1 ቆሮንቶስ 9 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ስለ ራሱና ስለ በርናባስ 1 እኔ ነጻ አይደለሁምን? ሐዋርያስ አይደለሁምን? ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ያየሁ አይደለሁምን? እናንተስ በጌታችን ሥራዬ አይደላችሁምን? 2 ለሌሎች ሐዋርያቸው ባልሆንም ለእናንተስ ሐዋርያችሁ እኔ ነኝ፤ በጌታችን የሐዋርያነቴ ማኅተም እናንተ ናችሁና። 3 ለሚከራከሩኝ መልሴ እንዲህ ነው። 4 በውኑ ልንበላና ልንጠጣ አይገባንምን? 5 እንደ ሌሎች ሐዋርያት ሁሉና፥ እንደ ጌታችን ወንድሞች እንደ ኬፋም ከሴቶች እኅታችንን ይዘን ልንዞር አይገባንምን? 6 ወይስ ሥራን ለመተው መብት የሌለን እኔና በርናባስ ብቻ ነን? 7 የሚያገለግልም ምግቡን ያገኝ ዘንድ ነው፤ ወይን ተክሎ ፍሬውን የማይበላ ማን ነው? መንጋውንስ ጠብቆ ወተቱን የማይጠጣ ማን ነው? 8 በውኑ ለሰው ይምሰል እናገራለሁን? የሙሴ መጽሐፍ ኦሪትስ እንዲህ ብሎ የለምን፦ 9 “እህልህን በምታበራይበት ጊዜ የበሬውን አፉን አትሰረው።” እንግዲህ ይህን የጻፈ ለእግዚአብሔር በሬ አሳዝኖት ነውን? 10 ይህን የሚለው ፈጽሞ ስለ እኛ አይደለምን? የሚያርስ በተስፋ ሊያርስ፥ የሚያበራይም እንዲካፈል በተስፋ ሊያበራይ ስለሚገባው በእውነት ስለ እኛ ተጽፎአል። 11 እኛ መንፈሳዊውን ነገር ከዘራንላችሁ ሥጋዊውን ነገር ብናጭድ ታላቅ ነገር ነውን? 12 በእኛ ሹመት ሌላ የሚቀድመን ከሆነ የሚሻላችሁን እናንተ ታውቃላችሁ፤ እኔ ይህን አልፈለግሁትም፤ ነገር ግን የክርስቶስን ትምህርት እንዳላሰናክል በሁሉ እታገሣለሁ። 13 የጣዖታቱ ካህናት የጣዖታቱን መባ እንደሚበሉ አታውቁምን? መሠዊያውን የሚያገለግሉም መሥዋዕቱን እንደሚካፈሉ አታውቁምን? ለቤተ እግዚአብሔር ሹሞች መተዳደሪያቸው የቤተ እግዚአብሔር መባ ነው። 14 ጌታችንም እንዲሁ ወንጌልን ለሚያስተምሩ ሰዎች ለሕይወታቸው መተዳደሪያ በዚያው ወንጌልን በማስተማር ይሆን ዘንድ አዘዘ። 15 እኔ ግን ይህንም ቢሆን አልፈቀድሁትም፤ ይህን የጻፍሁም ይህን እንዳገኝ ብዬ አይደለም፤ እኔ ግን ምስጋናዬ ከሚቀርብኝ ሞት ይሻለኛል። 16 ወንጌልን ባስተምርም መመስገን አይገባኝም፤ ታዝዤ አድርጌዋለሁና፤ ወንጌልን ባላስተምር ደግሞ ወዮልኝ። 17 ይህንስ በፈቃዴ አድርጌው ብሆን ዋጋዬን ባገኘሁ ነበር፤ በግድ ከሆነ ግን በተሰጠኝ መጋቢነት አገለገልሁ። 18 እንግዲህ ዋጋዬ ምንድን ነው? ወንጌልን ባስተምርም በሹመቴ የማገኘው ሳይኖር ወንጌልን ያለ ዋጋ እንዳስተምር ባደርግ ነው። ብዙዎችን ስለ መጥቀም 19 እኔ ከሁሉ ይልቅ ነጻ ስሆን ብዙዎችን ወደ ሃይማኖት እሰበስባቸው ዘንድ እንደ ባሪያ ራሴን ለሁሉ አስገዛሁ። 20 አይሁድን እጠቅማቸው ዘንድ ለአይሁድ እንደ አይሁዳዊ ሆንሁላቸው፤ ከኦሪት በታች ያሉትን እጠቅም ዘንድ እኔ ራሴ ከኦሪት በታች ሳልሆን ከኦሪት በታች ላሉት ከኦሪት በታች እንዳለ ሰው ሆንሁላቸው። 21 የእግዚአብሔርን ሕግ የዘነጋሁ ሳልሆን፥ በክርስቶስ ሕግም ሳለሁ ሕግ የሌላቸውን እጠቅማቸው ዘንድ ሕግ ለሌላቸው ሕግ እንደሌለው ሆንሁላቸው። 22 ደካሞችንም እጠቅማቸው ዘንድ ለደካሞች እንደ ደካማ ሆንሁላቸው፤ በሁሉ መንገድ አንዳንዶቹን አድን ዘንድ ከሁሉ ጋር በሁሉ ነገር እንደ እነርሱ ሆንሁ። 23 በወንጌልም ትምህርት አንድነት ይኖረኝ ዘንድ ስለ ወንጌል ትምህርት ሁሉን አደርጋለሁ። 24 በእሽቅድምድም ስፍራ የሚሽቀዳደሙ ሁሉ እንደሚፋጠኑ አታውቁምን? ለቀደመው የሚደረግለት ዋጋ አለ፤ እንዲሁ እናንተም እንድታገኙ ፈጽማችሁ ሩጡ። 25 የሚታገል ሁሉ በሁሉ ነገር ይታገሣል፤ እነርሱስ የሚጠፋውንና የሚያልፈውን የምስጋናቸውን ዋጋ አክሊል ያገኙ ዘንድ ይበረታሉ፤ እኛ ግን የማያልፈውን አክሊል ለማግኘት እንታገሣለን። 26 እኔ ያለ አሳብ እንደሚሮጥ ሁሉ እንዲሁ አልሮጥም፤ ነፋስንም እንደሚጐስም ሁሉ እንዲሁ አልጋደልም። 27 ነገር ግን ለሌላ ሳስተምር፥ እኔ ለራሴ የተናቅሁ እንዳልሆን ሰውነቴን አስጨንቃታለሁ፥ ሥጋዬንም አስገዛዋለሁ። |