1 ነገሥት 14 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)1 በዚያም ወራት የኢዮርብዓም ልጅ አብያ እጅግ ታመመ። 2 ኢዮርብዓምም ሚስቱ ሐኖንን፥ “ተነሺ፥ ራስሽን ለውጪ የኢዮርብዓምም ሚስት እንደ ሆንሽ ማንም አይወቅ፤ ወደ ሴሎም ሂጂ፤ ስለዚህም ሕፃን ከደዌው ይድን እንደሆነ ጠይቂ፤ እነሆ፥ በዚህ ሕዝብ ላይ እንደምነግሥ የነገረኝ ነቢዩ አኪያ በዚያ አለ። 3 በእጅሽም ለእግዚአብሔር ሰው ዐሥር እንጀራና የወይን እሸት አንድም ማሠሮ ማር ይዘሽ ወደ እርሱ ሂጂ፤ በልጁም የሚሆነውን ይነግርሻል” አላት። 4 የኢዮርብዓምም ሚስት እንዲሁ አደረገች፤ ተነሥታም እንጀራ፥ የወይን ዘለላና አንድ ማሠሮ ማር በመያዝ ወደ ሴሎ ሄደች፤ ወደ አኪያም ቤት ገባች። አኪያ ግን ስለ መሸምገሉ ዐይኖቹ ፈዝዘው ነበርና ማየት አልቻለም። 5 እግዚአብሔርም አኪያን፥ “እነሆ፥ ስለ ታመመው ልጅዋ ትጠይቅህ ዘንድ የኢዮርብዓም ሚስት ትመጣለች፤ ራስዋንም ለውጣ ወደ አንተ በገባች ጊዜ እንዲህና እንዲህ በላት” አለው። 6 እርስዋም በደጅ ስትገባ አኪያ የእግርዋን ኮቴ ሰማ፤ እንዲህም አላት፥ “የኢዮርብዓም ሚስት ሆይ፥ ግቢ! ስለምንስ ራስሽን ለወጥሽ? እኔም የሚያስጨንቅ ወሬ ይዤ ወደ አንቺ ተልኬአለሁ። 7 ሂጂ ለኢዮርብዓም እንዲህ በዪው፦ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ከሕዝብ መካከል ለይቼ ከፍ አድርጌህ ነበር፤ በሕዝቤ በእስራኤል ላይም ንጉሥ አድርጌህ ነበር። 8 ከዳዊትም ቤት፤ መንግሥቱን ከፍዬ ሰጥቼህ ነበር፤ ነገር ግን በፍጹም ልቡ እንደ ተከተለኝ፥ በፊቴም ቅን ነገር ብቻ እንዳደረገ፥ ትእዛዜንም እንደ ጠበቀ እንደ ባሪያዬ እንደ ዳዊት አልሆንህም። 9 ከአንተም አስቀድመው ከነበሩት ሁሉ ይልቅ ክፉ ሠራህ፤ ታስቈጣኝም ዘንድ ሄደህ ሌሎችን አማልክትና ቀልጠው የተሠሩትን ምስሎች አደረግህ፤ ወደ ኋላህም ተውኸኝ። 10 ስለዚህ እነሆ፥ በኢዮርብዓም ቤት ላይ መከራን አመጣለሁ፤ ኢዮርብዓምንም አጠፋዋለሁ፤ አጥር ተጠግቶ እስከሚሸን ወንድ ድረስ አላስቀርለትም፤ በእስራኤልም ላይ ይነግሥ ዘንድ አልተወውም፤ ሰው ገለባ እስኪያልቅ ድረስ እንደሚያነድድ በኢዮርብዓም ቤት ላይ እሳትን አነዳለሁ። 11 እግዚአብሔር እንደ ተናገረ ከኢዮርብዓም ወገን በከተማዪቱ ውስጥ የሞተውን ውሾች ይበሉታል፤ በሜዳውም የሞተውን የሰማይ ወፎች ይበሉታል። 12 እንግዲህ ተነሥተሽ ወደ ቤትሽ ሂጂ፤ እግርሽም ወደ ከተማ በገባ ጊዜ ልጅሽ ይሞታል። 13 ደንገጡሮችሽም ሊቀበሉሽ ይወጣሉ፤ ልጅሽም ሞተ ይሉሻል፥ እስራኤልም ሁሉ ያለቅሱለታል፤ ይቀብሩትማል፤ በእስራኤል አምላክ በእግዚአብሔር ዘንድ በኢዮርብዓም ቤት በዚህ ልጅ መልካም ነገር ተገኝቶበታልና ከኢዮርብዓም እርሱ ብቻ ይቀበራል። 14 እግዚአብሔር ደግሞ የኢዮርብዓምን ቤት የሚያጠፋ ንጉሥ በእስራኤል ላይ ያነግሣል፤ እርሱም ዛሬ ይደረጋል፤ እንግዲህ ወዲህ ምን እናገራለሁ? 