላል፥ “የእስራኤል አምላክ ልዑል እግዚአብሔር እኔን ለዘለዓለም አነገሠኝ። 4 በይሁዳ ባለችው በኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስን እሠራለት ዘንድ አዘዘኝ፤ 5 ስለዚህ ከእናንተ ውስጥ ከሕዝቡ ወገን የሆነ ቢኖር እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ይሁን፤ በይሁዳ ወደ አለች ወደ ኢየሩሳሌም ይውጣ፤ ለእስራኤል ጌታ ለእግዚአብሔር በኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስን ይሥራ። 6 በያገራችሁ ያላችሁ ሁሉ በየአውራጃችሁ ወርቁንና ብሩን ርዱ። 7 እናንተም ለእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ፈረሱንና ከብቱን ስእለት ካለው ሁሉ ጋር ጨምሩ። 8 “የይሁዳና የብንያም ሀገሮች መሳፍንትም በየነገዳቸው፥ ሕዝቡም፥ ካህናቱም፥ ሌዋውያኑም፥ እግዚአብሔርም ልቡናውን ያነሣሣለት ሁሉ ይውጣ፤ በኢየሩሳሌም ያለውንም የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ይሥራ። 9 ባውራጃቸው ያሉም በወርቅና በብር፥ በፈረስና በከብት ሁሉ፥ ስእለት ያለባቸውም፥ ልቡናውም የወደደ ሁሉ ይርዷቸው።” 10 ንጉሥ ቂሮስም ናቡከደነፆር ከኢየሩሳሌም ወስዶ በጣዖቶቹ ቤት ያኖረውን የእግዚአብሔርን ንዋየ ቅድሳት አወጣ። 11 የፋርስ ንጉሥ ቂሮስም ንዋየ ቅዱሳቱን ባወጣ ጊዜ ለጠባቂው ለሚትረዳጡ ሰጠው፥ 12 ለይሁዳ የተሾመው ሰልምናስም ከእርሱ ተቀበለ፤ 13 ቍጥሩም እንዲህ ነው፦ የወርቁ ወጭት አንድ ሺህ፥ የብሩም ወጭት አንድ ሺህ ነው። የብር ሳህኖች ሃያ ዘጠኝ፥ የወርቅ ጽዋዎችም ሠላሳ፥ የብርም ጽዋዎች ሁለት ሺህ አራት መቶ ዐሥር፥ ሌሎች ዕቃዎች ግን አንድ ሺህ ነበሩ። 14 የተመለሰውም የወርቁና የብሩ ዕቃ ሁሉ ተዳምሮ አምስት ሺህ አራት መቶ ስድሳ ዘጠኝ ነበር። 15 ስልምናሶርም ከምርኮኞቹ ጋር ከባቢሎን ወስዶ ወደ ኢየሩሳሌም አገባው። በግንቡ ሥራ ላይ የደረሰ ተቃውሞ 16 ከእነርሱም ውስጥ የፋርስ ንጉሥ አርጤክስስ በይሁዳና በኢየሩሳሌም አውራጃዎች ያስቈጠራቸው አሉ፤ ቤልሞስና ሚጥራዳጢ፥ ጠቢልዮስና ራቲሞስ፥ ቤሔልጤሞስና ጸሓፊው ሲሳዮስ፥ ከነዚህም በታች ያሉ በሰማርያ የሚኖሩ ሁሉ፥ በሌላም ሀገር ያሉ ሁሉ እንዲህ ብለው መልእክት ጻፉ። 17 “ለጌታችን ለንጉሡ ለአርጤክስስ፦ ከብላቴኖችህ፥ ከታሪክ ጸሓፊህ ከራቲሞስና ከጸሓፊው ከሰሜልዮስ ከእነርሱ በታች ከተሾሙት ሁሉና በቄሌ-ሶርያና በፊኒቄ ከሚኖሩ ሁሉ፦ 18 አሁንም ጌታችን ንጉሥ ሆይ፥ ይህን ዕወቅ፤ ከእናንተ ወደ እኛ የመጡ አይሁድ ወደ ኢየሩሳሌም ሄደው፥ ክፉና ከዳተኛ ከተማን ይገነባሉ፤ የገበያ ቦታዎችዋንና ቅፅሮችዋን፥ ቤተ መቅደስዋንም ያድሳሉ። 19 ያችም ከተማ ከተሠራች፥ ቅፅሯም ካለቀ፥ ከዚያ በኋላ ግብር አይገብሩም፤ ዳግመኛም መንግሥታችንን ይቀማሉ። 20 ቤተ መቅደስንም አሳምረው ይሠራሉ። አሁንም ስለዚህ ቸል አትበል። 21 በአባቶቻችሁ የታሪክ መጽሐፍ ይፈልጉ ዘንድ ወደ ንጉሡ ወደ ቂሮስ ላክ። 22 ያች ከተማ ነገሥታቱን የምትከዳና ከተሞችን እንደምታውክ፥ ስለዚህ የተጻፈ ታገኛለህ። 23 አይሁድም ከጥንት ጀምሮ ከዳተኞች እንደ ሆኑ ተጽፎ ታገኛለህ፤ ስለዚህም ያች ከተማ ጠፍታ ነበር። 24 አሁንም ጌታችን ንጉሥ ሆይ፥ እንነግርሃለን፤ ያች ከተማ ከተሠራች፥ ቅጽሮችዋም ከተፈጸሙ በኋላ ወደ ቄሌ-ሶርያና ወደ ፊንቄ አያሳልፏችሁም።” 25 ከዚህ በኋላ ንጉሡ ለጻፈለት ለታሪክ ጸሓፊው ለራቲሞስና ለቤሔልማቴም፥ ለጸሓፊው ለሳሚልዮስም በሰማርያና በፊኒቂስ ለሚኖሩ፥ ከእነርሱ በታች ላሉ፥ ለቀሩትም እንደ ጻፉለት እንዲህ የምትል ደብዳቤን ጻፈላቸው። 26 “እኔም የላካችሁልኝን ደብዳቤ አንብቤ ይፈልጉ ዘንድ አዘዝሁ፤ ያቺም ከተማ ከጥንት ጀምሮ ነገሥታቱን የምትከዳ እንደ ሆነች አገኘሁ። 27 ሰዎችም ከዳተኞች እንደ ነበሩ፥ ሥራቸውም ጦርነት እንደ ነበረ፥ የኢየሩሳሌምም ነገሥታት ጠንካሮችና ክፉዎች እንደ ነበሩ፥ ቄሌ-ሶርያንና ፊኒቄን እንደ ገዙና እንደገበሩላቸው አገኘሁ። 28 አሁንም እነዚያን ሰዎች ያቺን ከተማ መሥራትን እንዲከለክሏቸው፥ 29 ነገሥታትም ይደክሙ ዘንድ ክፋትን እንዳታበዛ በውስጧ ምንም የሚሠራ እንዳይኖር እነሆ አዘዝሁ።” 30 ከዚህ በኋላ ራቲሞስና ጸሓፊው ስልምዮስ፥ ከእነዚህም በታች ያሉት ንጉሡ አርጤክስስ የጻፋትን ያችን መልእክት ባነበቧት ጊዜ ከብዙ ሰዎች ጋር በብዙ ችኮላ ወደ ኢየሩሳሌም ፈረሶቻቸውን አስነሡ፤ የሚሠሩትንም ይከለክሉ ጀመሩ። 31 የኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስ ሥራም እስከ ፋርስ ንጉሥ ዳርዮስ ሁለተኛዪቱ ዘመነ መንግሥት ድረስ ቆመ። |