1 ሳሙኤል 21 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ዳዊት ከሳኦል ፊት እንደ ሸሸና ወደ ኖብ እንደ ሄደ 1 ዳዊትም ወደ ካህኑ ወደ አቤሜሌክ ወደ ኖብ መጣ፤ አቤሜሌክም እርሱን በተገናኘው ጊዜ ደነገጠ፥ “ስለምን አንተ ብቻህን ነህ? ከአንተስ ጋር ስለምን ማንም የለም?” አለው። 2 ዳዊትም ካህኑን አቤሜሌክን፥ “የተላክህበትን ነገርና የሰጠሁህን ትእዛዝ ማንም አይወቅ ብሎ ንጉሡ አንድ ነገር አዝዞኛል፤ ስለዚህም ‘ብላቴኖቼን በእግዚአብሔር መታመን’ በሚባለው እንዲህ ባለው ስፍራ እንዲሆኑ አዝዣቸዋለሁ። 3 አሁንም አምስት እንጀራ በእጅህ ካለ፥ ወይም በእጅህ ያለውን ስጠኝ” አለው። 4 ካህኑም ለዳዊት መልሶ፥ “ሁሉ የሚበላው እንጀራ የለኝም፤ ነገር ግን የተቀደሰ እንጀራ አለ፤ ብላቴኖቹ ከሴቶች ንጹሓን እንደ ሆኑ መብላት ይችላሉ” አለው። 5 ዳዊትም ለካህኑ መልሶ፥ “ከሴቶች ተለይተን ወደ መንገድ ከወጣን ዛሬ ሦስተኛ ቀናችን ነው። እኔም ብላቴኖቼም ንጹሓን ነን። ነገር ግን ዛሬ ሰውነቴ ንጽሕት ስለ ሆነች ነው እንጂ ይህች መንገድ የነጻች አይደለችም” አለው። 6 ካህኑ አቤሜሌክም በእርሱ ፋንታ ትኩስ እንጀራ ይደረግ ዘንድ በእግዚአብሔር ፊት ከአለው ኅብስት በቀር ሌላ እንጀራ አልነበረምና የቍርባኑን ኅብስት ሰጠው። 7 በዚያም ቀን ከሳኦል አገልጋዮች አንድ ሰው በኔሴራ አቅራቢያ በዚያ በእግዚአብሔር ፊት ነበር፤ ስሙም ሶርያዊው ዶይቅ ነበረ፤ የሳኦልም በቅሎዎች ጠባቂ ነበረ። 8 ዳዊትም አቤሜሌክን፥ “የንጉሥ ጉዳይ ስላስቸኰለኝ ሰይፌንና መሣሪያዬን አላመጣሁምና በአንተ ዘንድ ጦር ወይም ሰይፍ እንዳለ እይልኝ” አለው። 9 ካህኑም፥ “በኤላ ሸለቆ የገደልኸው የፍልስጥኤማዊው የጎልያድ ሰይፍ እነሆ፥ በመጐናጸፊያ ተጠቅልላ አለች፤ የምትወስዳት ከሆነ ውሰዳት፤ ከእርስዋ በቀር ሌላ ከዚህ የለምና” አለው። ዳዊትም፥ “ከእርስዋ በቀር ሌላ ከሌለ እርስዋን ስጠኝ” አለው። እርሱም ሰጠው። 10 ዳዊትም ተነሣ በዚያም ቀን ከሳኦል ፊት ሸሸ፤ ወደ ጌትም ንጉሥ ወደ አንኩስ መጣ። 11 የአንኩስ ብላቴኖችም፥ “ይህ ዳዊት የሀገሩ ንጉሥ አይደለምን? ሳኦል ሺህ፥ ዳዊትም ዐሥር ሺህ ገደለ ብለው ሴቶች በዘፈን የዘመሩለት እርሱ አይደለምን?” አሉት። 12 ዳዊትም ይህን ቃል በልቡ አኖረ፤ የጌትንም ንጉሥ አንኩስን እጅግ ፈራ። 13 በፊቱም መልኩን ለወጠ፤ በዚያችም ቀን አመለጠ። በከተማውም በር ከበሮ ይዞ በእጁ መታ፤ በበሩም መድረክ ላይ ተንፈራፈረ፤ ልጋጉም በጢሙ ላይ ይወርድ ነበር። 14 አንኩስም ብላቴኖቹን፥ “እነሆ፥ ይህ ሰው እብድ እንደ ሆነ አይታችኋል፤ ለምን ወደ እኔ አመጣችሁት? 15 በፊቴ ያብድ ዘንድ ይህን ያመጣችሁት እኔ የእብዶች አለቃ ነኝን? እንዲህ ያለውስ ወደ ቤቴ ይገባልን?” አላቸው። |