1 ነገሥት 10 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ንግሥተ ሳባ ወደ ኢየሩሳሌም ያደረገችው ጕዞ ( 2ዜ.መ. 9፥1-12 ) 1 የሳባም ንግሥት የሰሎሞንን ስም፥ የእግዚአብሔርንም ስም በሰማች ጊዜ ሰሎሞንን በእንቆቅልሽ ትፈትነው ዘንድ መጣች። 2 በግመሎችም ላይ ሽቱና እጅግ ብዙ ወርቅ የከበረም ዕንቍ አስጭና ከታላቅ ጓዝ ጋር ወደ ኢየሩሳሌም ገባች፤ ወደ ሰሎሞንም በመጣች ጊዜ በልብዋ ያለውን ሁሉ ነገረችው። 3 ሰሎሞንም የጠየቀችውን ሁሉ ፈታላት፤ ያልተረጐመላትና ከንጉሡ የተሰወረ ነገር አልነበረም። 4 የሳባም ንግሥት የሰሎሞንን ጥበብ ሁሉ፥ ሠርቶትም የነበረውን ቤት፥ 5 የሰሎሞንንም የማዕዱን መብል፥ የብላቴኖቹንም አቀማመጥ፥ የሎሌዎቹንም ሥርዐት፥ አለባበሳቸውንም፥ ጠጅ አሳላፊዎቹንም፥ በእግዚአብሔርም ቤት የሚያቀርበውን መሥዋዕት ባየች ጊዜ ተደነቀች። 6 ንጉሡን ሰሎሞንንም አለችው፥ “ስለ ነገርህና ስለ ጥበብህ በሀገሬ ሳለሁ የሰማሁት ዝና እውነት ነው። 7 እኔም መጥቼ በዐይኔ እስካይ ድረስ የነገሩኝን አላመንሁም ነበር ፤ እነሆም፥ እኩሌታውን አልነገሩኝም ነበር፤ በሀገሬ ሳለሁ ከነገሩኝ ይልቅ የበለጠ መልካም ተጨማሪ አየሁ። 8 ሚስቶችህ የተመሰገኑ ናቸው፤ በፊትህ ሁልጊዜ የሚቆሙ፥ ጥበብህን የሚሰሙ እነዚህ አገልጋዮችህም ምስጉኖች ናቸው። 9 አንተን በእስራኤል ዙፋን ያስቀምጥህ ዘንድ የወደደ አምላክህ እግዚአብሔር የተመሰገነ ይሁን፤ እግዚአብሔር እስራኤልን ለዘለዓለም ያጸናው ዘንድ ወድዶታልና ስለዚህ በየነገራቸው ጽድቅና ፍርድ ታደርግ ዘንድ በላያቸው አነገሠህ።” 10 ለንጉሡም መቶ ሃያ መክሊት ወርቅ እጅግም ብዙ ሽቶ፥ የከበረም ዕንቍ ሰጠችው፤ የሳባ ንግሥት ለንጉሡ ለሰሎሞን እንደ ሰጠችው ያለ የሽቶ ብዛት ከዚያ ወዲያ አልመጣም ነበር። 11 ከኦፌርም ወርቅ ያመጣች የኪራም መርከብ እጅግ ብዙ የተጠረበ እንጨትና የከበረ ዕንቍ አመጣች። 12 ንጉሡም ከተጠረበው እንጨት ለእግዚአብሔር ቤትና ለንጉሡ ቤት መከታ፥ ለመዘምራኑም መሰንቆና በገና አደረገ፤ እስከ ዛሬም ድረስ በምድር ላይ እንደዚያ ያለ የተጠረበ እንጨት ከቶ አልመጣም፤ በየትም ቦታ አልታየም። 13 ንጉሡም ሰሎሞን በእጁ ከሰጣት ሌላ፥ የወደደችውን ሁሉ፥ ከእርሱም የጠየቀችውን ሁሉ ለሳባ ንግሥት ሰጣት፤ የከለከላትም የለም፤ እርስዋም ተመልሳ ከአገልጋዮችዋ ጋር ወደ ሀገርዋ ሄደች። 14 በየዓመቱ ለሰሎሞን የሚመጣለት የወርቅ ሚዛን ስድስት መቶ ስድሳ ስድስት መክሊት ወርቅ ነበረ። 