2 ዜና መዋዕል 5 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)የቃል ኪዳኑ ታቦት ወደ ቤተ መቅደስ እንደ ገባ ( 1ነገ. 8፥1-9 ) 1 ሰሎሞንም አባቱ ዳዊት የቀደሰውን ብሩንና ወርቁን፥ የመገልገያ ዕቃውንም ሁሉ አምጥቶ በእግዚአብሔር ቤት ውስጥ በነበረው ግምጃ ቤት አገባ። 2 በዚያ ጊዜም ሰሎሞን የእግዚአብሔርን ቃል ኪዳን ታቦት ከዳዊት ከተማ ከጽዮን ያወጡ ዘንድ የእስራኤልን ሽማግሌዎችና የነገድ አለቆችን ሁሉ፥ የእስራኤልንም ልጆች አባቶች ቤቶች መሳፍንት ወደ ኢየሩሳሌም ሰበሰበ። 3 የእስራኤልም ሰዎች ሁሉ በሰባተኛው ወር በበዓሉ ጊዜ ወደ ንጉሡ ወደ ሰሎሞን ተሰበሰቡ። 4 የእስራኤልም ሽማግሌዎች ሁሉ መጡ፤ ሌዋውያንም ሁሉ ታቦቷን አነሡ። 5 የምስክሩንም ድንኳን፥ በድንኳኑም ውስጥ የነበረውን የተቀደሰውን ዕቃ ሁሉ አወጡ፤ ታቦቷንም ካህናቱና ሌዋውያኑ አወጡ። 6 ንጉሡም ሰሎሞንና የእስራኤል ማኅበር ሁሉ፥ እግዚአብሔርን የሚፈሩ ሁሉ በአንድነት በታቦቷ ፊት ሆነው ከብዛት የተነሣ የማይቈጠሩትንና የማይመጠኑትን በጎችና በሬዎች ይሠዉ ነበር። 7 ካህናቱም የእግዚአብሔርን የቃል ኪዳን ታቦት ወደ ቤትዋ አምጥተው በቅድስተ ቅዱሳን ውስጥ ከኪሩቤል ክንፍ በታች በነበረው መቅደስ አኖሯት። 8 ኪሩቤልም በታቦቷ ስፍራ ላይ ክንፎቻቸውን ዘርግተው ነበር፤ ኪሩቤልም ታቦቷንና መሎጊያዎቹን በስተላዩ በኩል ይሸፍኑ ነበር። 9 መሎጊያዎቹም ረጃጅሞች ነበሩና በቅድስተ ቅዱሳኑ ፊት ከመቅደሱ ውስጥ ጫፎቻቸው ይታዩ ነበር፤ ነገር ግን ከውጭ አይታዩም ነበር፤ እስከ ዛሬም ድረስ እዚያ አሉ። 10 በታቦቷም ውስጥ የእስራኤል ልጆች ከግብፅ ምድር በወጡ ጊዜ፥ እግዚአብሔርም ከእነርሱ ጋር ቃል ኪዳን ባደረገ ጊዜ ሙሴ በኮሬብ ካስቀመጣቸው ከሁለቱ ጽላት በቀር ምንም አልነበረባትም። 11 ከመቅደስም ከወጡ በኋላ በዚያ የነበሩት ካህናት ሁሉ ተቀድሰው ነበር፤ በሰሞናቸውም አልተከፈሉም ነበር። 12 መዘምራንም የነበሩት ሌዋውያን ሁሉ፥ ከአሳፍና ከኤማን፥ ከኤዶትምም ልጆች ጋር ወንድሞቻቸውም፥ ጥሩ በፍታ ለብሰው ጸናጽልና ከበሮ፥ መሰንቆም እየመቱ በመሠዊያው አጠገብ በምሥራቅ በኩል ቆመው ነበር፤ ከእነርሱም ጋር መቶ ሃያ ካህናት መለከት ይነፉ ነበር። 13 መለከቱንም የሚነፉ መዘምራኑ በአንድነት ሆነው እግዚአብሔርን እያመሰገኑና እያከበሩ፥ “እግዚአብሔር ቸር ነውና፥ ምሕረቱም ለዘለዓለም ነውና እግዚአብሔርን አመስግኑ” እያሉ በአንድ ቃል ድምፃቸውን ወደ ላይ ከፍ አድርገው በመለከትና በጸናጽል፥ በዜማም ዕቃ ሁሉ እግዚአብሔርን ባመሰገኑ ጊዜ፥ የእግዚአብሔር የክብሩ ደመና የእግዚአብሔርን ቤት ሞላው። 14 የእግዚአብሔርም ክብር የእግዚአብሔርን ቤት ሞልቶት ነበርና ካህናቱ ከደመናው የተነሣ መቆምና ማገልገል አልተቻላቸውም። |