መዝሙር 98 - አዲሱ መደበኛ ትርጒምመዝሙር 98 መዝሙር። 1 ለእግዚአብሔር አዲስ ዝማሬ አቅርቡ፤ እርሱ ድንቅ ነገሮችን አድርጓልና፤ ቀኝ እጁ፣ ቅዱስ ክንዱም ማዳንን አድርገውለታል። 2 እግዚአብሔር ማዳኑን አሳወቀ፤ ጽድቁንም በሕዝቦች ፊት ገለጠ። 3 ለእስራኤል ቤት ምሕረቱን፣ ታማኝነቱንም ዐሰበ፤ የምድር ዳርቻዎችም ሁሉ፣ የአምላካችንን ማዳን አዩ። 4 ምድር ሁሉ ለእግዚአብሔር እልል በሉ፤ ውዳሴን አፍልቁ፤ በደስታና በዝማሬ አመስግኑ፤ 5 ለእግዚአብሔር በገና ደርድሩለት፤ በበገናና በዝማሬ ድምፅ ዘምሩለት፤ 6 በእንቢልታና በመለከት ድምፅ፣ በንጉሡ በእግዚአብሔር ፊት እልል በሉ። 7 ባሕርና በውስጧ ያለው ሁሉ፣ ዓለምና የሚኖሩባትም ሁሉ ያስገምግሙ። 8 ወንዞች በእጃቸው ያጨብጭቡ፣ ተራሮችም በአንድነት ይዘምሩ፤ 9 እነዚህ በእግዚአብሔር ፊት ይዘምሩ፤ እርሱ በምድር ላይ ሊፈርድ ይመጣልና፤ በዓለም ላይ በጽድቅ፣ በሕዝቦችም ላይ በእውነት ይበይናል። |
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.
Biblica, Inc.