15 ይኽንም፥ ግብር የሚያስገብሩ ሰዎች፥ ነጋዴዎችም፥ በዙሪያው ያሉ ነገሥታትም ሁሉ፥ የምድርም ሹሞች ከሚያወጡት ሌላ ነው። 16 ንጉሡ ሰሎሞንም ከጥፍጥፍ ወርቅ ሁለት መቶ አላባሽ አግሬ ጋሻ አሠራ፤ በአንዱም አላባሽ አግሬ ጋሻ ውስጥ የገባው ወርቅ ሦስት መቶ ሰቅል ነበረ። 17 ከጥፍጥፍም ወርቅ ሦስት መቶ ጋሻ አሠራ፤ በአንዱም ጋሻ የገባው ወርቅ ሦስት ምናን ነው፤ ንጉሡም የሊባኖስ ዱር በተባለው ቤት ውስጥ አኖራቸው። 18 ንጉሡም ደግሞ ከዝሆን ጥርስ ታላቅ ዙፋን አሠራ፤ በጥሩም ወርቅ ለበጠው። 19 ወደ ዙፋንም የሚያስኬዱ ስድስት እርከኖች ነበሩ፤ በስተኋላውም ያለው የዙፋኑ ራስ ክብ ነበረ፤ በላም ምስል የተቀረጸ በወዲህና በወዲያም መደገፊያ ነበረው፤ በመደገፊያዎቹም አጠገብ ሁለት አንበሶች ቆመው ነበር፤ 20 በስድስቱም እርከኖች ላይ በዚህና በዚያ ዐሥራ ሁለት አንበሶች ቆመው ነበር፤ በመንግሥታት ሁሉ እንዲህ ያለ ሥራ አልተሠራም። 21 ንጉሡም ሰሎሞን ያሠራው የመጠጫ ዕቃ ሁሉ ወርቅ ነበረ፤ ኵስኵስቱም የወርቅ ነበረ፤ የሊባኖስ ዱር የተባለውን የዚያን ቤት ዕቃ ሁሉ በወርቅ አስለበጠው። የብርም ዕቃ አልነበረም፤ በሰሎሞን ዘመን የብር ዋጋ ዝቅተኛ ነበርና። 22 ለንጉሡም ከኪራም መርከቦች ጋር በባሕር ውስጥ የተርሴስ መርከቦች ነበሩት፤ በየሦስት ዓመትም አንድ መርከብ ከተርሴስ ወርቅና ብር፥ የተቀረጸና የተደረደረ ዕንቍ ይዞ ይመጣ ነበር። 23 ንጉሡም ሰሎሞን በብልጥግናና በጥበብ ከምድር ነገሥታት ሁሉ እጅግ በልጦ ነበር። 24 የምድርም ነገሥት ሁሉ እግዚአብሔር በልቡ ያኖረለትን ጥበቡን ይሰሙ ዘንድ የሰሎሞንን ፊት ለማየት ይሹ ነበር። 25 እነርሱም ሁሉ በዓመት በዓመቱ ገጸ በረከቱን፥ የብርና የወርቅ ዕቃ፥ ልብስና የጦር መሣሪያ፥ ሽቱም፥ ፈረሶችና በቅሎዎች እየያዙ ይመጡ ነበር። 26 ሰሎሞንም ለሰረገሎቹ ዐራት ሺህ እንስት ፈረሶች ነበሩት፤ ዐሥራ ሁለት ሺህ ፈረሰኞችም ነበሩት፤ በሰረገሎችም ከተሞች ከንጉሡ ጋር በኢየሩሳሌም አኖራቸው። ሰሎሞንም ከወንዙ ጀምሮ እስከ ፍልስጥኤም ምድርና እስከ ግብፅ ድንበር ድረስ በነገሥታቱ ሁሉ ላይ ንጉሥ ነበር። 27 ንጉሡም ብሩንና ወርቁን በኢየሩሳሌም እንደ ድንጋይ እንዲበዛ አደረገው፤ የዝግባም እንጨት ብዛት በቆላ እንደሚበቅል ሾላ ሆነ። 28 ሰሎሞንም ፈረሶችን ከግብፅና ከቴቁሄ ሀገር አስመጣ፤ የንጉሡም ነጋዴዎች በገንዘብ እየገዙ ከቴቁሄ ያመጡአቸው ነበር። 29 አንዱም ሰረገላ በስድስት መቶ፥ አንዱም ፈረስ በመቶ ኀምሳ ብር ከግብፅ ይወጣ ነበር። እንዲሁም ለኬጤዎናውያን ነገሥታትና ለሶርያ ነገሥታት ሁሉ በባሕሩ በኩል ያወጡላቸው ነበር። |