15 በዚያ ጊዜም ሸምበቆ በውኃ ውስጥ እንደሚንቀሳቀስ እግዚአብሔር እንዲሁ እስራኤልን ይመታል፤ እግዚአብሔርንም ያስቈጡ ዘንድ የማምለኪያ አፀድ ተክለዋልና ለአባቶቻቸው ከሰጣቸው ከዚች ከመልካሚቱ ምድር እስራኤልን ይነቅላል፤ በወንዙም ማዶ ይበትናቸዋል። 16 ስለ በደለውና እስራኤልንም ስላሳተበት ስለ ኢዮርብዓም ኀጢአት እስራኤልን ይጥላል።” 17 የኢዮርብዓምም ሚስት ተነሥታ ሄደች፤ ወደ ቴርሳም መጣች፤ ወደ ቤቱም መድረክ በገባች ጊዜ ልጁ ሞተ። 18 በባሪያውም በነቢዩ በአኪያ እንደ ተነገረው እንደ እግዚአብሔር ቃል እስራኤል ሁሉ ቀበሩት፥ አለቀሱለትም። 19 የቀረውም የኢዮርብዓም ነገር፥ እንዴት እንደ ተዋጋ፥ እንዴትም እንደ ነገሠ፥ እነሆ፥ በእስራኤል ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ ተጽፎአል። 20 ኢዮርብዓምም የነገሠበት ዘመን ሃያ አራት ዓመት ነበረ፥ ከአባቶቹም ጋር አንቀላፋ፥ ልጁም ናባጥ በፋንታው ነገሠ። የይሁዳ ንጉሥ ሮብዓም ( 2ዜ.መ. 11፥5—12፥15 ) 21 የሰሎሞንም ልጅ ሮብዓም በይሁዳ ነገሠ፤ ሮብዓምም ንጉሥ በሆነ ጊዜ የአርባ አንድ ዓመት ጐልማሳ ነበረ፤ እግዚአብሔርም ስሙን ያኖርባት ዘንድ ከእስራኤል ነገድ ሁሉ በመረጣት ከተማ በኢየሩሳሌም ዐሥራ ሰባት ዓመት ነገሠ፤ የእናቱም ስም ናዕማ ነበረ፥ እርስዋም አሞናዊት ነበረች። 22 ሮብዓምም በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ሠራ፤ አባቶቹ በሠሩት ኀጢአትና በደል ሁሉ እንደ አስቀኑት በሠራው ኀጢአት አስቀናው። 23 እነርሱም ደግሞ ከፍ ባለው ኮረብታ ሁሉ ላይ፥ ቅጠሉም ከለመለመ ዛፍ ሁሉ በታች መስገጃዎችን ሠሩ፤ ሐውልቶችንና የማምለኪያ አፀዶችንም ለራሳቸው አቆሙ። 24 በምድርም ሁሉ ዐመፅ ነበረ፥ ከእስራኤልም ልጆች ፊት እግዚአብሔር ያሳደዳቸው የአሕዛብን ርኵሰት ሁሉ ያደርጉ ነበር። 25 ሮብዓምም በነገሠ በአምስተኛው ዓመት የግብፅ ንጉሥ ሱስቀም በኢየሩሳሌም ላይ ዘመተ። 26 የእግዚአብሔርን ቤተ መዛግብትና የንጉሡን ቤተ መዛግብት ሁሉ ወሰደ፤ ዳዊትም ከሱባ ንጉሥ ከአድርዓዛር ልጆች እጅ ወስዶ ወደ ኢየሩሳሌም ያመጣቸውን የወርቅ ጦሮችና ሰሎሞን የሠራቸውን የወርቁን ጋሻና ጦር ሁሉ ወደ ግብፅ ወሰደ። 27 ንጉሡም ሮብዓም በፋንታው የናስ ጋሾችን ሠራ፤ በፊቱም ለሚሮጡና የንጉሥን ቤት ደጅ ለሚጠብቁ የዘበኞች አለቆች ሰጣቸው። 28 ከዚህ በኋላ ንጉሡ ዘወትር ወደ እግዚአብሔር ቤት ሲገባ ዘበኞች ይሸከሙአቸው ነበር፤ መልሰውም በዘበኞች ቤት ውስጥ ያኖሩአቸው ነበር። 29 የቀረውም የሮብዓም ነገር፥ ያደረገውም ሁሉ፥ በይሁዳ ነገሥታት ታሪክ መጽሐፍ እነሆ፥ ተጽፎአል። 30 በዘመኑም ሁሉ በሮብዓምና በኢዮርብዓም መካከል ጦርነት ነበረ። 31 ሮብዓምም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፥ በዳዊትም ከተማ ከአባቶቹ ጋር ተቀበረ። ልጁም አብያ በፋንታው ነገሠ። |