መዝሙር 61 - አዲሱ መደበኛ ትርጒምመዝሙር 61 ለመዘምራን አለቃ፤ በበገናዎች የሚዘመር፤ የዳዊት መዝሙር። 1 እግዚአብሔር ሆይ፤ ጩኸቴን ስማ፤ ጸሎቴንም አድምጥ። 2 ልቤ በዛለ ጊዜ፣ ከምድር ዳርቻ ወደ አንተ እጣራለሁ፤ ከእኔ ይልቅ ከፍ ወዳለው ዐለት ምራኝ። 3 አንተ መጠጊያዬ፣ ከጠላትም የምተገንብህ ጽኑ ግንብ ሆነኸኛልና። 4 በድንኳንህ ለዘላለም ልኑር፤ በክንፎችህም ጥላ ልከለል። ሴላ 5 አምላክ ሆይ፤ ስእለቴን ሰምተሃልና፤ ስምህን የሚፈሩትንም ሰዎች ርስት ለእኔ ሰጠህ። 6 የንጉሡን ዕድሜ አርዝምለት፤ ዘመኑንም እስከ ብዙ ትውልድ ጨምርለት፤ 7 በእግዚአብሔር ፊት ለዘላለም ይንገሥ፤ ይጠብቁት ዘንድ ምሕረትህንና ታማኝነትህን አዘጋጅለት። 8 ስለዚህ ለስምህ ዘወትር ውዳሴ አቀርባለሁ፤ ስእለቴንም በየጊዜው እፈጽማለሁ። |
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.
Biblica, Inc.