1 ሳሙኤል 22 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ሳኦል ካህናትን እንደ ገደለ 1 ዳዊትም ከዚያ ተነሥቶ አመለጠ፤ ወደ ዔዶላም ዋሻም መጣ፤ ወንድሞቹና የአባቱ ቤተ ሰብ ሁሉ ይህን በሰሙ ጊዜ ወደ እርሱ ወደዚያ ወረዱ። 2 የተጨነቀም ሁሉ፥ ዕዳም ያለበት ሁሉ፥ የተከፋም ሁሉ ወደ እርሱ ተሰባሰበ፤ እርሱም በላያቸው አለቃ ሆነ፤ ከእርሱም ጋር አራት መቶ የሚያህሉ ሰዎች ነበሩ። 3 ዳዊትም ከዚያ በሞዓብ ምድር ወዳለችው ወደ መሴፋ ሄደ፤ የሞዓብንም ንጉሥ፥ “እግዚአብሔር የሚያደርግልኝን እስካውቅ ድረስ አባቴና እናቴ ከአንተ ጋር ይቀመጡ ዘንድ እለምንሃለሁ” አለው። 4 የሞዓብንም ንጉሥ ማለደው፤ ዳዊትም በአንባ ውስጥ በነበረበት ወራት ሁሉ በእርሱ ዘንድ ተቀመጡ። 5 ነቢዩ ጋድም ዳዊትን፥ “ተነሥተህ ወደ ይሁዳ ምድር ሂድ እንጂ በአንባው ውስጥ አትቀመጥ” አለው፤ ዳዊትም ሄደ፤ ወደ ሳሬቅ ከተማም መጥቶ ተቀመጠ፤ 6 ሳኦልም ዳዊትና ከእርሱ ጋር የነበሩት ሰዎች ያሉበት ቦታ እንደ ታወቀ ሰማ። ሳኦልም በራማ በሚገኘው በመሰማርያው ቦታ በኮረብታው ላይ ተቀምጦ በእጁም ጦር ይዞ ነበር፤ ብላቴኖቹም ሁሉ በአጠገቡ ቆመው ነበር። 7 ሳኦልም በአጠገቡ የቆሙትን ብላቴኖች፥ “ብንያማውያን ሆይ! እንግዲህ ስሙ በእውነት የእሴይ ልጅ እርሻና የወይን ቦታ ለሁላችሁ ይሰጣችኋልን? ሁላችሁንስ መቶ አለቆችና ሻለቆች ያደርጋችኋልን? 8 ሁላችሁ በላዬ ዶልታችሁ ተነሣችሁብኝ፤ ልጄ ከእሴይ ልጅ ጋር ሲማማል ማንም አልገለጠልኝም፤ ከእናንተም አንድ ለእኔ የሚያዝን የለም፤ ዛሬም እንደ ሆነው ሁሉ ልጄ አገልጋዬን እንዲዶልት ሲያስነሣብኝ ማንም አላስታወቀኝም” አላቸው። 9 የሳኦልም በቅሎዎች ጠባቂ ሶርያዊው ዶይቅ መልሶ፥ “የእሴይ ልጅ ወደ ኖብ ወደ አኪጦብ ልጅ ወደ ካህኑ አቤሜሌክ ሲመጣ አይቼዋለሁ። 10 እግዚአብሔርንም ጠየቀለት፤ ስንቅንም ሰጠው፤ የፍልስጥኤማዊውንም የጎልያድን ሰይፍ ሰጠው” አለው። 11 ንጉሡም የአኪጦብን ልጅ ካህኑን አቤሜሌክን፥ በኖብም ያሉትን ካህናት፥ የአባቱን ልጆች ሁሉ ልኮ አስጠራቸው፤ ሁላቸውም ወደ ንጉሡ መጡ። 12 ሳኦልም፥ “የአኪጦብ ልጅ ሆይ! እንግዲህ ስማ” አለ፤ እርሱም፥ “እነሆኝ ጌታዬ ሆይ” ብሎ መለሰ። 13 ሳኦልም፥ “አንተ ከእሴይ ልጅ ጋር ለምን ዶለትህብኝ? እንጀራና ሰይፍ ሰጠኸው፤ ዛሬም እንደ ተደረገው ጠላት ሆኖ ይነሣብኝ ዘንድ እግዚአብሔርን ስለ እርሱ ጠየቅህለት” አለው። 14 አቤሜሌክም መልሶ ንጉሡን፥ “ከባሪያዎቹ ሁሉ የታመነ፥ ለንጉሥም አማች የሆነ፥ የትእዛዝህ ሁሉ አለቃ፥ በቤትህም የከበረ እንደ ዳዊት ያለ ማን ነው? 15 በውኑ ስለ እርሱ እግዚአብሔርን እጠይቅ ዘንድ ዛሬ ጀመርሁን? ይህ ከእኔ ይራቅ፤ እኔ ባሪያህ ይህን ሁሉ ትልቅ ወይም ጥቂት ቢሆን አላውቅምና ንጉሡ እንደዚህ ያለውን ነገር በእኔ በባሪያውና በአባቴ ቤት ሁሉ ላይ አያኑር” አለ። 16 ንጉሡም፥ “አቤሜሌክ ሆይ! አንተና የአባትህ ቤት ሁሉ ፈጽማችሁ ትሞታላችሁ” አለ። 17 ንጉሡም በዙሪያው የቆሙትን እግረኞች፥ “የእግዚአብሔር ካህናት እጅ ከዳዊት ጋር ነውና፥ ኵብለላውንም ሲያውቁ አልነገሩኝምና፥ ዞራችሁ ግደሉአቸው” አላቸው። የንጉሡ አገልጋዮች ግን እጃቸውን በእግዚአብሔር ካህናት ላይ ይዘረጉ ዘንድ እንቢ አሉ። 18 ንጉሡም ዶይቅን፥ “አንተ ዞረህ ካህናቱን ግደላቸው” አለው። ሶርያዊው ዶይቅም ዞሮ ካህናቱን ገደላቸው፤ በዚያም ቀን የበፍታ ኤፉድ የለበሱትን ሦስት መቶ ሰማንያ አምስት ሰዎችን ገደለ። 19 የካህናቱንም ከተማ ኖብን በሰይፍ ስለት መታ፤ ወንዶችንና ሴቶችንም፥ ብላቴኖችንና ጡት የሚጠቡትን፥ በሬዎችንና አህዮችንም፥ በጎችንም በሰይፍ ስለት ገደለ። 20 ከአኪጦብም ልጅ ከአቤሜሌክ ልጆች ስሙ አብያታር የሚባል አንዱ ልጅ አምልጦ ሸሸ፤ ዳዊትንም ተከተለ። 21 አብያታርም ሳኦል የእግዚአብሔርን ካህናት እንደ ፈጀ ለዳዊት ነገረው። 22 ዳዊት አብያታርን፦ ሶርያዊው ዶይቅ በዚያ መኖሩን ባየሁ ጊዜ፥ “ለሳኦል በርግጥ ይነግራል ብዬ በዚያ ቀን አውቄዋለሁ፤ ለአባትህ ቤት ነፍስ ሁሉ ጥፋት በደለኛው እኔ ነኝ። 23 እንግዲህ ወዲህ ከእኔ ጋር ተቀመጥ፤ አትፍራ፤ ለእኔ ነፍስ የደኅንነት ቦታን እንደምፈልግ ለአንተም ነፍስ የደኅንነት ቦታን እፈልጋለሁና፥ ከእኔም ጋር ተጠብቀህ ትኖራለህ” አለው። |